የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ መግለጫ

ማውጫ

Share this Article

ወንጀል ለተለያየ ዓላማ ሊፈጸም የሚችል ቢሆንም ገንዘብ የሚያስገኙ ወንጀሎች የሚፈጸሙት ፈፃሚዎቹ በዋናነት ከወንጀል ድርጊታቸው የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል የሙስና ወንጀሎች በተለይም ጉቦ መቀበል ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፥ የተከለከሉ ዕፆችን ማዘዋወር፣ የሐሰት ገንዘብ ማተም፣ ሕገ ወጥ ሀዋላ፣ የታክስ እና የኮንትሮባንድ ወንጀሎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህ እና መሰል ወንጀሎች በባህሪያቸው ለወንጀል ፈጻሚዎች ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኙ ሲሆኑ በሀገር ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የሚያሳርፉት አሉታዊ ተጽዕኖ ደግሞ በተቃራኒው እጅግ አደገኛና ውስብስብ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ወንጀልን ከመከላከል እና አጥፊዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ከማስተላለፍ አንፃር በወንጀሉ የተሳተፉ ሰዎችን በወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ በተጨማሪ የወንጀል ፍሬ ወይም ለወንጀል መፈጸሚያነት የዋለውን ንብረት መውረስ ተገቢ ነው፡፡

በወንጀል የተገኘ ሃብትን የማስመለስ ሂደት የተለያዩ ደረጃዎችን የሚያልፍ ሲሆን በዚህም የወንጀል ምርመራን መሠረት በማድረግ ንብረት የመለየት፣ ንብረት የማገድ፣ ንብረት የመያዝ እና በአስተዳደር ስር እንዲቆይ የማድረግ እንዲሁም ንብረት የመውረስ ተግባራት ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡

ይህንን ሂደት በአግባቡ ለመፈጸም ወጥና ራሱን የቻለ የንብረት ማስመለስና አስተዳደር ሕግ ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ራሱን የቻለ በወንጀል የተገኘ ሃብትን የሚመለከት ሕግ ባይኖራትም በተለያዩ አዋጆች ስር በወንጀል የተገኘ ሃብት ማስመለስን በተመለከተ ተፈጻሚነት ያላቸውን ድንጋጌዎች ተካተው እናገኛለን፡፡ በእነኚህ አዋጆች ውስጥ ተካተው የሚገኙት የንብረት ማስመለስ ድንጋጌዎችም ተበታትነው ከመገኘታቸው ባሻገር ተፈፃሚነታቸውም በአዋጆቹ ስር ለተደነገጉት የወንጀል አይነቶች ብቻ እንደመሆኑ መጠን ወጥ የሆነ የንብረት ማስመለስ እና ማስተዳደር ሕግ አለመኖሩ በአዋጆቹ ባልተካተቱ እና ከፍተኛ የሆነ የንብረት ጥቅም ወይም ጉዳት በሚያስከትሉ ወንጀሎች ላይ የንብረት ማስመለስ ሂደት መሠረታዊ የሆነ የሕግ እና አፈፃፀም ክፍተት እንዲኖር አድርጓል፡፡

በመሆኑም እነዚህን በተለያዩ ሕጎች ውስጥ ተበታትነው ያሉትን የንብረት ማስመለስ እና አስተዳደር ድንጋጌዎች በአንድ ወጥ ሕግ ውስጥ በማካተት ለአፈጻጸም ምቹ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሁኔታ በወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ መርሆዎች መካከል አንዱ የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችንና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመለየት፣ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለማስተዳደር ወይም ለመውረስ የሚያስችል ግልጽና ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንደሚሆን እንዲሁም በዚሁ ፖሊሲ ተራ ቁጥር 3.16.3 ላይ ስለንብረት ማገድና መውረስ የተካተተ በመሆኑ በዚህ የፖሊሲ አቅጣጫ መሠረት አንድ ወጥ የሆነ ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ አዋጅ ተዘጋጅቷል።

የዚህ አዋጅ ዋነኛ ዓላማ የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችንና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል ግልጽና ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ በማበጀት ማንም ሰው ከሕገ-ወጥ ድርጊት ማናቸውንም አይነት የኢኮኖሚ ጥቅም እንዳያገኝ ለማድረግ እና የንብረት ማስመለስ ሕግ ወንጀልን በመከላከል ሂደት ያለውን ከፍተኛ ሚና ለማሳካት የሚያስችል የንብረት ማስመለስና ማስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ለዚህም ሲባል በአሁኑ ወቅት ከወንጀል ጋር ግንኙነት ያለውን ምንጩ ያልተወቀ ንብረትን ማስመለስ እንዲቻል እና በተለያዩ ሕጎች ውስጥ ተበታትነውና ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ሆነው ያሉትን የንብረት ማስመለስ እና መውረስ መሠረታዊ ድንጋጌዎች እና የሥነ-ሥርዓት ሂደቶች የንብረት ማስመለስና መውረስ ሂደት ውስጥ ያሉትን ልዩ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሁሉም አይነት ወንጀሎች የሚያገለግል አንድ ወጥ የሆነ ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት በንብረት ማስመለስና መውረስ ሂደት ውስጥም ሆነ ንብረቱ ከተወረሰ በኋላ የንብረቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስጠበቅ የመንግሥትና የሃገሪቱን ጥቅም ማስከበር ማዕከል በማድረግ የተዘጋጀ ሕግ ነው።

ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን እና በወንጀል የተገኘ ሀብትን ከማስመለስ ጋር በተያያዘ ሰፋ ያለ ጽንሰ-ሐሳባዊ ጉዳዮችን እና የሀገራትን ልምድ በአግባቡ ለመረዳት ከዚህ በታች የተመላከቱተን ጽሁፎች ያግዛሉ።

ተጨማሪ ማጣቀሻዎች

• Dornbierer, A., 2021. Illicit Enrichment: A Guide to Laws Targeting Unexplained Wealth. Basel: Basel Institute on Governance. Available at: illicitenrichment.baselgovernance.org

• Brun, J. et al, 2021. Asset Recovery Handbook: A Guide for Practitioners, Second edition, https://star.worldbank.org/…/asset-recovery-handbook…