በወንጀል ጉዳይ የፖሊስ፣ የዐቃቤ ሕግ፣ የፍርድ ቤቶች እና የማረሚያ ቤቶች ሀላፊነት

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ወንጀል የማኅበረሰብን እና የሀገርን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመሆኑ ወንጀልን የመከላከልና ወንጀል ፈፃሚዎችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ የተለያዩ ተቋማትን የተቀናጀ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤቶች እና ማረሚያ ቤቶች የየራሳቸው ሀላፊነቶች ያሏቸው ተቋማት ናቸው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ እያንዳንዳቸው ያለባቸውን ኃላፊነት እንደሚከተለው እንዳስሳለን፡፡

የፖሊስ ኃላፊነት

ፖሊስ የእለት ተእለት የወንጀል መከላከል ኃላፊነት ያለበት ተቋም ነው፡፡ ይህ ማለት ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል እና ተፈፅሞም ሲገኝ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ኃላፊነት አለበት፡፡ ወንጀል በተፈፀመ ጊዜ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ህጎችን ተከትሎ የወንጀል ጥቆማን በመቀበል ምርመራ ማድረግ እና ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ ይሰራል፡፡ ምርመራውን ሲያጠናቅቅ መዝቡን ለዐቃቤ ሕግ ያቀረባል፡፡

የዐቃቤ ሕግ ኃላፊነት

የወንጀል ድርጊት በማንም ላይ ቢፈፀም የሀገርና የመንግሥትን ጥቅም የሚነካ እንደመሆኑ በወንጀል ጉዳይ ክስ የመመስረት እና የመከታተል ኃላፊነት የዐቃቤ ሕግ ነው፡፡ በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ በሚያከናወንበት ወቅት ምርመራው የመምራት ኃላፊነት ያለበት ሲሆን ምርመራው ተጠናቆ መዝገቡ ሲቀርብለትም የቀረበለትን ጉዳይ ከህጉ ጋር በማገናዘብ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ውሳኔውም

  • በምርመራ መዝገቡ በቂ ማስረጃ የቀረበ ከሆነ በጉዳዩ ክስ መመስረት
  • በቂ ማስረጃ የሌለ ከሆነ በወ/ሥ/ሥ/ህጉ አንፅ 42 መሠረት አያስከስስም ውሳኔ መስጠት ወይም
  • በጉዳዩ ተጨማሪ ማስረጃ መቅረብ የሚስፈልግ ሆኖ ካገኘው በወንጀል ሥነ ሥርአት ህጉ አንቀጽ 38 መሠረት ተጨማሪ ማስረጃ እንዲቀርብ ማዘዝ ሊሆን ይችላል፡፡

በጉዳዩ ላይ ክስ ከመሰረተ በፍርድ ቤት ሂደት ክርክሩ የሚቀጥል በመሆኑ ክርክር ያደርጋል፡፡ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ ቅሬታ ካለው ህጉ በሚፈቅደው መሠረት ይግባኝ በማቅረብ ይከራከራል፡፡

የፍርድ ቤቶች ኃላፊነት

ፍርድ ቤት ተከራካሪ ወገኖች ባቀረቡት ጉዳይ ላይ በማከራከር እና የቀረቡ ማስረጃን ከሕግ አንፃር በመመዘን ውሳኔ የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ በወንጀል ጉዳዮችም ዐቃቤ ሕግ ክስ ሲመሰርት በወንጀል ሥነ ሥርአት ህጉ መሠረት በዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ በኩል የሚቀረቡ ማስረጃዎችን በመስማት እና ከህጉ ጋር በማገናዘብ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ በሂደቱም ዳኞች የግራ ቀኙ ተከራካሪዎች የክርክር ሂደት በእኩል ሚዛን የመምራታ፣ ችሎት የማስከበር፣ ዜጎችን በግልፅ ችሎት የማስተናገድ እንዲሁም ሕግን መሠረት ያደረጉ ዉሳኔዎችን ሳይዘገዩ መስጠት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በተጨማሪም በምርመራ እና በክርክር ሂደት በሕግ የተቀመጡ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥና ተጥሰው ሲገኙም ማስተካከያ እንዲደረግ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

የማረሚያ ቤት ኃላፊነት

በፍርድ ቤት የተሰጡ የእስራት ቅጣት ውሳኔዎችን የማስፈፀም እና ታራሚዎች በቆይታቸውም በልዩ ልዩ የማረሚያ ስልቶች እንዲታረሙ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ በአመክሮ መዉጣት ያለባቸዉን እና ፍርዳቸዉን የጨረሱትን ታራሚዎችን በሕግ አግባብ እንዲለቀቁ ያደረጋል፡፡ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ያላቸውን ፍርድ ቤት ያቀርባል፣ ትእዛዝም ይቀበላል፡፡ ታራሚዎች በቆይታቸዉ ጊዜ እዉቀት እና ክህሎት እንዲያገኙ እንዲሁም በሥነ ምግባር ታንፀዉ እንዲወጡ የማደረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ በተጨማሪም ታራሚዎች በቆታቸው ከጠበቃዎች፣ ከሀይማኖት አባቶች እና ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር የመገናኘት መብታቸዉ እንዲረጋገጥ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸዉ፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርተና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ