የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምንነት
ሕፃን የሚለዉ ቃል የማሕበራዊ ትርጉሙ እንደየማሕበረሰቡ አኗኗርና ባህላዊ ሁኔታ የሚለያይ ሊሆን ይችላል። የተባብሩት መንግስታት የሕጻናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 1 ላይ ሕጻን ማለት ማንኛዉም ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው ማለት ነው በማለት ገልጾታል። በሀገራችንም ሕጻን ማለት ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው መሆኑ በሰው የመነገድና ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/12 ዓንቀፅ 2(10) ስር ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ሕጻን የሚለዉ ትርጉም 18 ዓመት ያልሞላው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሰው መሆኑ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር ውስጥ ሕግ የተረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል።
የሕጻናት ስራ ማለት ማንኛውም ሕፃን ሀገሪቱ ከደነገገችው ዝቅተኛ የስራ ቅጥር የዕድሜ ገደብ በታች ሆነው የሚሰሩት ለዕድሜያቸዉ የማይመጥን ስራ ማለት ነው። ሆኖም ግን የሕጻናት ጉልበት ስራ ጉዳት በማያስከትልና ጤናማ በሆነ መልኩ ሊከናወን ይችላል።
የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ግን የዚህ ተቃራኒ ሆኖ ማለትም በሕግ ከተፈቀደው ሁኔታ ውጭ ወይም ለሕጻኑ አካል ወይም ዕድሜ በተፃረረ መልኩ ስራ እንዲሰራ ወይም አገልግሎት እንዲሰጥ መድረግ ስለመሆኑ በአ/ቁ 1178/12 ዓንቀፅ 2(5) ላይ ሰፍሯል፡፡
የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች፡- ምንም እንኳን ሕጻናት በብዙ ዓይነት ስራ ተሰማርተው ስለሚገኙ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶችን መለየት አስቸጋሪ ቢሆንም ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
- የቤት ውስጥ ስራ፡- ይህ የስራ ዓይነት ሕጻናት በወላጆቻቸው ወይም በአሳዳጊዎቻቸው ቤት ሆነው የሚሰሩት ስራ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በክፍያ ከቤተሰባቸው ውጭ በቤት ሠራተኛነት የሚሰሩ ሕጻናትም በዚሁ ስር የሚካተቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ህጻናት ከእይታ የራቁና መረጃ የማይገኝባቸው በመሆናቸው ለብዙ ዓይነት ብዝበዛና ጥቃት የተጋለጡ ናቸው። ይህ ማለት ግን ሕጻናቱ አቅማቸው የሚችለውን ያክል ቤተሰቦቻቸውን መርዳታቸው ብዝበዛ ነው ማለት አይደለም፡፡
- የደመወዝ ስራ፡- ይህ የህሕናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነት መደበኛ ወይም ኢ-መደበኛ፣ ህጋዊ ወይም ህገወጥ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያክል በኮንስትራክሽን ድርጅት፣ በማምረቻ ድርጅት፣ በማእድን ስራ፣ በአግሮ ኢንደስትሪ እንዲሁም በወንጀል ስራ ሕጻናት የሚቀጠሩባቸው መስኮች ናቸው።
- ከቤት ውጭ ያለ ያለክፍያ ስራ፡- ይህ የስራ ዓይነት በብዛት የተለመደው በግብርና ስራዎች ላይ ነው። በተለይ በታዳጊ ሀገሮች ሕጻናት በግብርና ስራ ላይ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት በለጋ እድሜያቸው ስራ ይጀምራሉ።
- ባርነት ወይም የግዴታ ስራ፡- ሕጻናት ምንም በማያውቁት ሁኔታ በገንዘብ ለስራ ይሸጣሉ። አንዳንዴም ባለሀብቶች ከሰራተኞቻቸው የሕጻን ልጆቻቸውን ጉልበት ይገዛሉ። በሌላ በኩል ሕጻናት የወላጆቻቸው ዕዳ መያዣ ይሆናሉ። ይኸውም የሕጻኑ ወላጆች ያለባቸውን ዕዳ መክፈል ሲያቅታቸው ሕጻን ልጃቸውን ለባለ መብቱ አሳልፈው ይሰጣሉ።
የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ መንስኤዎች፡- ብዙ ጊዜ ሕጻናትን ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ድህነት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ይደረጋል። ብዙ ደሃ ቤተሰቦች ኑሯቸውን ለመደጎም ሲሉ ለስራ ያልደረሱ ሕጻናትን የተለያዩ ስራዎችን እንዲያከናዉኑና ለቤተሰቡ ተጨማሪ ገቢ እንዲያስገኙላቸዉ ይጥራሉ። ሆኖም ግን ድህነት ብቻውን ለሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ መንስኤ ሊሆን አይችልም።
ሕጻናትን ለጉልበት ብዝበዛ የሚያጋልጣቸው ሌላው ምክንያት ከባህላችንና ከልምዳችን ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኛው ሰው ሕጻናት በለጋ ዕድሜያቸው የተለያዩ ዕውቀቶችና ክህሎቶች እንዲኖራቸው በማሰብ በስራ ላይ እንዲሰማሩ ይደግፋሉ ይገፋፋሉም። ከድህነቱ በተጨማሪ አንድ ሕጻን አካል ጉዳተኛነቱ ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ መሆኑን ይበልጥ ያጠናክረዋል። የትምህርት ዕድል ያለመኖርም ሌላው ገፊ ምክንያት ነው። የወላጆች ሞት፣ በቂ የገቢ ምንጭ አለመኖር፣ የወላጆች የትምህርት ደረጃ ማነስ፣ የቤተሰብ መፍረስ፣ ግጭትና የቤት ውስጥ ጥቃቶች የመሳሰሉትም በመንስኤነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ የሚያስከትለው ጉዳት፡- የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በህፃናቱ ላይ ከሚያሰከትለው ከፍተኛ የአካላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ማኅበራዊና የመሳሰሉት ጉዳቶች ባለፈ በህብረተሰብና በሀገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው። በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምክንያት በሕፃናቱ ላይ በቀጥታ ከሚደርሱ ጉዳቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የጤና ጉዳት ነው። የብዝበዛ ሰለባ የሆኑ ሕፃናት ከቀላል የአካል ጉዳት እስከ ሞት ለሚደርስ ጉዳት ይጋለጣሉ ወይም ለዕድሜ ልክ ለማይሽር አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጉዳት ሊዳረጉ ይችላሉ።
በሕፃናቱ ላይ ከሚያስከትለው ተፅእኖ በተጨማሪ በማህበረሰቡም ላይ የሚኖረው ጉዳት ቀላል አይደለም። የአዘዋዋሪዎች መስፋፋት በማህበረሰቡ ውስጥ ህገወጥነትንና ወንጀል እንዲበራከት ዓይነተኛ ምክንያት ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ የብዝበዛ ሰለባ የሆኑት ሕፃናት ራሳቸው ለአደንዛዥ ዕፆችና ለተለያዩ ሱሶች ስለሚጋለጡ ወደ ወንጀል ነክ ተግባራት እንዲገቡ ያደርጋል።
የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሀገር ኢኮኖሚ ላይም አሉታዊ ተፅእኖ ያስከትላል። ከድህነት ጋር በተያያዙና በልዩ ልዩ ምክንያቶች በሀገር ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ በሚደረገው የህገወጥ የሕፃናት ዝውውር የወደፊት ሀገር ተረካቢ ሊሆን የሚችለውን በርካታ አምራችና ብቁ የሰው ኃይል ማጣትን ሊያስከትል ይችላል።
የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን የሚመለከቱ የሕግ ማእቀፎች፡- በሀገራችን በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለመቆጣጠር የሚስችሉ ዓለም አቀፋዊም ሆነ ሀገራዊ የሕግ ማእቀፎች መኖራቸው ችግሩን ለመቅረፍ የሚጠቀስ ምቹ ሁኔታ ነው። ሆኖም ግን ከሕግ ክፍተቱ ባሻገር ህሕን የማስፈጸም እንቅስቃሴዎች በሚገባ የዳበሩ ባለመሆናቸው ችግሩ ከሕግ አንጻር ተገቢውን ትኩረት አግኝቷል ለማለት አያስችልም።
ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች፡- በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን፣ የአፍሪካ ሕጻናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር፣ የዓለም ስራ ድርጅት አነስተኛ የስራ ስምሪት ዕድሜ መወሰኛ ስምምነት ቁጥር 138/1973 እና የአስከፊ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ማስወገጃ ስምምነት ቁጥር 182/1999 የሚጠቀሱ ናቸው። በእነዚህ ስምምነቶች የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ ክልከላ የሚያደርጉ አንቀጾች ተካተዋል።
ሀገር አቀፍ ህጎች፡- በኢትዮጵያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ ክልከላና ጥበቃ የሚያደርጉ ህጎችና ድንጋጌዎች አሉ። ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ በኢፌድሪ ሕገመንግሥት፣ በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ፣ በኢፌድሪ የወንጀል ሕግና በአዋጅ ቁጥር 1178/12 ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እነዚህ ሕጎች የሕጻናት መብቶችን የሚያስከብሩ፣ ዝቅተኛ የስራ ስምሪት ዕድሜን የሚወስኑ ወዘተ ድንጋጌዎችን የያዙ ሲሆን ድንጋጌዎቹ ተጥሰው ሲገኙ ደግሞ ከ7-15 ዓመት ሊደርስ በሚችል የእስራት ቅጣት ድርጊቱ በከባድ ሁኔታ ተፈፅሞ ከተገኘም እስከ 25 ዓመት ብሎም በዕድሜ ልክና በሞት ቅጣትም የሚያስቀጡ ሕጎች ናቸው፡፡ (አዋጅ ቁጥር 1178/12 ዓንቀፅ 3 እና 4ን ይመልከቱ)