We Are Prepared to Serve You Better in the New Fiscal Year!

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር በ2015 በጀት ዓመት በአምስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ በመመርኮዝ የላቀ አገልግሎት ለመስጠት በሙሉ አቅሙ ይሰራል፡፡ ምሰሶዎቹም አዲስ እይታ እና ጅማሬ፣ የላቀ የባለሙያ ስነ-ምግባር፣ የላቀ የሙያ ብቃት፤ የተሻለ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የጎንዮሽ ቅንጅቶች ማጠናከር ናቸው፡፡

የባለሙያዎችን እውቀት ከማሳደግ እና ተቋሙን የሚመጥን ክህሎት እንዲላበስ ከማድረግ አንጻር በዘንድሮው በጀት ዓመት ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ ከቁጥር ይልቅ ጥራት ላይ በማተኮር በተመረጡ የተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በዘርፉ የላቀ እውቀት እና ልምድ ባላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ አሰልጣኞች አማካኝነት ሥልጠናዎች እንዲሰጡ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ሥልጠናውን የወሰዱ ባለሙያዎች በሥልጠናው ያገኙትን ተጨማሪ አቅም በመከታተልም በስራቸው ላይ እንዲተገብሩ እና ለውጥ እንዲፈጥሩ የሚደረግም ይሆናል፡፡ በተለይም በዐቃቤያነ ሕግ እና ሌሎች የተቋሙ ባለሙያዎች ላይ በምናካሂዳቸው የተለያዩ ክትትሎች እና ምዘናዎች የእውቀት እና ክህሎት ውስንነት የተስተዋሉባቸውን በመለየት ክፍተቶቹን በበቂ የሚሞሉ ሥልጠናዎችን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር እንዲከታተሉ በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ ተገቢው ጥረት ይደረጋል፡፡

ዜጎች ያለአግባብ ለመበልጸግ ፍላጎት ባላቸው አመራሮች እና ሰራተኞች በህገ መንግሥት የተጎናጸፏቸውን መብቶች በገንዘብ እንዲገዙ መደረጋቸው እየጨመረ የመጣበት፤ አግባብ ያልሆነ እጅ መንሻ ካልሰጡ አገልግሎቱን እንዳያገኙ ወይም ከአሰልቺ መዘግየት በኋላ እንዲሰጣቸው የሚደረግበት ሁኔታ በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ የበላይነትን እና የወንጀል ሕግን የማስከበር ኃላፊነት ያለበት ተቋም እንደመሆኑ መጠን ከራሱ በመጀመር በሁሉም ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች የፍትሕን መርህ ተከትሎ በአግባቡ እንዲመሩ የህጎች ተፈጻሚነትን ከመከታተል ጀምሮ የወንጀል መከላከል ስታራቴጂውን በአግባቡ እንዲተገበር በማድረግ እንዲሁም ጥቆማዎች ምስጢራዊነታቸውን ጠብቀው በሚገባ በማስተናገድ ከፖሊስ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ምርመራ በማድረግ አጥፊዎችን በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን ከማድረግ አንጻር ወንጀሉ በሰጪው እና በተቀባይ መካከል በሚደረግ ስምምነት በከፍተኛ ሚስጥር እና ጥንቃቄ የሚፈጸም ወንጀል በመሆኑ ከወንጀሉ ስፋት ጋር የሚመጣጠን ባይሆንም ባገባደድነው በጀት ዓመት ብዙዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ በቀጣይም የተሻለ የሕግ ማስከበር ስራን ለመሥራት የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ወደ ተግባር ይገባሉ፡፡

ስራው ውጤታማ ይሆን ዘንድ ደግሞ ይህን አደራ የሚሸከመው የተቋማችን ባለሙያ ከሙስና ወንጀል እና የሥነ-ምግባር ጉድለቶች የጸዳ መሆኑን ማረጋገጥ ለነገ የማይባል የቤት ሳይሆን የክፍል ስራችን ነው፡፡ ተቋሙ የሥነ-ምግባር ጉድለትን እና ሙስናን የማይታገስ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ቅንጣት ያህል አንጠራጠርም፡፡ ይህንንም በተቋሙ ባለሙያዎችም ላይ ጭምር በወሰዳቸው እርምጃዎች አሳይቷል፡፡

በቀጣይም ባለሙያው ሙያዊ ግዴታውን በንጽህና እንዲከውን የሚያስችለው ምቹ የስራ ሁኔታን ከመፍጠር አንስቶ ከመስመር የሚወጡ እና መብትን በጥቅም የሚሸጡ የየትኛውም ተቋም ባለሙያዎች ካሉ ያለምንም ማወላዳት ተገቢውን እርምጃ ወስዶ ሌሎችም ከዚሁ ትምህርት እንዲወስዱ ለማድረግ ተገቢው ጥረት ይደረጋል፡፡

በሌላ በኩል ስራን በቴክኖሎጂ መደገፍ እና አሠራርን ማዘመን ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ በነባሩ እና በተለመደው የአሠራር ዘዴ ስራን መምራት የሕዝብን ቅሬታ ከማባባስ አንስቶ ተገልጋይ በተቋሙ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሽር የሚያደርግ በመሆኑ አብዛኛዎቹ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው መሰጠት አለባቸው፡፡ በመሆኑም ተቋማችን ከዚህ ቀደም አልምቶ ወደ ስራ ካስገባቸው ቴክኖሎጂዎች በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን በዘመናዊ ዘዴ ለመስጠት የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን አልምቶ ወደ ስራ የሚያስገባበት እና ፈጣን፤ ቀልጣፋ እና ወጥነቱን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጥበት በጀት ዓመት ይሆናል፡፡

የፍትሕ ስርዓት የሁሉንም ትግግዝ እና ትብብር የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ የፍትሕ ሚኒስቴርም ከፌዴራል እና ከክልል ፍትሕ ተቋማት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር ከምን ጊዜውም በላይ የሚያጠናክርበት በጀት ዓመት እንዲሆን ታስቦ ይህንኑ እውን የሚያደርጉ ስራዎች በዕቅድ እንዲካተቱ ተደርጓል፤ ይፈጸማልሉም፡፡

በተቋጨው በጀት ዓመት በፌዴራል ደረጃ የተካሄዱ የሕግ ሪፎርሞችን ወደ ክልል ለማስፋፋት የተሄደው ርቀት ይበል የሚያስብል ሲሆን ክልሎች የራሳቸውን ህጎች ሊያወጡባቸው በሚገቡ 4 ህጎች ላይ ድጋፍ እና ክትትል ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረት ክልሎች ህጎቹን የማርቀቅ ስራ በማገባደድ ላይ ይገኛሉ፤ በዚህ በጀት ዓመትም አጸድቀው ወደ ተግባር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የተቋሙን የአፈጻጸም አቅም ከማጎልበት እና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ በበላይ አመራሮች በተሰጠ የስራ አቅጣጫ መሠረትም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ስር የሚገኙ ክፍሎች በሀገሪቱ የትኛውም ክፍል የሚፈጸሙ ከባባድ ወንጀሎችን በተመለከተ በልዩ ትኩረት መከታተል እና የወንጀል ምርመራ ስራዎችን የመምራት እና ከሶ አጥፊን የማስቀጣት ስራው ካለፉት በጀት ዓመታት በተሻለ በዚህ በጀመርነው የ2015 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተገቢውን ጥረት የዳርጋሉ፤ አመራሩም በቁርጠኝነት ስራን በልዩ ትኩረት ይመራል፣ ይከታተል፤ ይገመግማል ብሎም ችግሮችን ከስር ከስር በመፍታት የህዝቡን ፍላጎት የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ይሰራል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በዚህም ሆነ በቀጣዮች ዘመናት በሕዝብ ያልተደገፈ እና ያልታገዘ ፍትሕ ስርዓት ውጤታማ ሊሆን አይችልምና በወንጀልም ሆነ በፍትሃ ብሄር ፍትሕ አስተዳር ውስጥ የሕዝብን እና የመንግሥትን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ተቋማችን ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተቻለ ሁሉ በመደገፍ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በማክበር እንጠይቃለን፡፡ ከፍትሕ ስርዓቱ ሁላችንም ተጠቃሚ የመሆናችንን ያህል ሂደቱም የሁላችንን ትብብር ይጠይቃል፡፡

————–//—————

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴርነሀሴ 3/11/2014 ዓ.ም

Share this press release: 

Facebook
Twitter
LinkedIn
Telegram

Other Press Releases