በንብረት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን አስምልክቶ በወንጀል ህጉ ከተደነገጉ በንብረት ላይ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መካከል የመሸሸግ ወንጀል አንዱ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የመሸሸግ ወንጀልን ምንነት እና የሚያስከትለውን ተጠያቂነት እንመለከታለን፡፡
የመሸሸግ ወንጀል ምንነት
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 682 መሠረት መሸሸግ ማለት ዕቃው የተገኘው በአንድ ንብረት ላይ በተፈፀመ ወንጀል ምክንያት መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባ ይህንኑ ዕቃ በመግዛትም ሆነ በተውሶ፣ በስጦታ፣ በመያዣነት መቀበል ወይም በማናቸውም ይህን በመሳሰለ አኳኋን መውሰድ፣ መገልገል፣ ማስቀመጥ ወይም መደበቅ፣ አሳልፎ መሸጥ ወይም በመሸጥና በመለወጥ ስምምነት ውስጥ አገናኝ በመሆን መርዳት እንዲሁም የወንጀል ተግባር ባስገኘው ፍሬ የመጣ መሆኑን እያወቁ በዚሁ በወንጀል ድርጊት በተገኘ ዕቃ ምትክ በልዋጭ የተገኘውን ወይም በሽያጭ ዋጋ የተገዛውን ሌላ አይነት ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ መቀበል ነው፡፡
በዚህ መሠረት የመሸሸግ ወንጀል ተፈፅሟል ለማለት
- ተሸሽጎ የተገኘው ዕቃ በአንድ ንብረት ላይ በተፈፀመ ወንጀል ምክንያት የተገኘ ወይም የወንጀሉ ተግባር ባስገኘው ፍሬ የመጣ መሆን
- ሸሻጊው ዕቃው በወንጀል ምክንያት መገኘቱን ማወቅ ወይም መገመት ሲገባው በቸልተኝነት ወንጀሉን የፈፀመ መሆን
- በወንጀል ተግባር የተገኘን ዕቃ የገዛ፣ የተቀበለ፣ የወሰደ፣ የተገለገለ ወይም በመሰል ድርጊት ውስጥ የተገኘ መሆን አለበት፡፡
የመሸሸግ ወንጀል የሕግ ተጠያቂነት
ከላይ በተገለፀው ሁኔታ የመሸሸግ ወንጀል አስቦ የፈፀመ ማንም ሰው በቀላል እስራት ወይም ከባድ በሆነ ጊዜ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡ ድርጊቱ በቸልተኝነት የተፈፀመ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡
ከባድ መሸሸግ
የመሸሸግ ወንጀል የተፈፀመው
- በሰዎች ወይም በንብረት ላይ ወንጀል ለመፈፀም የተቋቋመ ቡድን አባልነት እንደሆነ
- ወንጀል ፈፃሚው የተሰጠውን የሥራ ወይም የንግድ ፍቃድ በወንጀል የተገኘን ንብረት ለመሸሸግ ተገልግሎበት እንደሆነ
- ወንጀል ፈፃሚው የሸሸገው ንብረት የውንብድና፣ የዘረፋ፣ የባህር ውንብድና፣ የቅሚያ፣ የማስፈራራት ፍሬ መሆኑን ወይም ዕቃው የተገኘው ከመከላከያ ሠራዊት ንብረት ወይም በጠቅላላው ከመንግሥት ሀብት ውስጥ መሆኑን እያወቀ እንደሆነ
ወንጀሉ ከባድ የመሸሸግ ወንጀል የሚሆን ሲሆን ፈፃሚውም አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና እስከ ብር ሀያ ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ህብረተሰቡ በማወቅም ወይም በቸልተኝነት በእንድ የወንጀል ድርጊት አማካኝነት የተገኘን ንብረት መግዛት፣ መዋስ፣ በስጦታ ወይም በመያዣነት መቀበል ወዘተ በወንጀል የሚያስቀጣ መሆኑን በመገንዘብ ዕቃዎችን ሲገዛም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ሲቀበል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ