የግል ቤቶችን ወይም የተከለከሉ ቦታዎችን መድፈር የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት

ማውጫ

Share this Article

ወንጀል አብዛኛውን ጊዜ በሰዎች አካልና ደኅንነት እንዲሁም መሠረታዊ የሆኑ መብቶች ላይ ይፈፀማል። በሰዎች መብት ላይ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መካከል አንዱ የግል ቤቶችን ወይም የተከለከሉ ቦታዎችን መድፈር ሲሆን አብዛኛው ማኅበረሰብ ቤቶችን መድፈር ወይም በተከለከሉ ቦታዎች መገኘት እንደ ወንጀል የሚቆጠር ስለመሆኑ አይረዳም። በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ሕግ የግል ቤቶችን ወይም የተከለከሉ ቦታዎችን መድፈር በወንጀል እንደሚያስጠይቅ ተደንግጎ ይገኛል። በዚህ ጽሑፍም ይህ የወንጀል ተግባር በምን ሁኔታ ሲፈፀም ሊያስጠይቅ እንደሚችል እና የሚያስከትለውን ቅጣት እንመለከታለን።

የግል ቤቶችን ወይም የተከለከሉ ቦታዎችን መድፈር ምንነት

የግል ቤቶችን ወይም የተከለከሉ ቦታዎችን መድፈር ምን ማለት እንደሆነ በግልፅ የተቀመጠ ትርጉም ባይኖርም የወንጀል ህጉን ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግ የሚከተለውን ትንታኔ መስጠት ይቻላል። በዋናነት ትርጉም የሚያስፈልገው “መድፈር” የሚለው ቃል ሲሆን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 604 መሠረት መድፈር ማለት ወደ ግለሰብ ወይም በድርጅት ግቢ ያለፍቃድ ገብቶ መገኘት ወይም ከገባ በኋላ ውጣ ሲባል አሻፈረኝ ማለት እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በመሆኑም ግቢ መድፈር ማለት በግለሰብ ቤት ውስጥ በኃይል ወይም ሳይፈቀድለት መግባትና ተፈቅዶለት ከገባ በኋላ ለመውጣት እንቢ ማለት እና በተከለከለ ቦታ ላይ ያለፍቃድ መገኘት ማለት ነው። ይህ ሲባል ግን ባለይዞታ የሆነው ሰው ሁልጊዜ የግድ በቃላት መቃወም ይገባዋል ማለት ሳይሆን እንደነገሮች ነባራዊ ሁኔታ ማለትም ሰዎች ግቢያቸውን አጥረው ማስቀመጣቸው የሌላን ሰው ያለፈቃድ መግባት መቃወም ነው ተብሎ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው አንድን የታጠረ ግቢ አጥሩን በመስበር፣ በመዝለል ወይም ያለፈቃድ መዝጊያውን በመክፈት ገብቶ ቢገኝ ምንም እንኳን ባለቤቱ በቦታው ተገኝቶ ባይቃወምም የግቢ መድፈር ወንጀሉ ግን እንደተፈፀመ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡

የወንጀል ተጠያቂነት

የግል ቤቶችን መድፈርም ሆነ በተከለከሉ ቦታዎች መገኘት የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በወንጀል ህጉ አንቀጽ 604 እና 605 ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል። በወንጀል ህጉ አንቀጽ 604 እንደተቀመጠው ማንም ሰው ከሕግ ውጭ፡-

  • ህጋዊ ነዋሪ የሆነው ሰው እየተቃወመ ወደ አንድ ቤት፣ ግቢ፣ ጀልባ ወይም ለመኖሪያ ወደሚያገለግል ማንኛውም ሌላ ቦታ ወይም ከቤቱ ወይም ከመኖሪያው ቦታ ጋር ወደ ተያያዘና ወደ ተከለከለ ቦታ ወይም የአትክልት ቦታ ወይም የግል ይዞታ ወደ ሆነ ማንኛውም ሌላ ንብረት የገባ እንደሆነ ወይም
  • ሰው ባይኖርበትም ወደ አንድ መስሪያ ቤት፣ ድርጅት፣ ኩባንያ ወይም ህጋዊ ሰውነት ያለው ማህበር ህንፃ፣ ቢሮዎች፣ ግምጃ ቤት /መጋዘን/ ወይም አጥር ግቢ ሳይፈቀድለት በኃይል የገባ እንደሆነ ወይም
  • ህጋዊ ነዋሪው ሳይቃወመው ወይም ፈቅዶለት ከገባ በኋላ እንዲወጣ ሲጠይቀው ያልወጣ እንደሆነ፣ የግል ቤቶችን ወይም የተከለከሉ ቦታዎችን መድፈር ወንጀል ፈፅሟል ማለት ነው።

ከዚህ አንቀጽ የምንረዳው አንድ ሰው ይህን የወንጀል ድርጊቱን ፈፀመ የሚባው ቤት ወይም ግቢ መድፈሩ ከሕግ ውጭ መሆኑ እና ተቃውሞ እየገጠመው ቤት ውስጥ ወይም ግቢ ውስጥ መግባቱ ወይም ከገባ በኋላ ውጣ ሲባል እንቢ ማለቱ እንደሆነ ነው። የግል ቤትን ወይም የተከለከሉ ቦታዎችን መድፈር ወንጀል መፈፀሙ የተረጋገጠበት ማንኛውም ሰው ከሶስት ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል።

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ወንጀሉን ያደረገው የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ በግል ቤት ወይም የተከለከለ ቦታ ላይ እንዲገባ ያልተፈቀደለት ወይም ቢፈቀድለትም ሊከተለው የሚገባውን ሕግ፣ ጥንቃቄ ወይም ሥነ-ሥርአት (ከብርበራ ጋር በተያያዘ ሥነ-ሥርአትን) ያልተከተለ እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 422 የተመለከተውን ቅጣት ይቀጣል፡፡ ይኸውም ድርጊቱን የፈፀመው ሳይፈቀድለት ከሆነ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት የሚቀጣ ሲሆን ተፈቅዶለት በሕግ የተቀመጠውን ሥርአት በመጣስ የፈፀመው ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት የማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ ይሆናል።

ወንጀሉን የሚያከብዱ ሁኔታዎች

በግል ቤት ወይም በተከለከሉ ቦታዎች ከሕግ ውጭ የገባ፣ ተፈቅዶለት ከገባ በኋላ እንዲወጣ ሲጠየቅ እንቢ ብሎ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመ ሰው ወይም ወንጀሉ የተፈፀመው፡-

  • መሳሪያ በመያዝ፣ በመዛት ወይም በኃይል ድርጊት በመጠቀም ሲሆን ወይም
  • በጋራ በተስማሙ የሰዎች ስብስብ ሲሆን ወይም
  • በሌላ አኳኋን በሕግ የተፈቀደው እንደተጠበቀ ሆኖ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ሲሆን ወይም
  • የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ባለሥልጣን መስሎ በመቅረብ የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመ እንደሆነ

ቅጣቱ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚሆን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 605 ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል።

የግል ቤት፣ ግቢ ወይም የተከለከሉ ቦታዎችን መድፈር በሰዎች መብት ላይ የሚፈፀም ወንጀል በመሆኑ ማንኛውም ሰው ከዚህ አይነት የወንጀል ተግባር መቆጠብ ይጠበቅበታል።

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ