Press Briefing Held On International Investment Lawsuits, National Performance, and Ongoing Reforms

የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ክሶችንና የአገራችንን የእስካሁን አፈጻጸም እና በዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን አስመልክቶ ለሚዲያ አካላት መጋቢት 30/2018 ዓ.ም በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር በተለያዩ አዋጆች በርካታ ስልጣን እና ሀላፊነቶች የተሰጡት ሲሆን በተለይም በአዋጅ ቁጥር 943/2008 ከተሰጡት ስልጣንና ሀላፊነቶች መካከል የህዝብ እና የመንግስትን የፍትሐብሔር ጥቅም ማስጠበቅ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

ምንም እንኩዋን በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ሀገራችን ማሸነፍዋ አዲስ ባይሆንም በወራት ልዩነት የተገኙት እነዚህ ድሎች አስቸጋሪ የክርክር ሂደት የታለፈባቸው እና ከፍተኛ የካሳ ጥያቄ የቀረበባቸው መሆኑ እና ድሉ የተገኘው በተከታታይ መሆኑ ጉዳዩን ለየት እንደሚያደርገው ክብር ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።

ከወር በፊት ሀገራችን ባለድል የሆነችበት አንደኛው ጉዳይ የቱርክ የኮንስትራክሽን ኩባንያ የሆነው Akgun Insaat Makina Sanayii ve Dis Ticaret Ltd. Sti. አቅርቦት ከነበረው ድምሩ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ክስ ሲሆን፣ የኢንቨስትመንት ጥበቃ መብት ጥሰት ደርሶብኛል በሚል ያቀረበው ክስ የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ ከሚያቀርበው ንጹህ የመጠጥ ውኃ ደህነንት አንጻር ሲታይ የአካባቢ ጥበቃ ዓለም አቀፍ ህግጋትን ያከበረ እና መንግስታዊ ኃላፊነቱን እንደተወጣ የሚቆጠር መሆኑን በማመን ክሱ ውድቅ መደረጉን ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ African Asset Finance Company Holding B.V. ወይም በተለምዶ ኢትዮ ሊዝ እየተባለ የሚጠራው በኔዘርላንድ የተመዘገበ ኩባንያ ያቀረበው ሆኖ በተለያዩ የሀገራችን ህጎች የተደነገጉ ግዴታዎችን እንዲያከብር ለማድረግ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎችን እንደኢንቨስትመንት ጥበቃ መብት ጥሰት በመቁጠር ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ እንዲከፈለው የጠየቀበት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴርም የክርክር ሂደቱን በበላይነት እየመራው በውስጥና በውጭ ባለሞያዎች ጥምረት ብርቱ ክርክር እያደረገ መቆየቱን የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው፣በሄግ ኔዘርላንድስ በተደረገው የቃል ክርክር ሂደትም ሀገራችን በተቋማችን ከፍተኛ አመራር ደረጃ ተወክላ ክርክሩን ማድረጉዋን አውስተው፣ ጉዳዩን የተመለከተው ችሎትም በሶስቱም ገላጋይ ዳኞች ተመሳሳይ የስምምነት ድምጽ የቀረበውን ክስ ውድቅ ያደረገው ሲሆን ለክርክር ያወጣነውን ወጭ እና ኪሳራ የተወሰነውን ለሀገራችን እንዲከፈል መወሰኑን ገልፀዋል።

እንደሃገር የሚቀርቡብን መሰል ክሶችን በአግባቡ መምራት ካልቻልን ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው፣ አለም አቀፍ ክሶችን በመርታታችን በአለም አደባባይ የተሟገትነው በቀረቡብን ጥቅሞችና መብቶች ላይ ፍትህን የማስፈን አካል በመሆኑ ሲሆን፣ በረታንባቸው ጉዳዮች የወጡ ወጪዎችን ማስመለሳችን ደግሞ ክስን በማስፈራሪያነት ለሚያውሉ አንዳንድ ባለሃብቶች ህግ አክባሪነትን ያስተማርንበትና በአለም አደባባይ ለእውነት ብቻ መቆም ያለውን ዋጋ ትምህርት የተሰጠበት እንዲሁም እንደ ሃገር ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የፈረምናቸው ስምምነቶችን አክብረን እንደምንንቀሳቀስ እና ለጤነኛ ኢንቨስተሮች ምቹ መሆናችንን ያሳየንበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም በዘርፉ ያለአግባብ የኢንቨስትመትንና ንግድ ነክ ክስ ሰለባ የሆኑ ታዳጊ ሀገራት ያደጉ ሀገራት እርስት መድረክ እንደሆነ የሚነገርለትን ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት መድረክ ላይ በመገኘትና በመርታት ያንጸባረቅንበት መሆኑ በፍትህ መድረኩ በአሸናፊነት የተወጣንበት መሆኑ ተመሳሳይ ክስ ለሚመጣባቸው ሌሎች ሀገራትም ትምህርት ሰጥተናል ብለዋል ፡፡

ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ የሁለትዮዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን የመመርመር እና ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች፣ የግልግል ዳኝነት ዘርፉ እንደሀገር እንዲስፋፋ እና ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች ይበልጥ ዘርፉ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል የግልግል ዳኝነት ህግ እንዲወጣ መደረጉ፣ የኒውዮርክ ኮንቬንሽንን በማጽደቅ በተለይ የኢንቨስተሩ መተማመን እንዲጨምር ማድረግ መቻሉ፣ የክስ እና ክርክር ሂደቱን በበላይነት የሚመራ መዋቅር መደራጀቱ፣ በሀገር ውስጥ የሚቋቋሙ የግልግል ዳኝነት ማዕከላትን ፍቃድ ለመስጠት እና ለመመዝገብ የሚያስችል ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል መቅረቡ፣ በመንግስት በኩልም ሊቋቋም በሚችለው ማዕከል ዙሪያ በዘርፉ ልምድ ካላቸው ባለሞያዎች ጋር በትብብር እየተሰሩ ያሉ ሠራዎች ዓለማቀፍ የክርክር አቅምን ለማሳደግ እና የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ እየተከናወኑ ካሉ የሪፎርም ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸው ተወስቷል፡፡

Share this press release: 

Facebook
Twitter
LinkedIn
Telegram

Other Press Releases