የወንጀል እና የፍትሐብሔር ህግ ልዩነት

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ህጎች የሚያካትቱትን ጉዳይ፣ የሚያስከትሉትን የኃላፊነት ዓይነት፣ የተሳታፊ አካላትን (parties) እና የመሳሰሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች ከግንዛቤ በማስገባት የወንጀል እና የፍትሐብሔር ተብለው ይከፈላሉ፡፡ የወንጀል ሕግ የህብረተሰብ ሕግ (public law) አካል ሲሆን የፍትሐብሔር ሕግ ደግሞ የግል ሕግ (private law) አካል ነው፡፡ ከሕግ ግንዛቤ እጥረት የተነሳ ማህበረሰቡ በሁለቱ የሕግ ዓይነቶች መካከል ያለውን ልዩነት ባለመገንዘብ ግር ሲሰኝ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ሰዎች ክርክርና ሙግት ሲገጥማቸው ጉዳዩ ወንጀል ይሁን ፍትሐብሔር ባለመለየት የወንጀል ጉዳይን በፍትሐብሔር ክርክር ለመፍታት የፍትሐብሔር ጉዳይን በወንጀል እንዲጣራ ጥያቄ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ በወንጀል እና በፍትሐብሔር ሕግ መካከል ያሉትን ዋና ዋና የልዩነት ነጥቦች እንመለከታለን፡፡

የወንጀል ሕግ አና የፍትሐብሔር ሕግ ምንነት

ስለ ወንጀል ሕግ እና ፍትሐብሔር ሕግ ከማየታችን በፊት ሕግ ምንድነው የሚለውን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ሕግ ማለት በአጭሩ ዜጎች ማድረግ ያለባቸው ወይም ማድረግ የሌለባቸውን ድርጊቶች የሚዘረዝር፣ በማድረግ ወይም ባለማድረግ ህጎችን መተላለፍ የሚያስከትለውን ቅጣት ወይም ውጤት የሚይዝ ገዢ ደንብ ነው፡፡

የወንጀል ሕግ በአጠቃላይ የሀገርን እና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል የሚወጣ ሆኖ እንደ ወንጀል የሚቆጠሩ ድርጊቶች የሚዘረዝር እና ተፈጽመው ሲገኙ የሚያስከትሉትን ቅጣቶች የሚደነግግ ሕግ ነው፡፡ በድርጊቶቹ መፈጸም ቀጥተኛ ተጎጂዉ አንድ ግለሰብ ቢሆንም እንኳን ጉዳቱ በማኅበረሰብ ላይ እንደደረሰ ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች እንዲቀጡ፣ ሌሎች ደግሞ ወንጀል እንዳይፈጽሙ ለማድረግ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች እንዲኖረው ተደረጎ የሚወጣ ሕግ ነው፡፡

የፍትሐብሔር ሕግ ግለሰባዊ ግንኙነቶችን እና መብቶችን እንዲሁም ግዴታዎችን (private relationships, rights and obligations) የሚደነግግና የሚገዛ ሲሆን በዋናነት የንብረት፣ የውል፣ የቤተሰብ፣ የውርስ ሕግን እና ከውል ዉጭ ኃላፊነትን የሚመለከቱ ህጎችን አካቶ የያዘ የሕግ ዘርፍ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች ወይም ግንኙነቶች በአግባቡ እንዲከበሩ እንዲሁም ባለመከበራቸው ምክንያት ጉዳት የደረሰበት አካል ሲኖር መብቱን የሚጠይቅበትን ሥነ-ሥርዓት የሚደነግገው ሕግም በዚሁ የሕግ ዘርፍ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ መሠረት የሚፈጠሩ መብቶች ሲጣሱ ወይም ግዴታዎች ሳይከበሩ ሲቀሩ የሚከሰቱ ችግሮች እንደአጠቃላይ የማኅበረሰብ ጉዳት የሚታዩ ሳይሆኑ በቀጥታ ጉዳቱ የደረሰበት አካል ጉዳት ናቸው፡፡

የወንጀል እና የፍትሐብሔር ሕግ መሠረታዊ የልዩነት ነጥቦች

በፍትሐብሔር ሕግ የተደነገገ መብት በመጣሱ ምክንያት በሚመለከተው አካል ፊት ቀርቦ መብቱን መጠየቅ የሚችለው መብቴ ተጥሷል የሚለው ሰው ሲሆን የወንጀል ድርጊት በተፈጸመ ጊዜ ግን ኃላፊነት ወስዶ አጥፊዎች እንዲቀጡ የሚያደርገው ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡ በወንጀል የሚኖር ተጠያቂነት በመርህ ደረጃ በማድረግ ወይም ባለማድረግ በቀጥታ ተሳታፊ በሚሆን ሰው ላይ ሲሆን በፍትሐብሔር ሕግ ግን ከጥፋት ውጪ (strict liability) በሆነ መንገድ ወይም በሌሎች ጥፋት (vicarious liability) ተጠያቂነት ጥፋት በሌለበት ሰው ላይ ሊኖር ይችላል፡፡

ወንጀልን መሠረት አድርጎ የሚፈጠር የግለሰቦች ተቃርኖ በግለሰቦቹ በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስሱ ቀላል ወንጀሎች ካልሆኑ በስተቀር እርቅ ወይም ስምምነት ክሱን ቀሪ ሊያደርግ አይችልም፡፡ እርቅ ቢደረግም እንኳን ለአጥፊው እንደ ቅጣት ማቅለያ ከሚያዝ በስተቀር ከተጠያቂነት የሚያድን አይሆንም፡፡ ፍትሐብሔራዊ ጉዳይን መሠረት አድርጎ በግለሰቦች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት ግን በማናቸውም ጊዜ በተበዳዩ ፍላጎት አልያም በሁለቱ ወገኖች እርቅ (ስምምነት) ክሱ ቀሪ ሊሆን ይችላል፡፡

ጥፋትን ለማስረዳት ወይም ለማረጋገጥ ተግባራዊ ከሚደረገው የማስረጃ ምዘና መለኪያ አንጻርም ዘርፎቹ ይለያያሉ፡፡ የወንጀል ሕግ ሲጣስ ወንጀል ፈጻሚውን ጥፋተኛ ለማድረግ ወንጀል የተባለውን ድርጊት የፈጸመ ስለመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ (beyond reasonable doubt) በሆነ አግባብ የማስረዳት ግዴታ ሲኖርበት በፍትሐብሔር ረገድ ኃላፊነትን ለማቋቋም ከሳሽ ተከሳሽ ከሚያቀርበው ማስረጃ በተሻለ መልኩ አሳማኝ የሆነ ማስረጃ (preponderance of evidence) ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

የፍትሐ ብሔር ሕግ ዋና ዓላማ ተጎጂን በተቻለ አቅም እንዲካስ ማድረግ ሲሆን የወንጀል ሕግ ደግሞ የማህበረሰቡን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕግ በአብዛኛው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ወይም የጉዳት አድራሽን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚነካ ውሳኔን የሚያስከትል ሲሆን ይህም ያደረሰውን ጉዳት ወደነበረበት መመለስ ወይም መካስ ሊሆን ይችላል፡፡ የወንጀል ሕግ በአንጻሩ ጥፋተኞችን የሚያስተምርና ሌሎችን ወንጀል እንዳይፈጽሙ የሚያስጠነቅቅ ቅጣቶችን መጣል ላይ ያተኮረ እና እንደ መቀጮ፣ እስራት አለፍ ሲልም የሞት ቅጣት የሚያስከትል ነው፡፡

የውሳኔውም አፈጻጸም ሲታይ በወንጀል ክርክር በፍርድ ቤት የሚሰጥ ውሳኔን ተከታትሎ የሚያስፈጽመው መንግሥት ሲሆን በፍትሐብሔር ክርክር የሚሰጥ ውሳኔን ተከታትሎ የማስፈጸሙ ኃላፊነት ውሳኔ የተወሰነለት ሰው ወይም የፍርድ ባለመብት ነው፡፡

ማጠቃለያ

የወንጀል እና የፍትሐብሔር ሕግ ያላቸው መሠረታዊ ልዩነት ከላይ የተገለፀው ሲሆን እነዚህን ልዩነቶች ማወቅ ለሚገጥሙ ችግሮች የምንፈልገውን መፍትሄ የሚወስኑ በመሆኑ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ