የሕግ ምንነት
ሕግ የሚለው ቃል በማህበረሰቡ ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ቃል ነው፡፡ በተለይ ሕግ አስገዳጅ መሆኑን የሚረዳው ለመሆኑ ቀደም ባለው ጊዜ በየዕለት ኑሮ ፀብ ሲገጥመው እንኳን “በሕግ አምላክ” ብሎ ፀብ የማብረድ ልምድ የነበረው መሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ሆኖም ማህበረሰቡ ሕግን የሚረዳው በተለምዶአዊው አረዳድ እንጂ የዘርፉ ባለሞያዎች በሚረዱበት መልኩ አይደለም፡፡
በመሰረቱ ሕግ ለሚለው ቃል ትርጓሜ መስጠት ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ ምሁራን ቃሉን በተለያየ መንገድ የሚገልፁት በመሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም የቃሉ ፍቺ ሊደረስባቸው በሚፈለጉት የተለያዩ ዓላማዎች ምክንያት ሊለያይ ይችላል።
ለሕግ ቃላት ትርጉም በመስጠት የሚታወቀው ብላክስ ሎው የሕግ መዝገበ ቃላት በተሻሻለው ስድስተኛ እትሙ (Black’s Law Dictionary, 6th ed.,) ለሕግ ትርጉም ሲሰጥ law is “a body of rules of action or conduct prescribed by controlling authority, and having binding legal force, which must be obeyed and followed by citizens subject to sanctions or legal consequence is a law.” ወደ አማርኛ በግርድፉ ሲመለስ ሥልጣን ባለው አካል የተደነገገ የተግባር ወይም የምግባር ደንብ እና አስገዳጅ የሕግ ኃይል ያለው አካል ነው። ይህንንም ዜጎች ሊታዘዙት እና ሊከተሉት የሚገባ ሆኖ ማዕቀብ ወይም ህጋዊ ውጤት የሚጥል ሕግ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
በመሆኑም የአንድ ሀገር ሕግ፡- ሰላምን ለማስጠበቅ፣ ነባራዊ ሁኔታውን ለማስጠበቅ (maintain the status quo)፣ የግለሰብ መብቶችን ለማስጠበቅ፣ አናሳዎችን ከብዙኃን ለመከላከል ( protect minorities against majorities)፣ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን( promote social justice) እና ሥርዓት ያለው ማኅበራዊ ለውጥ እንዲኖር ለማድረግ( provide for orderly social change) ያገለግላል።
የሕግ መሠረታዊ ባህሪያት
የህጎችን የተለመዱ ባህሪያት እና ተፈጥሮ መፈተሽ የሕግ ጽንሰ-ሀሳብን ለመገንዘብ የሚረዳ ሲሆን ከእነዚህ ባህሪያት እና ተፈጥሮዎች መካከል እንደ ወሰኝ ወይም አስፈላጊ የሚታሰቡት አጠቃላይነት(ሕግ በሁሉም ሰው ላይ በተመሳሳይነት (uniformity) እና እኩልነትን (Equality) የሚፈፀም መሆኑ)፣ መደበኛነት (ሕግ ማኅበራዊ ባህሪን በመፍቀድ፣ በማዘዝ ወይም በመከልከል ልማዶችን የሚፈጥር መሆኑ) እና ማዕቀብ ወይም ቅጣትን (ሕግን ያላከበረ ቅጣት የሚጠብቀው መሆኑን) ያካትታሉ፡፡
ሕግን አለማወቅ እና የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ
በወንጀልም ሆነ በፍትሐ ብሄር ጉዳይ ህጎቹ ሥልጣን ባለው የሕግ አውጪ አካል ወጥተው ከፀደቁበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ዜጎች የህጎቹን መኖር ወይም መውጣት የማወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይኸውም ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም የሚለው የሕግ መርህ በላቲን Ignorantia juris non excusat ወይም በእንግሊዘኛ “ignorance of the law excuses not” ከሮማውያን ሕግ የተወሰደ ሲሆን ሕግን የማያውቅ ሰው ይዘቱን ባለማወቅ ብቻ ህጉን በመተላለፍ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ እንደማይችል የሚገልጽ የሕግ መርህ ነው። እንዲሁም የሕግ ስህተት (mistake of law) ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ተፈጻሚነት ያለው ሕግ እንዴት እንደሚተገበር የሚይዙትን የአረዳድ ስህተቶችን የሚያመለክት የሕግ መርህ ነው። ‘ሕግን አለማወቅ’ እና ‘የሕግ ስህተት’ የሚሉት ቃላቶች በህጋዊ እይታ ውስጥ ተመሳሳይ ትርጉም የማይሰጡ ሲሆን አለማወቅ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አጠቃላይ የእውቀት ያለመኖርን ያመለክታል። ማሳሳት ግን እውቀትን ተቀብሎ ወይም እውቀት እንዳለ አምኖ ነገር ግን የተሳሳተ መደምደሚያን ላይ መድረስን ያሳያል። ይሁንና ሕግን አለማወቅም ሆነ የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት እንደማያድን እንደ አንድ የሕግ መርህ ይወሰዳል፡፡
ሕግን አለማወቅ እና የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ መርህ ምክንያት (rationale for “ignorance of the law excuses not” principle)
በመሠረቱ አንድ ሰው ሕግን ከጣሰ ህጉን ስለመጣሱ ምንም እውቀት ባይኖረውም ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ሰዎች ህጉን አላውቀውም በማለት ድርጊታቸውን ሊከላከሉ እንደማይችሉ ያመለክታል፡፡ የዚህ ሕግ መርህ ምክንያት( rationale) አለማወቅ ሰበብ ቢሆን ኖሮ ምንም እንኳን ያ ሰው ህጉ መኖሩን ቢያውቅም በወንጀል ሕግ ወይም በፍትሐ ብሄር ጉዳይ ቢከሰስ ህጉን አላወኩም በማለት ከተጠያቂነት ማምለጫ እንዳይሆን በሚል ነው፡፡ በመሆኑም ከመርህ በስተጀርባ ያለው ምክንያት አለማወቅ ሰበብ ከሆነ ማንኛውም በወንጀል ወይም በፍትሐ ብሄር የተከሰሰ ሰው ተጠያቂነትን ለማስወገድ አላዋቂ ነኝ ሊል ይችላል የሚል ነው። ስለዚህ ህጉ የቱንም ያህል አጭር ጊዜ ቢቆይ ሁሉም ህጎች በስልጣኑ ውስጥ ላለ ለእያንዳንዱ ሰው ተፈፃሚ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያም ሕግን አለማወቅ ወይም የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት እንደማያድን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 81 ስር ተደንግጓል፡፡ በዚሁ መሠረት ሕግን አለማወቅ ወይም በሕግ ላይ መሳሳት መከላከያ ሊሆን እንደማይችል ያስቀምጣል፡፡ በሌላ በኩል በፍትሐ ብሄር ሕግ አንቀጽ 2035/1 እና 2 ስር አንድ ሰው በሕግ ላይ በትክክል የተገለፀውን ድንጋጌ፣ ልዩ ደንብና ሥርዓት የጣሰ እንደሆነ ጥፋተኛ እንደሆነ እና ሕግን አለማወቅ ይቅርታ ሊያስገኝ የማይችል መሆኑ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የሕግ መኖር ማወቅ የሚቻልበት መንገድ
ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም የሚል የሕግ መርህ ተቀባይነት አለው ማለት ሁሉም ሰው ሕግ የማወቅ ግዴታ እንዳለበት እና የሕግን መኖር ያውቃል የሚል ግምት እንደሚወሰድ ያመለክታል፡፡ ታዲያ ሁሉም ሰው ሕግን የተማረ ሊሆን የማይችል በመሆኑ እንዲሁም ሕግን ቢማር እንኳ ሁሉን ሕግ በተገቢው ሁኔታ ያውቃል ማለት ተጨባጭ (realistic) የማይመስል በመሆኑ የሕግን መኖር እንዴት ማወቅ ይቻላል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡
የሕግን መኖር በተለያዩ መንገዶች ማወቅ ይቻላል፡፡ ይኸም በዋናነት ህጎች የሚፀኑበትን ጊዜ ከሚገነግጉ ድንጋጌዎች ሲሆን ሕግ የሚፀናበት ጊዜ በተለያዩ ህጎች ላይ በተለያየ ሁኔታ ተገልፆ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት ህጉ ወይም አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከሚወጣበት ቀን ጀምሮ የሚፀና ይሆናል፣ ህጉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል እና የተወሰነ ቀን በማስቀመጥ ከዛ ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ሊደነገግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት በህዳር 29/1987 የፀደቀ ሲሆን ከነሐሴ 15/1987 ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውል እና የፀና እንደሚሆን በመደንገግ ህጉ የሚፀናበትን ጊዜ በዚህ መልኩ አውጇል ፡፡ በመሆኑም ህጎቹ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታውጀው ከፀደቁበት ቀን ጀምሮ ወይም በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ በህብረተሰቡ ይታወቃሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
ሕግን አለማወቅ እና የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ መርህ የማይፈፀምበት ልዩ ሁኔታ
ሕግን አለማወቅ እና የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ መርህ የማይፈፀምበት ልዩ ሁኔታ የተፈጠረው በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍርድ ቤቶች በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ነው። ፍርድ ቤቶች የሕግ አለማወቅ እንደ ሰበብ የተቀበሉት የሕግ ጥሰት ሆን ተብሎ ያልተፈፀመ ወይም ያለጥፋት ሲጣስ ሆኖ በዚህ ጊዜ ቅጣት ለመጣል ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ስለሆነም የሕግ ስህተት እንደ መከላከያ የሚሠራው የሕግ ስህተቱ ሐቀኛ ሆኖ በቅን ልቦና ሲሠራ ነው። እንዲሁም የተከሳሽ ሕግን አለማወቅና ስህተት ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ አጠቃላይ ሕግን አለማወቅ እና የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት አያድንም የሚለው መርህ ተፈፃሚ አይሆንም ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ወንጀል ሕግ አንቀጽ 81/2 ስር እንደተደነገገው ድርጊቱን ለመፈፀም መብት ያለው መሆኑን በቅን ልቦና ለማመንና እንደዚህ ባለ የተሳሳተ እምነት ላይ ለመገኘት በቂና እርግጠኛ ምክንያት ያለው ሆኖ ለተገኘ ወንጀለኛ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ሊያቀልለት እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን የሚወስነው ከስህተት የደረሰበትን ምክንያት በተለይም የስህተትና የነገሩን ሁኔታ በመገመት ነው፡፡ በተጨማሪ ምክንያት ሊገኝበት በሚችልና ፍፁም በሆነ አለማወቅና ቅን ልቦና እንዲሁም ወንጀሉን የማድረግ አሳብ መኖሩን በግልፅ በማይታይባቸው የተለዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ከቅጣት ነፃ ለማድረግ እንደሚችል የወንጀል ህጉ ይደነግጋል፡፡
በአጠቃላይ ሕግ የሰዎችን የእለት ተዕለት ተግባር በመግዛት ሰላማዊ ኖሮ እንዲኖሩ የሚያስችል አንዱ መሳሪያ በመሆኑ ሰዎች ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት እንደማያድን እና መከላከያ ሊሆን እንደማይችል በማወቅ በተቻለ መጠን ህገ ወጥ ከሆኑ ተግባራት እራሳቸውን በማረቅ ይኖርባቸዋል፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት