የወንጀል ክስ የተመሰረተበት ተከሳሽ ባመነው ክስ ላይ ፍርድ ቤት ምስክሮችን የሚሰማበት የህግ አግባብ

ማውጫ

Share this Article

የወንጀል ክስ የተመሰረተበት ተከሳሽ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክስ ሲሰማ የእምነት ክህደት ቃሉን የሚጠየቅ ሲሆን ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ ሊያምን ወይም ሊክድ ይችላል፡፡ ተከሳሽ ፍርድ ቤት ቀርቦ ድርጊቱን ስለመፈፀም አለመፈፀሙ በግልፅ ችሎት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ በክሱ የተዘረዘረውን ስለመስራቱ ሙሉ በሙሉ ያመነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የተከሣሹን ቃል በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 134(1) መሠረት ቃሉን በመዝገብ አስፍሮ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንደሚሰጥ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በመሠረታዊነት በወንጀል የተከሰሰ ሰው የክሱን ድርጊት ሙሉ በሙሉ አምኖ የእምነት ቃሉን ከሰጠ ማስረጃ መሰማት ሳያስፈልግ ጥፋተኛ ይሆናል፡፡ ተከሣሽ ክሱ በችሎት ተነቦለት አምኗል የሚባለው ሙሉ በሙሉ የወንጀሉን የሀሳብ ክፍል፣ የድርጊቱን አፈፃፀም እና የተከሰሰበትን የወንጀል ድንጋጌ እንደ ክሱ አቀራረብ ወይም የክሱን ዝርዝር ፍሬ ቃል ያለምንም ተቃውሞ (ተአቅቦ ሳይኖር) አምኖ የእምነት ቃሉን የሰጠ እንደሆነ ነው፡፡ ሆኖም ተከሳሽ ቢያምንም ፍርድ ቤት ማስረጃ እንዲሰማ የሚያዝበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል በሥነ ሥርአት ህጉ ተደንግጓል፡፡

ይኸውም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርአት ሕግ አንቀጽ 134(2) መሠረት ፍርድ ቤቱ ማስረጃ መሰማቱን *አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው* በዐቃቤ ሕግ በኩል ለክሱ የሚደግፍ ማስረጃ እንዲያቀርብ ለማዘዝ እና ተከሳሹም መከላከያ ማስረጃ ካለው እንዲያቀርብ ሊያዥ የሚችል ሲሆን

ተከሳሽ አምኖ የእምነት ቃል ከሰጠ በኋላ ፍርድ ቤቱ ክሱን መስማት በሚቀጥልበት ጊዜ ጥፋተኛ አይደለሁም የማለት ቃል መመዝገብ የሚገባው ሆኖ ካገኘው በክህደት ተመዝግቦ ማስረጃ እንደሚሰማ በሥነ ሥርአት ህጉ አንቀጽ 135 ተደንግጓል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ