የሴቶች ቀን ለምን ይከበራል ብለው ያስቡ ይሆን?

ማውጫ

Share this Article

ይህ በዓል መከበር የጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1908፤ 15 ሺህ ሴቶች በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ወደ አደባባይ በመውጣት ጥሩ ደመወዝ፣ ጥሩ የሥራ ቦታ፣ ጥሩ የሥራ ሁኔታ እና የሥራ ሰዓት ማስተካከያ እንዲደረግ የመብት ጥያቄዎችን በማሰማታቸው፤ በዋናነት ደግሞ ሴቶች መምረጥ እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ለመጠየቅ አደባባይ በመውጣታቸው ሲሆን በዚህ ምክንያት በአመቱ ዕለቱ ብሔራዊ የሴቶች ቀን ተብሎ እንዲከበር ተደረጓል፡፡

ይህ በሆነ በሁለተኛው ዓመት ደግሞ ክላራ ዚክተን የተባለች ሴት በዓሉ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ እንዲከበር በዴንማርክ፣ ኮፐንሐገን በተደረገ ጉባኤ ላይ ከ17 አገራት የተውጣጡ ቁጥራቸው መቶ የሚጠጋ ሴቶች በታደሙበት ጉባኤ ላይ በዓሉ በአለም ደረጃ እንዲከበር ሃሳብ በማንሳቷ የክላርን ሐሳብ ተቀባይነት አገኝቶ በዓሉ በጀርመን፣ ስዊትዘርላንድ ኦስትሪያና ዴንማርክ መከበር የጀመረ ሲሆን ቀስ በቀስ በሁሉም ሀገራት እየተስፋፋ በአለም ደረጃ የሚከበር በዓል ሆነ፡፡

በዚህም መሠረት በአለም ለ112ኛ ጊዜ በኢትዮጲያ ደግሞ ለ47ኛ ግዜ የሚከበር ሲሆን እኔ “የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ይውላል፡፡

ከሴቶች ቀን መከበር ጋር በተያያዘም የመብት እና የእኩልነት ጥያቄዎች አብረው የሚነሱ በመሆናቸው በዓለም ላይ 143 ሃገራት የሴቶች እና ወንዶች እኩልነት አስመልክቶ በሕገ መንግሥታቸው ላይ እንዳሰፈሩ አንድ አንድ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ ህጉ ባስቀመጠውና አግባብ ባለው ሁኔታ የሴቶችና ወንዶች የመብት እኩልነትን በተሻለ ሁኔታ እየፈጸሙ ያሉ ሀገራት በጣም ጥቂቶች እንደሆኑ ይነገራል፤ እነሱም ቢሆኑ የወንድና ሴቶች እኩልነት ሙሉ በሙሉ አረጋግጠዋል ማለት ግን አይደለም፡፡

በርግጥ በአለምም ሆነ በሀገራችን የሴቶች መብት መሻሻሉ የማይካድ ቢሆንም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ የሴቶች መብት ተረጋግጧል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ቀኑን ስናከብር ከበአል አከባበበር ባሻገር በርግጥም ሴቷ የሚገባትን መብት በመስጠትና ከጥቃት እራሷን የምትከላከልበትን መንገድ በመንደፍ፣ በነገሮች ላይ እኩል ተጠቃሚና ውሳኔ ሰጪ በማድረግ፣ ወንዶችና ሴቶች እኩል ሊራመዱበት የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎችን በመገንባት ከቃላት ያለፈ ተግባር ላይ መድረስ ተገቢ ነው፡፡