የንግድ ሥራ ፍቃድ መስፈርቶች እና የነጋዴዎች መብትና ግዴታ

ማውጫ

Share this Article

ንግድ በሀገር ኢኮኖሚም ሆነ በዜጎች የእለት ተእለት ህይወት ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው ዘርፍ እንደመሆኑ የሚካሄድበት የራሱ የሕግ ማዕቀፍና ሥርአት ያለው ነው፡፡ በዚህም መሠረት የንግድ ሥራ ለማከናወን የሚፈልግ ሰው የፀና የንግድ ፈቃድ ሊኖረው የሚያስፈልግ ሲሆን የንግድ ሥራውን በሚያከናውንበትም ጊዜ በህጉ የተጣሉበትን ግዴታዎች እንዲወጣ ይጠበቃል፡፡

በዚህ አጭር ጽሑፍ በሀገራችን የንግድ ሥራ ፍቃድ የምስክር ወረቀት ለማውጣት መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች እና የንግድ ሥራ ፍቃድ የተሰጠው ነጋዴ መብትና ግዴታ ከአዋጅ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 እና ከማሻሻያው አዋጅ 1150/2011 እንዲሁም አዋጁን ለማስፈፀም በሚንስቴሮች ምክር ቤት ከወጣው ደንብ ቁጥር 392/2009 እና ከማሻሻያ ደንብ ቁጥር 461/2012 አንፃር እንመለከታለን፡፡

የንግድ ሥራ ፈቃድ ምንነት

የንግድ ሥራ ፈቃድ ማለት ነጋዴ የሆነ ሰው የንግድ ሥራውን እንዲያከናውን ከሚመለከተው አካል የሚሰጥ ፈቃድ ሲሆን ይህ ፈቃድ የፀና ፈቃድ ነው የሚባለው በንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 መሠረት በበጀት አመቱ የተሰጠ ወይም የታደሰ ወይም ያለቅጣት የሚታደስበት ጊዜው ያላለፈበት ሲሆን መሆኑን ከአዋጁ አንቀጽ 2(12) መረዳት ይቻላል፡፡

የንግድ ሥራ ፍቃድ የምስክር ወረቀት ለማውጣት መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች

ማንኛውም ነጋዴ ወይም የንግድ ድርጅት የንግድ ሥራ ፍቃድ ሳያወጣ የንግድ ሥራ መሥራት አይችልም፡፡ ይህን ፈቃድ ለማውጣት ከግለሰብ ነጋዴ፣ የሽርክና ማህበር እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ የአክሲዮን ማህበር እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ንግድ ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች በአዋጅ ቁጥር 980/2008 ዓ.ም የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ እና በ ማሻሻያው አዋጅ 1150/2011 እንዲሁም አዋጁን ለማስፈፀም በሚንስቴሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ቁጥር 392/2009 እና በማሻሻያ ደንብ ቁጥር 461/2012 ላይ በዝርዝር ተደንግጓል፡፡ ይኸውም የንግድ ሥራ ፈቃድ እንዲሰጠው ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀውን የማመልከቻ ቅጽ በመሙላት አግባብ ላለው ባለሥልጣን ማመልከት ያለበት ሲሆን ከማመልከቻ ቅጹ ጋር

የግለሰብ ነገዴ ሲሆን

  • የአመልካች መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ኮፒ
  • የአመልካቹ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሳው ሁለት የፓስፖርት መጠን ያላቸው ፎቶ ግራፎች
  • የንግድ መዝገባ የምስክር ወረቀት
  • አመልካቹ የውጭ አገር ዜጋ ከሆነ የኢንቨስትመንት ፍቃድ
  • የአመልካቹ ዋና የሥራ አድራሻ እና የቅርንጫፍ ያለው ከሆነ ይህንን የሚያረጋግጥ የአድራሻ ማረጋገጫ
  • የሚሰማራበት ዘርፍ የብቃት ማረጋገጫ የሚያስፈልገው ከሆነ ከሚመለከተው አካል የተሰጠ የብቃት ማረጋጋጫ ምስክር ወረቀት

የሽርክና ማህበራት፣ የአክሲዮን ማህበር እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን

  • የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀት
  • የሥራ አስኪያጅ ወይም የወኪል የታደሰ መታወቂያ ወይም የፀና ፓስፖርት
  • የንግድ ማህበሩ ሥራ አስኪያጅ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሳው ሁለት የፓስፖርት መጠን ያላቸው ፎቶ
  • ሰነድን ለማረገገጥ በሕግ ሥልጣን በተሰጠው አካል የተረጋገጠ የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ እና የመተዳደሪያ ደንብ ፎቶ ኮፒ
  • የአመልካቹ ዋና የሥራ አድራሻ እና የቅርንጫፍ የሥራ አድራሻ ያለው ከሆነ ይህንን የሚያረጋግጥ የአድራሻ ማረጋገጫ
  • የሚሰማራበት ዘርፍ የብቃት ማረጋገጫ የሚያስፈልገው ከሆነ ከሚመለከተው አካል የብቃት ማረጋጋጫ ምስክር ወረቀት
  • አመልካቹ የውጭ አገር ዜጋ ከሆነ ወይም በአክሲዮን ማህበር ውስጥ የውጪ ዜጎች ያሉ ከሆነ የኢንቬስትመንት ፍቃድ እና የፀና ፓስፖርት ፎቶ ኮፒ
  • አክሲዮን ማህበር ከሆነ የአክሲዮን ድርሻ ሰርተፊኬት ናሙና እና የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ
  • የሽርክና ማህበራት፣ የአክሲዮን ማህበር እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ውስጥ አባል የሆነው በውጭ አገር የሕግ ሰውነት ያለው ከሆነ ከተቋቋመበት አገር ህጋዊ ሰውነት ያገኘበትን ማረጋገጫ፣ በንግድ ማህበሩ ውስጥ ለመግባት የተወሰነበት ሰነድን ለማረጋገጥ በሕግ ሥልጣን በተሰጠው አካል የተረጋገጠ ቃለ ጉባዔ ወይም ተመሳሳይ ሰነድ እና የኢንቬስትመንት ፍቃድ

የመንግሥት የልማት ድርጅት ሲሆን

  • የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀት
  • የተቋቋመበት ሕግ
  • የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የምደባ ደብዳቤ
  • የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ የታደሰ መታወቂያ ወይም የፀና ፓስፖርት፤
  • የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሳው ሁለት የፓስፖርት መጠን ያላቸው ፎቶግራፎች
  • ማመልከቻው በወኪል የቀረበ ከሆነ በድርጅቱ የበላይ ሀላፊ የተወከለበት ደብዳቤ እና የወኪሉ የታደሰ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ዋነው እና አስፈላጊ ገጾች ፎቶ ኮፒ
  • የአመልካቹ ዋና የሥራ አድራሻ እና የቅርንጫፍ የሥራ አድራሻ ያለው ከሆነ ይህንን የሚያረጋግጥ የአድራሻ ማረጋገጫ
  • የሚሰማራበት ዘርፍ የብቃት ማረጋገጫ የሚያስፈልገው ከሆነ ከሚመለከተው አካል የብቃት ማረጋጋጫ ምስክር ወረቀት

ተያይዞ መቅረብ አለበት፡፡ አግባብ ያለው ባለሥልጣንም የቀረበለት ማመልከቻ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ እና ይህን መሠረት በማድረግ በወጡት ደንብ እና መመሪያዎች መሠረት ሊሟሉ የሚገባቸው መሥፈርቶች ያሟላ እና ሊሰራ ያቀደው የንግድ ሥራ በሕግ ያልተከለከለ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ተገቢውን ክፍያ በማስከፈል ለአመልካቹ የንግድ ሥራ ፈቃድ ምስክር ወረቀት ይሰጠዋል፡፡

የንግድ ስራ ፍቃድ የተሰጠው ነጋዴ መብትና ግዴታዎች

የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ነጋዴ መብት

ማንኛውም የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ነጋዴ

  • አዋጅን፣ አዋጁን ለማስፈፀም የወጡ ደንብ እና መመሪዎች እንዲሁም በሌሎች ሕጎች የተቀመጡ ንግድ ነክ ድንጋጌዎችን በማክበር በተሰጠው የንግድ ፈቃድ መስክ ወሰን የንግድ ሥራዎች የማካሄድ
  • ለተመሳሳይ የንግድ ሥራ ለሚከፍተው ቅርንጫፍ ተጨማሪ የንግድ ሥራ ፈቃድ እንዲያወጣ ያለመገደድ
  • ስለ ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መረጃ የማግኘት
  • በህጉ መሠረት የንግድ ምዝገባን፣ የንግድ ስምን እና የንግድ ፈቃድን የመለወጥና የማሻሻል
  • በአዋጁ፣ አዋጁን ለማስፈፀም በወጡ ደንብ እና በመመሪያዎች የተፈቀዱ ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን የማከናወን መብት አለው፡፡

የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ነጋዴ ግዴታዎች

የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ነጋዴ

  • የንግድ ፈቃድ የተሰጠባቸውን የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን በአንድ ሥፍራ ወይም ግቢ ውስጥ አጣምሮ መሥራት በተጠቃሚው ሕዝብ ጤንነትና ደኅንነት ወይም ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ እነዚህን ሥራዎች በተለያዩ ሥፍራዎች ወይም ግቢዎች በተናጠል የማካሄድ
  • የንግድ ዕቃዎቹንና የአገልግሎቶቹን የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ በግልፅ በሚታይ ቦታ የማመልከት ወይም በንግድ ዕቃዎች ላይ የመለጠፍ
  • የንግድ ሥራው ጠባይ የሚጠይቃቸውን ግዴታዎች የማክበር፣ ደረጃዎችን የማሟላት እና የመሥራት
  • የንግድ ሥራ ፍቃዱን በንግድ ቤቱ ውስጥ በግልፅ በሚታይ ቦታ የማስቀመጥ ወይም የንግድ ቤቱ ቅርንጫፍ ከሆነ የመዝጋቢው አካል ማህተም የተደረገበት የንግድ ሥራ ፍቃድ ፎቶ ኮፒ በንግድ ቤቱ ውስጥ በግልፅ በሚታይ ቦታ የማስቀመጥ
  • የንግድ ፈቃዱን ለሌላ ለማንኛውም ሰው እንዲገለገልበት ወይም በመያዣነት እንዲይዘው ወይም እንዲያከራየው አሳልፎ ያለመስጠት
  • በአስተዳደራዊ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የንግድ ድርጅቱ እንዲፈርስ ወይም የግለሰብ ነጋዴ ንግዱን እንዳያካሂድ ሲወሰንበት የተሰጠውን የንግድ ሥራ ፈቃድ በሥራ ላይ ያለማዋል
  • የአድራሻ ለውጥ ሲያደርግ ለውጡን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመዝጋቢው መሥሪያ ቤት የማሳወቅ
  • አክስዮን ማህበር እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከሆነ በየበጀት ዓመቱ በኦዲተር ሂሳቡን የማስመርመር እና ሪፖርት የማቅረብ
  • ስለንግዱ በሚመለከታቸው አካላት የሚጠየቀውን ማንኛውንም መረጃ የመስጠት
  • በተመሳሳይ ደረጃ ግብይት ያለመፈፀም እና
  • አግባብ ባለው ባለሥልጣን የተወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እና በሕግ የተደነገጉ ሌሎች ግዴታዎችን የማክበር ግዴታ አለበት፡፡

በአጠቃላይ ማንኛውም ሰው የንግድ ሥራ ለመሥራት በህጉ መሠረት የንግድ ፈቃድ ማውጣት ያለበት ሲሆን ሥራውን በሚያከናውንበትም ጊዜ መብት እና ግዴታዎቹን ማወቅ እና አገሪቱ ያወጣችውን ሕግ ማክበር ይጠበቅበታል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ