Ministry of Justice Issues Press Statement on Proclamation No. 1364/2017 Regarding Asset Recovery

የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርአያስላሴ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጥር 1ቀን 2017 ዓ.ም የፀደቀዉን የንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017ን አስመልክቶ ለመንግሥት እና የግል የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በዛሬዉ እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 በጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን ተከትሎ የአዋጁን ዓላማ፣ መሠረታዊ ይዘቶች፣ እንዲሁም ቀጣይ አተገባበር በተመለከተ የተፈጠሩ ብዥታዎችን ለማጥራት መግለጫ መስጠት ማሰፈለጉን የገለፁት ክብርት ሚኒስትሯ፣ ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በወንጀል የተገኘ ሃብት ማስመለስን በተመለከተ ራሱን የቻለና ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ያልነበረ በመሆኑ በሕግ ማስከበር ሂደት በጣም ክፍተት ፈጥሯል። የወንጀል ሕጉን ጨምሮ በተለያዩ አዋጆች የሃብት ማስመለስ ሥነ-ሥርዓትን በሚመለከት የተካተቱ ድንጋጌዎች በራሳቸው የተሟሉ ካለመሆናቸው ባለፈ አንዱን ከሌላው ጋር እያስማሙ ለመተግበር አስቸጋሪ የሚያደርጓቸው ድንጋጌዎችን የያዙ እና ተፈጻሚነታቸውም ውስን የሆኑ ወንጀሎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተቀረጹ በመሆኑ በርካታ በማህበረሰቡ ላይ ጉዳትን በሚያደርሱ ወንጀሎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻልም። በዚህም ወንጀል ፈፃሚዎች ከወንጀል ድርጊት ያገኙትን ንብረቶች በማስመለስ ረገድ ከፍተኛ የሆነ የሕግ እና አሠራር ክፈተቶች እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።

ክብርት ሚኒስትሯ አክለውም ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በተመለከተ እስካሁን ባሉን ሕጎች ተጠያቂ የሚሆኑት የመንግሥትና ሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኞች ሲሆኑ ሌሎች ሰዎችን የማይመለከት በመሆኑ ሰፊ በሚባል ደረጃ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት የማፍራት ሁኔታ ተስተውሏል። የዚህ ሕግ አለመኖር ሌሎች የመንግሥትና ሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች በቀላሉ በሕገ-ወጥ መልኩ ያፈሩትን ንብረት በእነዚህ ሰዎች ስም ለማፍራት እና ለመደበቅ እንዲችሉ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል ብለዋል።

በሌላ በኩል አዋጁ የዜጎችን የንብረት መብት ተገቢ ጥበቃ ለማረጋገጥ ብዙ ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ፣ በቅን ልቦና ንብረትን የያዙ ሰዎች በቅን ልቦና የያዙት ንብረት እንዳይወረስ ተገቢውን ጥበቃ ሰጥቷል። ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በሚመለከት ለማስረዳት የሚቀርበው የማስረጃ አይነት እንደየአግባቡ የተለያየ ሊሆን ይችላል። የንብረቱን አመጣጥ የማስረዳት ሸክም ያለበት ሰው በማንኛውም ያስረዱልኛል በሚላቸው የማስረጃ አይነቶች ሊያስረዳ የሚችል ሲሆን የማስረጃው አጥጋቢነት ደግሞ በፍርድ ቤት የሚመዘን ይሆናል። በመሆኑም የንብረት ማስመለስ ሕግ መውጣት ዜጎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸውን የእኩል ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት እና የግለሰቦችን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ንብረት የማፍራት ባህልን በማሳደግ ጠንካራ የሆነ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋዕፆ እንደሚኖረው አመላክተዋል።

የዚህ ሕግ አተገባበር በሰዎች የንብረት መብት ላይ ያልተገባ ተጽዕኖን እንዳይፈጥር እና የሕግ አስፈጻሚ አካላት ባልተገባ አሠራር የዜጎችን መብት እንዳይጥሱ በሚያስችል መልኩ እንዲተገበር አዋጁ የአደረጃጀት እና የአሠራር መፍትሔዎችን አካቷል ያሉት ክብርት ሚኒስተሯ፣ አዋጁ የሚተገበረው በፍትሕ ሚኒስቴር በተማከለ አደረጃጀት ለዚህ ሥራ ዓላማ በሚደራጅ የሥራ ክፍል በመሆኑ ግልጽ የአሠራር ሂደትና የተጠያቂነት ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተገልፆል።

ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በተመለከተ በቅድመ ክስ ሂደት ማንኛውም ሰው ጉዳዩን እንዲያስረዳ የሚቀርቡ ጥያቄዎች እና አቤቱታዎች የፍርድ ቤቶች የሥነ ሥርዓት ሕጎችንና መርሆዎችን ተከትለው ጥብቅ የሆነ ማጣራት የሚደረግባቸው ሲሆን አቤቱታ የሚቀርብባቸውም ሰዎች በሕጉ መሠረት ያላቸውን ማስረጃዎች የማቅረብ እና በፍርድ ቤት ዘንድ ቀርበው የመደመጥ መብታቸው እንዲከበርላቸው ይደረጋል። ለሥራ ክፍሉ የሚቀርቡ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን የሚመለከቱ ጥቆማዎችም ሆነ ጥርጣሬዎች ጥብቅ በሆነ አሠራር የሚጣሩ እና በቂ ምክንያት መኖሩ የሚታመንባቸው ጉዳዮች ብቻ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱበት የአሠራር ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናልም ተብሏል።

በአጠቃላይ የንብረት ማስመለስ ሕግ በኢትዮጵያ ሰዎች ከወንጀል ድርጊት የሚያፈሩትን ሀብት እና ምንጩ ሳይታወቅ የሚያገኙትን ንብረት በመቆጣጠር እና ሲገኝም ለማሕበረሰቡ ተመላሽ እንዲሆን በማድረግ ወንጀል አትራፊ ሥራ እንዳይሆን ማድረግን እና በአጠቃላይ ደግሞ ማኅበራዊ ፍትሕን ማስፈንን ዓላማው አድርጎ የጸደቀ እና ይህንን ዓላማ በሚያሳካ አግባብ ጥብቅ የሆነ የአፈጻጸም ሥርዓትን የሚከተል የሕግ ማዕቀፍ ነው ሲሉ ክብርት ሚኒስተሯ አብራርተዋል።

Share this press release: 

Facebook
Twitter
LinkedIn
Telegram

Other Press Releases