በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ በዝምድና ምክንያት የተከለከሉ ጋብቻዎች

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ቤተሰብ የህብረተሰብ መሠረት ነው፡፡ ቤተሰብ የሚመሠረትባቸው ሁኔታዎች በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ መንግሥት እና ቤተሰብ ህጉ ውስጥ ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ መሠረት ህጋዊ እውቅና ያላቸው ሁለት አይነት የቤተሰብ መመስረቻ መንገዶች አሉ፡፡ እነሱም ጋብቻ እና ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ናቸው፡፡

ጋብቻ ለመፈፀም መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች በቤተሰብ ህጉ ተደንግገዋል፡፡ ይኸውም ጋብቻ ለመፈፀም የተጋቢዎች በሕግ የተቀመጠ ዝቅተኛ እድሜ፣ የተጋቢዎች ፍቃድ፣ የተጋቢዎች የዝምድና ደረጃ መሟላት ካለባቸው መስፈርቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቤተሰብ ህጉ እንደተደነገገው ጋብቻ ለመፈፀም መሟላት ካለባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ በሆነው የዝምድና ደረጃ ምክንያት ዘመድ በመሆናቸው እንዳይጋቡ ህጉ የከለከላቸው ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የዝምድናን ምንነት፣ የጋብቻ ክልከላ የሚያስከትሉ የዝምድና አይነቶች እና በዝምድና ምክንያት የተከለከለ ጋብቻ መፈፀም የሚያስከትለውን ውጤት እንዳስሳለን፡፡

የዝምድና ምንነት

በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 8 እና 9 ስር እንደተደነገገው ሁለት የዝምድና አይነቶች አሉ፡፡ እነሱም የስጋ እና የጋብቻ ዝምድና ናቸው፡፡

የስጋ ዝምድና

  • ቀጥታ የስጋ ዘመዳሞች (በወላጅና በተወላጆች/አባት እና ልጅ/እናት እና ልጅ/አያት እና የልጅ ልጅ) እና
  • ወደ ጎን በሚቆጠሩ የሥጋ ዝምድና፤ አንድ ወንድ ከእህቱ ወይም ከአክስቱ እንዲሁም አንዲት ሴት ከወንድሟ ወይም ከአጎቷ ጋር ዝምድና አላቸው፡፡

የጋብቻ ዝምድና

  • ቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች (ባል ከሚስቱ እናትና፤ ሚስት ከባል አባት)
  • ወደ ጎን በሚቆጠር የጋብቻ ዝምድና፣ ባል ከሚስቱ እህት ወይም ሚስት ከባሏ ወንድም ጋር ዘመድ እንደሆኑ ከቤተሰብ ህጉ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡

ጋብቻን የሚከለክሉ የዝምድና አይነቶች

የቤተሰብ ህጉ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት በዝምድና ምክንያት ጋብቻ መፈፀም የማይፈቀድላቸውን ዘመዳሞች ዝርዝር አስቀምጧል፡፡ እነሱም

  • በስጋ ዝምድና፡- በቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 8 መሠረት ቀጥታ የስጋ ዘመዳሞች (በወላጅና በተወላጆች/አባት እና ልጅ/እናት እና ልጅ/አያት እና ልጅ)፤ ወደ ጎን በሚቆጠሩ የሥጋ ዝምድና፤ አንድ ወንድ ከእህቱ ወይም ከአክስቱ እንዲሁም አንዲት ሴት ከወንድሟ ወይም ከአጎቷ ጋር ጋብቻ መፈፀም የተከለከለ ነው፡፡
  • በጋብቻ ዝምድና፡- በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 9 መሠረት ቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች (ባል ከሚስቱ እናት፤ ሚስት ከባል አባት)፣ ወደ ጎን በሚቆጠር የጋብቻ ዝምድና፣ ባል ከሚስቱ እህት ወይም ሚስት ከባሏ ወንድም ጋር ጋብቻ መፈፀም ክልክል ነው፡፡

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ይህ ክልከላ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ በመኖር ላይም ተፈፃሚ መሆኑን ነው፡፡ በአንቀጽ 98 መሠረት ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት መኖር አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት በሕግ በሚፀና ጋብቻ ሳይፈፅሙ በትዳር መልክ አብሮ መኖር ነው፡፡ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት መኖር በወንዱ እና በሴቲቱ የሥጋ ዘመዶች መካከል እንዲሁም በሴቲቱ እና በወንድየው የሥጋ ዘመዶች መካከል የጋብቻ ዝምድና አይፈጥርም፡፡ ሆኖም ልክ የጋብቻ ዝምድና ባለ ጊዜ የተቀመጡ የጋብቻ ክልከላዎች ግን ተፈፃሚ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ልክ እንደጋብቻ ሁሉ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት የሚኖሩ እንኳን ቢሆን ከላይ የተጠቀሰው የጋብቻ ዝምድና ክልከላ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

በዝምድና ምክንያት ጋብቻ እንዳይፈፀም ስለመቃወም

በህጉ ክልከላ የተደረገባቸው ዘመዳሞች መካከል ጋብቻ ሊፈፀም ከሆነ የተጋቢዎቹ ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆች፣ 18 ዓመት የሞላቸው ወንድሞች ወይም እህቶች ወይም ዐቃቤ ሕግ ጋብቻው እንዳይፈፀም መቃወም ይችላሉ፡፡ ይህ መቃወሚያ በጽሑፍ ሆኖ እጅግ ቢዘገይ ጋብቻው ከሚፈፀምበት 15 ቀናት በፊት ለጋብቻ አስፈፃሚው ባለሥልጣን መቅረብ አለበት፡፡ ጋብቻ የሚስፈፅመው ባለሥልጣንም የተጋቢዎቹን አስተያየት ከተቀበለ በኋላ በ5 ቀናት ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ የቀረበውን ተቃውሞ የተቀበለ ከሆነ ለውሳኔው ምክንያት ያደረገውን ጉዳይ ለተጋቢዎቹ በማሳወቅ ጋብቻው እንዳይፈፀም ማድረግ ያለበት ሲሆን ተጋቢዎች በውሳኔው ላይ ለፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ ይችላሉ፡፡

በዝምድና ምክንያት የተከለከለ ጋብቻ መፈፀም የሚያስከትለው ውጤት

በሥጋ ወይም በጋብቻ ዝምድና ምክንያት ጋብቻ እንዳይፈፀም የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ የተፈፀመ ጋብቻ በማንኛውን ባለጉዳይ ወይም በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ እንዲፈርስ እንደሚደረግ የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 32 ስር ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 647 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው በሕግ የተከለከለውን ጋብቻ አስቦ የፈፀመ ወይም ያስፈፀመ ወይም ለዚህ አይነቱ ጋብቻ ምስክር የሆነ ሰው ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመው በቸልተኝነት የሆነ እንደሆነ ደግሞ ከሦስት ወር በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡

በአጠቃላይ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ በዝምድና ምክንያት የተከለከሉ ጋብቻዎች የተደነገጉ በመሆኑ ጋብቻ ፈፃሚዎችም ሆኑ ጋብቻ አስፈፃሚዎች ጋብቻ ለመፈፀም መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች መሟላታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህትርና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ