ህጻናት የሚባሉት እስከ ምን ያህል እድሜ ያሉት ናቸው፤ በዓለም ዓቀፍ፣ አህጉራዊ እና በብሔራዊ ህጎች የተጠበቁላቸው መብቶችስ ምንድን ናቸው እና በተጨባጭ ሊፈጸምባቸው የሚችሉ የወንጀል አይነቶች እና ተጠያቂነታቸውስ ለሚሉ ጥያቄዎች አጭር ምላሽ እነሆ፡፡
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለህጻናት የሚሰጡት ትርጓሜ እንደየአካባቢው አኗኗር እና ባህላዊ ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም ከሕግ አንፃር አንድን ሰው ህፃን የሚያደርገው የእድሜው ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በዓለም ዓቀፍ፣ አህጉራዊ እና በብሔራዊ ህጎች የተቀመጠውን የሕፃናት እድሜ ክልል ስንመለከት ሀገራችን በ1984 ዓ.ም ፈርማ ያፀደቀችው የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መብቶች ስምምነት ኮንቬንሽን አንቀጽ 1 እና በ1994 ዓ.ም ፈርማ ያፀደቀችው የአፍሪካ የህጻናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር አንቀጽ 2 መሠረት ህፃን ማለት እድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውንም ሴት እና ወንድን የሚያካትት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡
ሰብዓዊ መብቶች ሰዎች ሰው ሆነው በመወለዳቸው ብቻ ያለምንም ልዩነት የተጎናፀፏቸው እኩል መብቶች ናቸው። ሕፃናትም ሰብዓዊ ፍጡራን እንደመሆናቸው ለሰው ልጆች የተረጋገጡላቸውን መሠረታዊ መብቶች እንዲሁም ከእድሜያቸው ለጋነት የተነሳ የተለየ መብቶች አሏቸው፡፡ ከእነዚህ መብቶች መካከል በሕይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደኅንነት መብት፣ የእኩልነት መብት፣ ሥምና ዜግነት የማግኘት መብት፣ ከወላጆቻቸው ጋር የመኖር መብት እና የሕፃናት ጥቅም የማስቀደም መብቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በዚህም መሠረት የህጻናት መብትና ደኅንነትን ከማስጠበቅ አንጻር የኢፌዲሪ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 36 ላይ አጠቃላይ የህጻናትን መብትና ጥቅም የሚመለከት ጉዳይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በፍትሐብሔር ሕግ፣ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እና ሌሎች ሀገራዊ ህጎች ላይ የተለያዩ መብትና ጥበቃዎች ተካቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ህጻናትን ከተለያየ ጥቃት ለመከላከል እና ተፈፅሞ ከተገኘ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ህጎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በ1996 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የወንጀል ሕግ፤በሰው የመነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012፣ የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 ወዘተ ይገኙበታል፡፡
በተለይ በወንጀል ህጉ ላይ በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በዝርዝር ተካተዋል። የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎችን በአምስት ከፍሎ ያስቀመጠ ሲሆን እነሱም፡-
- በመውለድና በሕፃናት ማንነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣
- በአካልና በስነ ልቦና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣
- የግብረ ሥጋ ድፍረት ወንጀሎች፣
- ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ወንጀሎች እና
- በሕፃናት መነገድ እና የጉልበት ብዝበዛ ወንጀሎች ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በማንም ሰው ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በሕፃናት ላይ የተፈጸሙ እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 84 (1) (ሠ) መሠረት ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ሊያከብድ ከሚችልባቸው ምክንያቶች አንዱ ይሆናል፡፡
በዚህም መሠረት ህጻናት ከእነኚህ ጥቃቶች እና የወንጀል ተግባራት ለመጠበቅ እና ለመከላከል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እና በሀገራችን “የሕፃናት ቀን” በየዓመቱ በህዳር 11 ቀን ይከበራል፡፡ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ፣ በሀገራችን ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ “ምቹና ሰላማዊት ኢትዮጵያ ለሁሉም ሕፃናት” ! በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡
ህጻናት ምቹና ሰላማዊት ኢትዮጵያ ትኖራቸው ዘንድ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡
የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር