የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ (ክፍል አንድ)

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በሰዎች የመነገድ ድርጊት ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመነገድና ለብዝበዛ ዓላማ በማከናወን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሰው ልጆች የመኖር ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋን የጋረጠ ተግባር ነው፡፡ በሰዎች መነገድ በሀገር ውስጥ ወይም ከሀገር ውጪ ሰዎችን በማዘዋወር ሊፈፀም ይችላል፡፡ ይህ ተግባር በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በተለያየ መንገድ እና ምክንያት ሊፈፀም የሚችል ሲሆን ለድርጊቱ በብዛት ተጋላጭ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ሴቶች እና ሕፃናት ይገኙበታል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 1 ህፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው ማለት ነው ይላል። የሀገራችንን ህጎች ስንመለከትም በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 215 መሠረት ህፃን በማለት ትርጉም ባይሰጥም ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሰው ጾታ ሳይለይ ማንኛውም እድሜው 18 ዓመት ያልሞላው ልጅ ማለት እንደሆነ ያመለክታል። በተጨማሪም በሰው የመነገድና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/12 አንቀጽ 2(10) መሠረት ህፃን ማለት ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ነው፡፡

ሕፃናት በሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጪ በሰዎች የመነገድ ድርጊት በመጋለጥ ለከፍተኛ ጉዳት ሲዳረጉ ይስተዋላል፡፡ ሕፃናትን በሰዎች የመነገድ ድርጊት ተጋላጭ የሚያደርጓቸው የተለያዩ ምክንያች ያሉ ሲሆን እድሜያቸው ውሳኔ የመወሰን አቅማቸው ላይ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ በተጓዳኝ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደ ዋና መንስኤ ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ በሰዎች የመነገድ ድርጊት የተዳረጉ ሕፃናት ከሚደርሱባቸው ጉዳቶች መካከል የጉልበት ብዝበዛ ዋንኛው ነው፡፡ ይህም ሕፃናትን ለከፋ የአካል እና የስነ-ልቦና ጉዳት ይዳርጋቸዋል፡፡

በዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች፣ አህጉራዊ ስምምነቶች እንዲሁም በአገራችን የሕግ ማዕቀፍ የሕፃናት መብቶች መከበር እንዳለባቸው የተደነገገ ቢሆንም የሕግ ድንጋጌዎችን በሚጥስ መልኩ ሕፃናት ተጎጂ ሆነው እናገኛለን፡፡ በመሆኑም በሕፃናት የመነገድ ድርጊትና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምክንያት በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እንዲሁም ጉዳት አድራሾችን ለመቅጣት የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች እና ህጎች በስራ ላይ ውለዋል፡፡

ይህ የንቃተ ሕግ ትምህርታዊ ፅሑፍ በሁለት ክፍል የቀረበ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል ምንነት በአጠቃላይ፣ ሕፃናትን ለሰዎች የመነገድ ድርጊትና ጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ የሚያደርጓቸው መንስኤዎች እና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ አይነቶችና የሚያስከትሉት ጉዳት እንመለከታለን፡፡ በክፍል ሁለት በሕፃናት የመነገድ ድርጊትና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በኢትዮጵያ ህጎች ያለው ሽፋን ይዳሰሳል፡፡

በሰዎች የመነገድ ድርጊት ምንነት በአጠቃላይ

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰዎች የመነገድ ድርጊት በተለይም በሴቶችና ሕጻናት የመነገድ ድርጊት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት በወጣው እና ሀገራችን ባፀደቀችው ፕሮቶኮል አንቀጽ 3 መሠረት በሰዎች የመነገድ ድርጊት የሚከተለውን ትርጉም ይዞ እናገኘዋለን፡፡

“በሰዎች የመነገድ ድርጊት ማለት ብዝበዛን ዓላማ በማድረግ ዛቻን፣ ኃይልን ወይም ሌላ የማስገደጃ ዘዴ በመጠቀም፣ በማገት፣ በመጥለፍ፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም የተስፋ ቃል በመስጠት፣ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ የሰዎችን ለጥቃት ተጋላጭነት በመጠቀም ወይም ስለሌላው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት መደለያ ወይም ጥቅም በመስጠት ወይም በመቀበል ሰዎችን መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማዘዋወር፣ ማስጠለል ወይም መቀበል ሲሆን የብዝበዛ ተግባር ቢያንስ በሌሎች ሰዎች ዝሙት አዳሪነት መጠቀም ወይም ሌላ ማንኛውም አይነት ወሲባዊ ብዝበዛን፤ የጉልበት ብዝበዛ፣ የግዳጅ ሥራ ወይም አገልጋይነት፤ ባርነት ወይም ባርነት መሰል ተግባር፤ የሰው ልጅን አካል ማውጣት ወይም መውሰድን ያካትታል፡፡” ስለሆነም እነዚህ ድርጊቶች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች በሆኑ ሕፃናት ላይ የተፈፀሙ እንደሆነ በሕፃናት የመነገድ ድርጊት ይሆናል ማለት ነው፡፡

በዚህ መግለጫ ውስጥ ሶስት መሠረታዊ ፍሬ ነገሮች ማለትም ተግባር (The Act, What is done)፣ አደራረግ/ዘዴ (The Means, How it is done) እና ዓላማ (The Purpose, Why it is done) መሟላት ያለባቸው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በተጨማሪም ከብዝበዛ ተግባራት ውስጥ የጉልበት ብዝበዛ በፕሮቶኮሉ የተካተተ በመሆኑ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በዚሁ የሚሸፈን መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በመሆኑም በሰዎች የመነገድ ድርጊት እና የጉልበት ብዝበዛ የማይነጣጠሉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እርግጥ የብዝበዛው አይነት እንደ ተጎጂው አይነት የሚለያይ ቢሆንም ማለትም በሴቶች ላይ የሚደረገው ብዝበዛ እና በወንዶች ወይም በሕፃናት ላይ የሚደረገው ብዝበዛ ሊለያይ ቢችልም ድርጊቱ ግን በሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት ላይ ጉዳትን ማስከተሉ አጠያያቂ አይደለም፡፡

በፕሮቶኮሉ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ፍሬ ነገሮች መቀመጣቸው አንድ ድርጊት በሰዎች የመነገድ ድርጊት ውስጥ ይወድቃል ወይስ አይወድቅም የሚለውን ለመወሰን የአለም ሀገራት ወጥነት ያለው እና ስምምነት የተደረሰበት (consistency and consensus) መለኪያ እንዲጠቀሙ የሚያደርጋቸው ሲሆን ይህንም በህጎቻቸው ውስጥ እንዲያካትቱ ይረዳቸዋል፡፡ የፕሮቶኮሉ አንቀጽ 5 በፕሮቶኮሉ አንቀጽ 3 ስር የተቀመጡትን ድርጊቶች ሀገራት በህጎቻቸው ውስጥ በወንጀል የሚያስቀጡ ተግባራት እንደሆኑ (criminalized in domestic legislation) መደንገግ እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ ከሀገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ለተግባራዊነቱ ጠቀሜታ ስለሚኖረው ነው፡፡

በሌላ በኩል ከሰዎች የመነገድ ድርጊት ጋር የሚነሳው ጉዳይ የፍቃድ ወይም የስምምነት (consent) ጉዳይ ነው፡፡ በፕሮቶኮሉ አንቀጽ 3/ለ/ ስር እንደተደነገገው ለመነገድ ድርጊት ስምምነቱ የተገኘው በዛቻ፣ በኃይል፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም የተስፋ ቃል በመስጠት፣ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ የሰዎችን ለጥቃት ተጋላጭነት በመጠቀም ወይም ሌሎች የተከለከሉ መንገዶችን በመጠቀም ከሆነ ተገጂው ተስማምቷል ወይም ፍቃዱን ሰጥቷል ለማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም የበሰዎች የመነገድ ድርጊት ፈፃሚዎች የተጎጂውን ፍቃደኝነት ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ እንደመከላከያ ሊያነሱት አይችሉም፡፡ ሕፃናትን በተመለከተ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱት መንገዶች (The Means) ተግባራዊ ባይደረጉም በሕፃናት የመነገድ ድርጊት ከተከናወነ የወንጀል ድርጊቱ ተፈፀመ ማለት ይቻላል፡፡

በሁለቱም ጊዜ ማለትም አዋቂዎች ፍቃዳቸውን በተለያዩ ተፅዕኖ ውስጥ ሲሰጡ እንዲሁም ሕፃናት በተፅዕኖም ይሁን ያለተዕፅኖ በሰዎች የመነገድ ድርጊት ሲጋለጡ ስምምነታቸውን ሰጥተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ በምንም አይነት ሁኔታ ለብዝበዛ ነፃ ፍቃዱን ይሰጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በዚህ ጊዜ የአዋቂዎች ፍቃድ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንደተገኘ፣ ሕፃናት ደግሞ ተጋላጭ (vulnerable) በመሆናቸው ፍቃድ መስጠት እንደማይችሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሕፃናትን በሰዎች የመነገድ ድርጊትና ጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ የሚያደርጓቸው መንስኤዎች

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ሕፃናት ለእድሜያቸው የማይመጥን፣ የህፃናቱን የጤና፣ የእድገት፣ የማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ደህንነታቸውን የሚጎዳና ለህይወታቸው አስጊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲሰሩ የሚያስገድድ ተግባር ነው። ይኸውም የሕፃናትን ጉልበት በክፍያም ሆነ በነፃ፣ በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ያላግባብ በመጠቀም ሕፃናትን ለጥቃትና ብዝበዛ ማጋለጥን ያመለክታል።

ሕፃናትን ለጉልበት ብዝበዛ ከሚያጋልጡ ተግባራት ውስጥ በሰዎች የመነገድ ድርጊት አንዱ ነው፡፡ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን በሚያስከትሉ ስራ ላይ የተሰማሩ ህጻናት አብዛኛውን ጊዜ በሰዎች የመነገድ ድርጊት ደላሎች አማካኝነት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከገጠር ወደ ከተማ እንዲኮበልሉ የተደረጉ ናቸው። እንዲሁም በማሳደግ ሰበብ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ለብዝበዛ የሚጋለጡ ሕፃናት ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡

በሰዎች የመነገድ ድርጊት ዓላማው በብዝበዛ ትርፍ ወይም ጥቅም ማግኘት በመሆኑ ህፃናቱ ከሚሰሩት የስራ አይነት በተጨማሪ የጉልበት ብዝበዛን የሚያሳዩ አመላካቾችንም መረዳት የሚያስፈልግ ሲሆን የህጻናትን ጤናማ ስራ ማለትም ቤተሰቦቻቸውን ለማገዝ ከሚሰሩት ስራ እና በሕግ በተፈቀደው የእድሜ ክልል የሚሰራ የስራ አይነት ከጉልበት ብዝበዛ ለይቶ መገንዘብ ይጠቅማል። አመላካቾች ተብለው ከሚጠቀሱት የሚከተሉት ይገኙበታል፦ የህጻናቱ እድሜ፣ በስራው ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ፣ የስራው ጸባይ፣ የስራው አካባቢ፣ የህጻናቱን የመማር መብት የሚነፍግ መሆን አለመሆኑ፣ ሲሰሩ የቤተሰብ ወይም አሳዳጊ ጥበቃና ክትትል መኖሩና አለመኖሩ የመሳሰሉት ሁኔታዎች ናቸው።

ብዙ ጊዜ ህጻናትን ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ድህነት በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ብዙ ደሃ ቤተሰቦች ኑሯቸውን ለመደጎም ሲሉ ለስራ ያልደረሱ ህጻናትን የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ለቤተሰቡ ተጨማሪ ገቢ እንዲያስገኙላቸው ይጥራሉ። በዚህም ምክንያት ቤተሰቦቻቸው በተለያየ ተፅዕኖ ስር በመሆን ህፃናቱ በሰዎች የመነገድ ድርጊት ፈፃሚዎች እጅ እንዲወድቁ ያደርጋሉ፡፡

ህጻናትን ለጉልበት ብዝበዛ የሚያጋልጣቸው ሌላው ምክንያት ከባህላችንና ከልምዳችን ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኛዎቹ ህዝቦች ህጻናት በለጋ እድሜያቸው የተለያዩ እውቀቶችና ክህሎቶች እንዲኖራቸው በማሰብ በስራ ላይ እንዲሰማሩ ይደግፋሉ ይገፋፋሉም። ይህም ወደ ፊት ህጻናት ከራሳቸው በተጨማሪ ለወላጆቻቸው የሚሰጡትን ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

ሌሎች መንስኤዎች በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብና በተቋማት ደረጃ ሊገለጹ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው። በግለሰብ ደረጃ አጋላጭ መንስኤ ሊሆን የሚችል ለምሳሌ አንድ ህጻን አካል ጉዳተኛነቱ ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ መሆኑን ይበልጥ ያጠናክረዋል። ይኸውም ህፃኑ በልመና ስራ ላይ ተሰማርቶ ገቢ እንዲያስገኝ ሊደረግ ይችላል፡፡ ሌላው የትምህርት እድል ያላገኙ ህጻናትም እንደዚሁ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ይሆናል። በቤተሰብ ደረጃ ሲታይ ደግሞ የወላጆች ሞት፣ በቂ የገቢ ምንጭ አለመኖር፣ የወላጆች የትምህርት ደረጃ ማነስ፣ የቤተሰብ መፍረስ፣ ግጭትና የቤት ውስጥ ጥቃቶች የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በማኅበረሰብ ደረጃ ደግሞ የጾታ ልዩነት፣ መድሎ፣ የማህበረሰቡ ባህልና የአኗኗር ሁኔታ የህጻናቱን ተጋላጭነት ከሚያጠናክሩ መንስኤዎች ይጠቀሳሉ። በተቋም ደረጃ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች መሠረታዊና ማኅበራዊ ተቋማት ያለመስፋፋታቸው፣ ምቹ የትምህርት አካባቢ ያለመመቻቸት፣ የሕግ ማዕቀፍና የፖሊሲ ክፍተቶች፣ የልደት ምዝገባ አለመስፋፋት ወ.ዘ.ተ የሚጠቀሱ መንስኤዎች ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱት ድህነትና ሌሎች ቀስቃሽ መንስኤዎች ህፃናቱን በሰዎች የመነገድ ድርጊት በማጋለጥ አልያም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። የህጻናትን ጉልበት ተጠቃሚዎች ከአዋቂዎች ይልቅ ህጻናትን ለመመልመል/መቅጠር የሚፈልጉበት የሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ፡- ሕፃናት እንደ አዋቂዎች ለጉልበታቸው ዋጋ የመከራከር አቅም ስለሌላቸው፣ ሕፃናት ለአዋቂዎች ታዛዦች ሆነው ማገልገል ይችላሉ ተብሎ ስለሚገመት፣ በርካሽ ሊገኝ የሚችል ጉልበት ተደርጎ ስለሚገመት፣ ለረጅም ጊዜ በታማኝነት ሊያገለግሏቸው እንደሚችሉ በማሰብ፣ ወ.ዘ.ተ የሚሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች የሕፃናትን በተለየ ሁኔታ በሰዎች የመነገድ ድርጊት ተጋላጭነት (a position of vulnerability) ያመላክታሉ፡፡

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ አይነቶችና የሚያስከትሉት ጉዳት

በሕፃናት የመነገድ ድርጊት (child trafficking) ሕፃናትን የመሸጥ፣ የመግዛት እንዲሁም የማዘዋወር ተግባርን የሚያካትት ሲሆን ይህም የሕፃናት ጉልበት ለመበዝበዝ ዓላማ የሚከናወን ተግባር ነው፡፡ ሕፃናት ለተለያየ ዓላማ መጠቀሚያነት ከቦታ ወደ ቦታ ሊዘዋወሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ፡- ለጾታዊ ብዛበዛ (sexual exploitation)፣ ለጉልበት ብዛበዛ፣ ለወታደርነት፣ በልመና እና በወንጀል ድርጊቶች ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ እና ለመሳሰሉ ድርጊቶች መጠቀሚያነት ሊመለመሉ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ በሕፃናት ላይ ከሚደረጉ የጉልበት ብዛበዛ አይነቶች ውስጥ የቤት ውስጥ ስራ፣ ባርነት ወይም የግዴታ ስራ፣ ዝሙት አዳሪነት፣ በወንጀል ድርጊቶች እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በልመና ተግባር ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ እና የደመወዝ ስራ( በአነስተኛ ክፍያ) ማሰራት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ከብዝበዛ አይነቶች አንዱ የሆነው የሰውነት ክፍልን ማውጣት በሕፃናት ላይ ሊፈፀም ይችላል፡፡

በሌላ በኩል በሕፃናት የመነገድ ድርጊት እና የጉልበት ብዛበዛ በህፃናቱ ጤናና እድገት ላይ ከሚያደርሰው ተፅእኖ በተጨማሪ በማህበረሰቡም ላይ የሚኖረው ጉዳት ቀላል አይደለም። ከሁሉም በላይ ለሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሚዳርግ በሕፃናት የመነገድ ድርጊት መስፋፋት በሁለት መልኩ ማኅበራዊ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይኸውም በአንድ በኩል በሰው የመነገድ ድርጊት መስፋፋት በማህበረሰቡ ውስጥ ህገ-ወጥነትንና ወንጀል እንዲበራከት አይነተኛ ምክንያት ይሆናል። በሰው የመነገድ ድርጊት ፈፃሚዎች በተለይም በድንበር ዘለል የመነገድ ድርጊት ላይ የሚሳተፉት በአብዛኛው ከሌሎች ወንጀሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደሆነ ይጠቀሳል። በሌላ በኩል ደግሞ የብዝበዛ ሰለባ የሆኑት ሕፃናት ራሳቸው ለአደንዛዥ እፆችና ለተለያዩ ሱሶች ስለሚጋለጡ ይኸውም ሁኔታ ወደ ወንጀል ነክ ተግባራት እንዲገቡ በመገፋፋት ማኅበራዊ ጠንቅን ሊፈጥር ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ለችግሩ ሰለባ የሆኑት ሕፃናት ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲመለሱ ወይም ከተሰማሩበት ቦታ ሆነው ቤተሰቦቻቸውን በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ ለመርዳት ሲሞክሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የመነገድ ድርጊትን ይበልጥ በማነሳሳት ማህበረሰቡ ከችግሩ ይልቅ በሚገኘው ገንዘብ ላይ እንዲያተኩርና ለብዝበዛው የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረው በማድረግ ማኅበራዊ ችግርን ሊፈጥር ይችላል።

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ላይም አሉታዊ ተፅእኖን ያስከትላል። ከድህነት ጋር በተያያዙ ልዩ ልዩ ምክንያቶች በሀገር ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ በሚደረገው በሰው የመነገድ ድርጊት የወደ ፊት ሀገር ተረካቢ ሊሆን የሚችለውን በርካታ አምራች የሰው ኃይል ማጣት ሊያስከትል ይችላል። በአጠቃላይ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ለወደፊት ትልቅ አምራች የሚሆንን ትውልድ በአጭር የሚቀጭ ድርጊት ነው፡፡

በአጠቃላይ በድርጊቱ ሕፃናት ከቀላል የአካል ጉዳት እስከ ሞት ለሚደርስ ጉዳት ሊጋለጡ ወይም እድሜ ልክ ለማይሽር አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጉዳት ሊዳረጉ ይችላሉ። በመሆኑም በሕፃናት የመነገድ ድርጊትና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የህፃናቱን የመኖር፣ የመማር፣ የጨዋታ፣ እንክብካቤና ጥበቃ የማግኘት መብታቸውን የሚያሳጣ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ድርጊቱ እንዳይፈፀም መከላከል፣ ተፈፅሞም ሲገኝ ፈፃሚዎች የሚቀጡበትን ስርዓት መዘርጋትና ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

ተቀራራቢ ጽሑፎች