ዓለም አቀፍ የ16ቱ የፀረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ ቀናት ከህዳር 16 እስከ ታህሳስ 1 ቀን ይከበራል

ማውጫ

Share this Article

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ17ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ ”ሴትን አከብራለሁ ጥቃቷንም እከላከላለሁ” በሚል መሪ ቃል” ከህዳር 16 እስከ ታህሳስ 1ቀን 2015 ዓ.ም ይከበራል፡፡

የ16ቱ ቀናት የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተደራጀ መልኩ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሲሆን የትኛውም ዓይነት በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ማውገዝ እና መከላከልን ዓላማ ያደረገ እንቅስቃሴ ነው፡፡

በእነዚህ ቀናት ጾታዊ ጥቃትን ለማስወገድ፡-

  • በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጸረ-ጾታዊ ጥቃት ስራዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል፣
  • በሀገር እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጾታዊ ጥቃትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ግልጽ የሆኑ መለያዎች ይቀመጣሉ፣
  • በዓለም አቀፍ እና በአገር አቀፍ ደረጃ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥያቄ መሆኑን ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች ይከናወናሉ፡፡
  • ወንዶች ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የመከላከል ስራዎች ላይ አጋር እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡
  • መንግስታት የኃይል ጥቃትን ለማስወገድ የገቡትን ቃል እንዲጠብቁ ጫና የመፍጠር ስራዎች ይከናወናሉ፡፡
  • በየአካባቢው የሚደረጉ የጸረ-ጾታ ጥቃት ትግሎችን ማጠናከር ስራዎች ይሰራሉ፡፡
  • የጾታ ጥቃትን ለማስወገድ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ቅንጅት የሚያጎለብቱ ውይይቶች እና ተከታታይ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ አዳዲስ የጸረ ጾታ ጥቃት ማስፈፀሚያ ስልቶች በመቀየስ ቀናቶቹ በተለያዩ ፕሮግራሞች ይከበራሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚደርሱትን የጾታዊ ጥቃት ድርጊቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት በመንግሥትና መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች አበረታች ናቸው፡፡ የ16ቱ የጸረ ጾታ ጥቃት ዘመቻ ቀናት በምናከብርበት ወቅት ከነዚህ በጎ እርምጃዎች የምንማርበትና ሥራዎቻችንን የምናወድስበት እንዲሁም መንግሥት የተቀናጀና የተጠናከረ እርምጃ እንዲወስድ፤ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትም እንዲሁ ግንዛቤ በማስጨበጥ ለተጎጂዎች የሕግ፣ የማኅበራዊና የስነ-ልቦናዊ ድጋፍ እና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት፤ ማህበረሰቡም ጥቃትን በማውገዝና የፍትሕ አካላትን በመተባባር ከመንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ለጥቃት የሚዳርጉ ሁኔታዎችና የተዛቡ አመለካከቶችን በመለወጥ ረገድ ሥራዎቻችንን በጋራ አጠናክረን መቀጠል ይጠበቅብናል፡፡

”ሴትን እናክብር፤ የሚደርሰባትን ጥቃትም እንከላከል”

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር