የወንጀል ሕግ ዓላማ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግሥት፣ የሕዝቦቹን፣ የነዋሪዎቹን፣ ሰላም፣ ደኅንነት፣ ሥርአት መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው፡፡ የወንጀል ሕግ ግብ ደግሞ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል፣ ስለወንጀሎችና ቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ ማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እርምጃ እንዲወስድባቸው ማድረግ ነው፡፡
አንድ የወንጀል ድርጊት በተፈፀመ ጊዜ በሕግ መሠረት እና የሥነ ሥርዓት ሂደቱን ጠብቆ የወንጀል ምርመራ ከተከናወነ በኋላ በገለልተኛ ፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎና የከሳሽና ተከሳሽ ማስረጃ ተሰምቶ ተከሳሹ ወንጀል መፈፀሙ ሲረጋገጥ የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ሁኔታዎች ታሳቢ ተደርገው ተመጣጣኝና አስፈላጊ በሕግ የተፈቀደ ቅጣት ይጣልበታል፡፡ ቅጣቱ እስራት በሚሆንበት ጊዜ በማረሚያ ቤት ገብቶ ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆና መሠረታዊ ፍላጎቶቹ ተሟልተው እንዲታረም ይጠበቃል፡፡ በዚህ የእስራት ቅጣት አፈፃፀም ወቅት በወንጀል ህጋችን እና በፍርድ ትእዛዙ የተመለከተው የእስራት ጊዜው ከማብቃቱ በፊት ታራሚው ሊፈታ ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ አመክሮ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የአመክሮን ምንነትና ተያያዥ ጉዳዮች በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
የአመክሮ ምንነት
አመክሮ ማለት አንድ ታራሚ ከተፈረደበት የእስር ጊዜ ሁለት ሶስተኛውን በመልካም ፀባይ ካሳለፈ ቀሪውን የእስር ጊዜ ከማረሚያ ቤት ውጪ ሆኖ በመልካም ጠባይ ሊያሳልፍ ይችላል ተብሎ ሲታመን የሚፈታበት ሥርአት ነው፡፡ አመክሮ አንድ ታራሚ ወደ ማረሚያ ቤት በሚገባበት ጊዜ በቅበላ ወቅት የተወሰነበት ቅጣት ከመፈፀሙ በፊት ቀደም ብሎ በአመክሮ ሊለቀቅ የሚችል መሆኑን እንዲሁም የአመክሮ እድል ለማግኘት ምን አይነት ግዴታዎችን መፈፀም እንደሚጠበቅበት እንዲገለፅለት ሕግ ያስገድዳል፡፡ (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 203)
በአመክሮ ለመለቀቅ ሊሟሉ የሚገባቸው ሁኔታዎች
በአመክሮ ለመለቀቅ የሚከተሉት ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባል፡፡
- ከተወሰነበት እስራት ጊዜ ከሶስት እጅ ሁለቱን መፈፀም ወይም የተወሰነበት የእድሜ ልክ እስራት ፍርድ ከሆነ ሀያ ዓመት መፈፀም፣
- የተወሰነበትን ነጻነት የሚያሳጣ ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ በመፈፀም ላይ እያለ በሥራውና በጠባዩ የተረጋገጠ መሻሻል ማሳየት፣
- ለደረሰው ጉዳት በተቻለ መጠን በፍርድ የተወሰነ ወይም ከተበዳይ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ካሳ ለመክፈሉ ማረጋገጫ ማቅረብ፣
- አመሉና ጠባዩ በመልካም አኗኗር ለመኖር እንደሚያስችለው እና በአመክሮ መፈታቱ መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ ሲታመን፣
- ደጋጋሚ ወንጀለኛ አለመሆን ማለትም አስቀድሞ ሌላ የወንጀል ሪከርድ ከሌለበት ናቸው፡፡ (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 202/2/)
አመክሮ የሚፈቅደው በወንጀል ህጉ መሠረት ቅጣቱን የጣለበት ፍርድ ቤት ነው፡፡ የአመክሮ ጊዜው ሲደርስ ጥያቄውን በማረሚያ ቤት በኩል ወይም በጠበቃው ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡ ማረሚያ ቤቱም የታሰረበትን ጊዜ መጠን እና በቆይታው የነበረውን መልካም ጠባይ መሠረት አድርጎ በአመክሮ ቢፈታ የሚደግፍ መሆኑን ወይም የሚቃወም መሆኑን አስተያየት እንዲያቀርብ ይጠበቃል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከላይ የተመለከቱት ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተዋል ብሎ ካመነ ታራሚው በአመክሮ እንዲፈታ በመፍቀድ አመክሮው የሚቆይበትን ጊዜ አብሮ ይወሰናል፡፡ ታራሚው ተፈቶ መልካም ጠባዩ ወይም ሕግ አክብሮ መኖሩ የሚፈተንበት ጊዜ መጠን የሚወሰነው እስከ ቀሪው የእስር ጊዜ ድረስ ሆኖ በማንኛውም ሁኔታ ከሁለት ዓመት ሊያንስ፣ ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ በስተቀር ከአምስት ዓመት ሊበልጥ አይችልም፡፡ የእድሜ ልክ ፍርደኛ ከሆነ የፈተና ጊዜው ከአምስት ዓመት ሊያንስ ከሰባት ዓመት ሊበልጥ አይችልም፡፡
አመክሮ የተቀጪው ጠባይ ማሻሻያና ወደ ደንበኛው ማኅበራዊ ኑሮ መመለሻ ሆኖ የሚቆጠር ሲሆን መፈታቱ ተፈላጊውን ውጤት የሚያስገኝ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ካላመነበት በቀር ሊፈቀድ አይችልም፡፡
ተቀጪው አመክሮ ተፈቅዶለት ከተፈታ በኋላ ሊከተል የሚገባውን የጠባይ አመራርና ቁጥጥር ደንብ (የወንጀል ሕግ አንቀጽ198) ፍርድ ቤቱ ሊወስን ይችላል፡፡
እነዚህም፡-
- በአንድ የጥበብ መስክ ሙያ መማር፣
- በተወሰነ ስፍራ መቀመጥ፣ መሥራት ወይም መኖር ግዴታ፣
- ከአንዳንድ ሰዎች ጋር እንዳይገናኝ መከልከል፣
- በአንዳንድ በተወሰኑ ስፍራዎች ከመድረስ መታገድ፣
- አልኮል ከመጠጣት መከልከል፣
- በስራ ከሚያገኘው ገቢ በሙሉ ወይም በከፊል ለቤተሰቡ ወይም ለሞግዚቱ ወይም ለአሳዳሪው መስጠት፣
- አስፈላጊ ህክምና መውሰድ፣
- ይህን መሰል ወይም ሌላ አስፈላጊ የአመራር ደንብ ሊሆን ይችላል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተለቀቀው ጥፋተኛ ሊከተላቸው የሚገቡ የጠባይ አመራር ደንቦችን ሲወስን እድሜን፣ ጠባይን፣ ከተፈታ በኋላ የሚኖርበትን የወንጀል መጋለጥ እድል፣ የቤተሰብን አስተማማኝነት፣ የሙያ ስራውን፣ የማኅበራዊ ኑሮ ሁኔታን መሠረት በማድረግ ይሆናል፡፡ የሚወሰኑ የመልካም ጠባይ አመራር ደንቦች የተቀጪውን አቅም፣ ፍላጎት፣ የነገሩን ሁኔታ፣ ጥፋቱ ያደረሰው ጉዳት መሠረት በማድረግ የጥፋተኛውን ጠባይ በማሻሻል የታሰበው ዓላማ ለማሳካት የሚያስችሉ መሆን አለባቸው፡፡ አዲስ ሁኔታ ሲያጋጥም ወይም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በተቀጪው በራሱ አመልካችነት፣ በሞግዚቱ፣ በዓቃቤ ሕግ፣ በባልደረባው ወይም በዋሱ ጠያቂነት ፍርድ ቤቱ ትእዛዙን ሊለወጥ ወይ ሊያሻሽል ይችላል፡፡
የመልካም ጠባይ አመራር ደንቡን የሚከታተልና የሚቆጣጠር በሕግ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ለጊዜው የሌለ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ይህን መሰል ትእዛዝ በሚሰጥበት ወቅት የሚከታተልና የሚያስፈፅም አካል ለይቶ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡
የአመክሮ ውጤት
ለአመክሮ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ በፍርድ ቤት አመክሮ የተፈቀደለት ጥፋተኛ በአመክሮ ከተፈታ በኋላ በተቀመጠለት የፈተና ጊዜ በመልካም ጠባይ ከተመራ እና ሌላ ወንጀል ሳይፈፅም ካጠናቀቀ ቀሪውን የእስር ጊዜ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 206(3) መሠረት እስከወዲያኛው ቀሪ ይሆንለታል፡፡
የአመክሮ መሻር
የአመክሮ ወይም የፈተና ሁኔታ ሲጣስ ማለትም ፍርድ ቤት እንዲያደርግ ያዘዘውን ከላይ ከተመለከቱት የጠባይ አመራር ደንብ ውስጥ አንዱን ከጣሰ፣ ከቁጥጥር ለማምለጥ ከሞከረ፣ በቸልታ ወንጀል ከፈፀመ፣ የተጣለበትን እምነት ካጎደለ ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፡፡ በተጨማሪም ተጨማሪ ወይም አዲስ ጠባይ አመራር ደንብ ሊወስንበት ወይም የአመክሮ ፈተና ጊዜውን ሊያራዝመው ይችላል፡፡ ከዚህ ባለመታረም በጥሰቱ ከቀጠለበት ወይም ከደገመ ወይም አስቦ አዲስ ወንጀል ካደረገ አዲስ በፈፀመው ወንጀል መጠየቁ እንደተጠበቀ ሆኖ የተፈቀደለት አመክሮ ይሻራል፡፡ ቀሪውን የእስር ጊዜም በማረሚያ ቤት እንዲፈፅም ይደረጋል፡፡
በአጠቃላይ ታራሚዎች የአመክሮ እድል ተጠቃሚ ለመሆን የአመክሮን ምንነት መረዳት፣ በማረሚያ ቤት በመልካም ጠባይ መመራት፣ ከላይ የተመለከቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት፣ በአመክሮ ከተፈቱም በኋላ በመልካም ጠባይ መመራትና ድጋሚ ሌላ ወንጀል አለመፈፀም እንደሚያስፈልግ ተረድተው የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ