የጋብቻ አፈፃፀም በተሻሻለው የፌዴራል ቤተሰብ ሕግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ጋብቻ በሀገራችን ለዘመናት አክብሮት ተሰጥቶት የኖረ የማኅበራዊ መስተጋብራችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ጋብቻ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን የሚያስከትል እንደመሆኑ ከምስረታው ጀምሮ በሕግ የሚገዛ እና ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጽሑፍም የጋብቻን ምንነት፣ በህጉ እውቅና ያላቸውን የአፈፃፀም ሥርአቶች እና ጋብቻ ለመመስረት ሊሟሉ የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በአጭሩ የምንመለከት ይሆናል፡፡

የጋብቻ ምንነት

ጋብቻ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ ቀጥተኛ ትርጓሜ ባይሰጠውም ከህጉ ጠቅላላ መንፈስ መረዳት የሚቻለው አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ህጋዊ እና ማኅበራዊ ተቀባይነት ባለው ሥርአት የሚፈጥሩትን ጥምረት የሚወክል ነው፡፡

ጋብቻ ያለው የሕግ ጥበቃ

ጋብቻ ህጋዊ እና ማኅበራዊ ውጤቶችን የሚያስከትል እንደመሆኑ ሀገራችን ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች፣ በእነዚህ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች መሠረት በተቃኘው የኢፌድሪ ህገ መንግሥት እንዲሁም በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ የቤተሰብ መመስረቻ መንገድ መሆኑ ታውቆ የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግሥት በአንቀጽ 34(3) ቤተሰብ የህብረተስብ የተፈጥሮ መሠረታዊ መነሻ እንደሆነ እና የህብረተሰብ ብሎም የመንግሥትን ጥበቃ የማግኘት መብት እንዳለው ደንግጓል፡፡ ጋብቻም የዚህ ቤተሰባዊ ግንኙነት ዋነኛ መመስረቻ ሥርአት እንደመሆኑ ጥበቃ የሚደረግለት ነው፡፡ በተጨማሪም በ1992 ዓ.ም የወጣው የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ 213/1992 የቤተሰብ ሕግ ከምስረታው ጀምሮ በሚኖረው ቆይታ እንዲሁም በሚፈርስበት ሂደት የሚደረግለትን ጥበቃ በዝርዝር የደነገገ ሕግ ነው፡፡

የጋብቻ አፈፃፀም ሥርአቶች

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 1 መሠረት ሶስት አይነት የጋብቻ አፈፃፀም ሥርአቶች አሉ፡፡ ይኸውም፡-

በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈፀም ጋብቻ

በተሻሻለው በቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 2 መሠረት አንድ ወንድ እና ሴት ጋብቻ ለመፈፀም ተስማምተው በክብር መዝገብ ሹም ፊት በመቅረብ ፈቃዳቸውን ሲገልፁ እና የክብር መዝገብ ሹሙም ይህንኑ ፈቃዳቸወን ሲቀበል ጋብቻ የሚፈፀምበት ሥርአት ነው፡፡

በሀይማኖት ሥርዐት መሠረት የሚፈፀም ጋብቻ

በተሻሻለው በቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 3 መሠረት አንድ ወንድ እና አንድ ሴት በሀይማኖታቸው ወይም ከሁለቱ በአንዳቸው ሀይማኖት መሠረት የሚፀና ጋብቻ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ሥርዐት ሲፈፅሙ ጋብቻ የሚፈፀምበት ሥርአት ነው፡፡ ይህ አማኞች በሚከተሉት እምነት ማለትም በእስልምና፣ በክርስትና እንዲሁም በሌሎች እምነቶች መሠረት የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡

በባህል ሥርዐት መሠረት የሚፈፀም ጋብቻ

በተሻሻለው በቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 4 መሠረት አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት በሚኖሩበት አካባቢ ባህል ወይም በሁለቱ ተጋቢዎች ወይም ከሁለቱ ተጋቢዎች በአንዳቸው ባህል መሠረት የሚፀና ጋብቻ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ሥርዐት ሲፈፅሙ ጋብቻ የሚፈፀምበት ሥርአት ነው፡፡

ጋብቻ ለመፈፀም መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች

ጋብቻው በየትኛውም አይነት አፈፃፀም ሥርአት የሚፈፀም ቢሆንም ከመፈፀሙ በፊት የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላትታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡

ፈቃድ

ጋብቻ በተጋቢዎች ነፃ እና ሙሉ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ ይህ ማለት ተጋቢዎች ወይም ከተጋቢዎቹ አንዱ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ጋብቻ እንዲፈፅሙ ሊገደዱ አይችሉም ማለት ነው፡፡ ይህ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 34(2) እና በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 6 የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ተጋቢዎች እራሳቸው ፈቃዳቸውን መግለፅ ያለባቸው ሲሆን በማስገደድ፣ በማሳሳት እና በመሳሰሉት መንገዶች ጋብቻው ቢፈፀም እንኳል ሊፀና አይችልም (የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 13 እና 14)፡፡

እድሜ

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 7 መሠረት ወንዱም ሆነ ሴቷ 18 ዓመት ካልሞላቸው ጋብቻ አይፈፀምም፡፡ ሆኖም ከባድ ምክንያት ባጋጠመ ጊዜ ተጋቢዎቹ ወይም ከተጋቢዎቹ የአንዳቸው መላጆች ወይም አሳዳሪ ጥያቄ ሲቀርብ ፍትሕ ሚኒስቴሩ ከመደበኛ የጋብቻ እድሜ ከ2 ዓመት ያልበለጠ ጊዜ ቀንሶ እንዲጋቡ በልዩ ሁኔታ ሊፈቅድ ይችላል፡፡

የሥጋ እና የጋብቻ ዝምድና

በተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 8 መሠረት በቀጥታ የሥጋ ዘመዳሞች ማለትም በወላጆችና በተወላጆች፣ ወደ ጎን በሚቀጠሩ የሥጋ ዘመዶች ማለትም በወንድምና እህት እንዲሁም የአክስትና የአጎት ዝምድና ባላቸው ሰዎች መካካል ጋብቻ ሊፈፀም አይችልም፡፡ በተመሳሳይ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 9 መሠረት በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች፣ ወደ ጎን በሚቆጠር የጋብቻ ዘመዳሞች ማለትም አንደኛው ተጋቢ ከሌላኛው ተጋቢ እህትና ወንድም ጋር ጋብቻ መፈፀም የተከለከለ ነው፡፡

የቀደም የፀና ጋብቻ መኖር

አስቀድሞ ጋብቻ የፈፀመ ሰው የቀደመ ጋብቻ ፀንቶ ባለበት ጊዜ ሌላ ጋብቻ እንዲፈፅም አይፈቀድለትም (የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 11)፡፡

የፍርድ ክልከላ መኖር

የሕግ ውጤት ያላቸውን ተግባራት እንዳያከናውን በፍርድ ቤት ክልከላ የተደረገበት ሰው ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቦ ካልፈቀደለት በስተቀር ጋብቻ መፈፀም አይችልም (የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 15)፡፡

የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች ጥሶ ጋብቻ ሊፈፅም ያሰበ ቢኖር በሚመለከተው ወገን ተቃውሞ የሚቀርብ ሲሆን ይኸውም ተቃውሞው

  • በእድሜ ምክንያት ሲሆን ወላጆች፣ ዐቃቤ ሕግ ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው
  • በሥጋ ወይም በጋብቻ ዝምድና ምክንያት ከሆነ የተጋቢዎቹ ወላጆች፣ 18 ዓመት የሞላቸው ወንድምና እህቶች ወይም ዐቃቤ ሕግ
  • በጋብቻ ላይ ጋብቻ ከሆነ ጋብቻ ከሚፈፅመው ሰው ጋር የቀደመ የፀና ጋብቻ ያለው ሰው ወይም ዐቃቤ ሕግ
  • በፍርድ ክልከላ የተደረገበት ከሆነ ደግሞ አሳዳሪው ወይም ዐቃቤ ሕግ

በተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 18 መሠረት ጋብቻው እንዳይፈፀም መቃወም ይችላሉ፡፡

ማጠቃለያ

ጋብቻ የማኅበረሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ የሚመሠረትበት ሥርአት ሲሆን ከአመሰራረቱ ጀምሮ የሕግ ጥበቃ የሚደረግለት እና አፈፃፀሙም በሕግ የሚመራ ነው፡፡ ስለሆነም ጋብቻ ህጉን ተከትሎ እንዲመሠረትና ጥሰቶችም ሲገኙ እነዲታረሙ በማድረግ ጤነኛ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ተምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ