በወንጀል ሕግ መሠረት የሚያስጠይቁ የወንጀል ተግባራት በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን እነሱም በማድረግ እና ባለማድረግ የሚፈፀሙ ናቸው። የመጀመሪያው አታድርግ የተባለን ነገር በማድረግ የሚመጣ የወንጀል ኃላፊነት ሲሆን በሁለተኛው ደግሞ አድርግ በሚል በሕግ የሚጣልን ግዴታ ባለማድረግ የሚመጣ ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ በወንጀል ሕግ አድርግ ተብሎ በሕግ የተጣለን ግዴታ ባለመወጣት የሚመጣን የወንጀል ኃላፊነት በተመለከተ እንዳስሳለን።
ባለማድረግ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ምንነት
ባለማድረግ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተደረጉ የሚባለው በወንጀል ድንጋጌ መሠረት አድርግ ተብሎ የተደነገጉ ድርጊቶች ሳይደረጉ ሲቀሩ ነው፡፡ በመሆኑም ባለማድረግ የሚመጣን የወንጀል ኃላፊነት ለማቋቋም በመሠረታዊነት በሕግ አድርግ የመባል ግዴታ መኖር የግድ ሲሆን እያንዳንዱ ሰው ይህ ግዴታ በሕግ የተጣለ መሆኑን ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም በወንጀል ሕግ አንቀጽ 81 መሠረት ሕግን ያለማወቅ ከተጠያቂነት የማያድን በመሆኑ ነው፡፡
በወንጀል ህጉም ሆነ በሌሎች ልዩ ህጎች በሕግ የተጣለን ግዴታ አለማድረግ በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ የተደነገገባቸው ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በወንጀል ሕግ መሠረት ባለማድረግ የሚያስጠይቁ ወንጀሎችን በሁለት ከፍለን ማየት የምንችል ሲሆን እነዚህም በሁሉም ሰው ላይ ግዴታ የሚጥሉ እና በተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ ግዴታን የሚጥሉ ናቸው። እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡፡
በተዘዋዋሪ መንገድ መርዳትና ማበረታታት
ማንም ሰው በአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ የፖለቲካና የግዛት ሊዓላዊነት፣ የመከላከያ ኃይል ወይም የውስጥና የውጭ ደኅንነት ላይ ወንጀል የተፈፀመ ወይም ሊፈፀም የተመከረ መሆኑን ወይም ወንጀል እንዲፈፀም የመሰናዳት ተግባር መከናወኑን እያወቀ ለባለሥልጣን ሳያሳውቅ የቀረ ወይም አደጋው እንዳይደርስ ወይም አድራጊው እንዲያዝ የሚችለውን ያላደረገ እንደሆነ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ወይም ግልፅ በሆነ ምክንያት ለማስታወቅ አለመቻሉን ካላስረዳ በስተቀር ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፊ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 254 ስር ተደንግጎ ይገኛል።
በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳት
በወንጀል ሕግ አንቀጽ 575 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው በራሱ ወይም በሶስተኛ ወገኖች ላይ አደጋ በማያደርስ ሁኔታ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ሊረዳው ሲችል በህይወቱ፣ በሰውነቱ ወይም በጤንነቱ ላይ ሊደርስ በሚችል ከባድ አደጋ ላይ የሚገኘውን ሌላ ሰው አስቦ ሳይረዳው የቀረ እንደሆነ ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል። የዚህን ድንጋጌ አጠቃላይ መንፈስ ስንመለከት አድርግ የተባለን ተግባር ባለማድረግ የሚመጣን የወንጀል ኃላፊነት የሚያመለክት ሲሆን ይህም ግዴታውን ለመወጣት በሚያስችል ሁኔታ ውስጥ መገኘት እንዲሁም ግዴታውን በሚወጣው ሰውና በሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ጥቅም ላይ ጉዳትና አደጋ የማይደርስ መሆኑ ዋና ዋና መስፈርቶች ሆነው እናገኛቸዋለን። በአጠቃላይ በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳት በወንጀል የሚያስጠይቀው ሆን ተብሎ ወይም ታስቦ ሲፈፀም፣ በቅርብ የሚደርስ አደጋ መኖሩ ሲረጋገጥ፣ ግዴታ የሚጣልበት ሰው ጉዳቱን ለመከላከል የሚያስችል ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን እና በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው በመርዳቱ በራሱና በሶስተኛ ወገኖች ላይ አደጋ የማይደርስ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው። በመሆኑም በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው ባለመርዳት ተጠያቂ ለመሆን ከላይ የተዘረዘሩት መስፈርቶች ባንድነት ተሟልተው መገኘት አለባቸው።
በወንጀል ህጉ ባለማድረግ እንደሚያስጠይቁ ከተደነገጉት ድንጋጌዎች በተጨማሪ በተለያዩ አዋጆች ባለማድረግ የሚያስጠይቁ ወንጀሎች አሉ። አብነት ለመጥቀስ ያክል የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 15 መሠረት የሽብር ወንጀልን አለማሳወቅ የሚያስጠይቅበት ሁኔታ ያለ ሲሆን ይህም ማንኛውም ሰው በአዋጁ አንቀጽ 3 የሽብር ድርጊት፣ አንቀጽ 6 የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ማቀድ እና ማሰናዳት፣ አንቀጽ 7 የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ማደም፣ አንቀጽ 9 ድጋፍ ማድረግ፣ አንቀጽ 10 ማነሳሳት እና አንቀጽ 11 ከሽብር ወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረትን ስለመያዝ ከተመለከቱ የሽብር ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ሊፈጸም፣ እየተፈፀመ ወይም የተፈፀመ መሆኑን እያወቀ ወይም የወንጀል ፈፃሚውን ማንነት እያወቀ በቂ ምክንያት ሳይኖረው ወዲያውኑ ለፖሊስ ወይም አግባብ ላለው ሕግ አስፈፃሚ አካል ያላስታወቀ እንደሆነ ከአንድ ዓመት እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ እንዲሁም ወንጀልን አለማስታወቁ ከባድ ሲሆን በተለይም መረጃው ቀድሞ ደርሶ ቢሆን የወንጀሉን መፈፀም መከላከል ወይም መቆጣጠር የሚቻል ዓይነት ሲሆን ቅጣቱ ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ይሆናል፡፡
በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 13 መሠረት በሰው መነገድ ወይም በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ወይም በህገወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀል መፈፀሙን ወይም እየተፈፀመ መሆኑን ወይም የወንጀሉን ፈፃሚ ማንነት እያወቀ በቂ ምክንያት ሳይኖረው ለፖሊስ ወይም አግባብ ላለው የሕግ አስከባሪ አካል ወዲያውኑ ያላሳወቀ ወይም ሐሰተኛ ማስረጃ የሰጠ እንደሆነ ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት የሚቀጣ ሲሆን ድርጊቱ ከባድ ሲሆን ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል።
ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች ኃላፊነትን የሚጥሉት በሁሉም ሰው ላይ ሲሆን በልዩ ሁኔታ የተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ ግዴታ የሚጥሉ የሕግ ድንጋጌዎችን በመቀጠል እንመለከታለን።
ሰውን ለአደጋ ማጋለጥ ወይም መተው
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 574 ላይ እንደተደነገገው በጤናው፣ በሁኔታው ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ራሱን ለመጠበቅ የማይችለውን ሌላ ሰው በማናቸውም ምክንያት ይሁን በጠባቂነት ወይም በኃላፊነት ለማኖር የተቀበለ ማንም ሰው የተባለውን ሰው አስቦ በህይወቱ ወይም በጤናው ላይ በቅርቡ መድረሱ ለማይቀር አደጋ ያጋለጠው እንደሆነ (በማድረግ የሚፈፀም ሲሆን) ወይም ይህን መሰል ሁኔታ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ጥሎት የሄደ እንደሆነ አስፈላጊ ሲሆን ከቤተዘመድ ሥልጣን የመሻሩ ቅጣት እንደተጠበቀ ሆኖ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ወይም ከስድስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ይቀጣል። ይህ ድንጋጌ ተጠያቂነት የሚያስከትለው ራሱን ለመጠበቅ የማይችልን ሌላ ሰው በማናቸውም ምክንያት ይሁን በጠባቂነት ወይም በኃላፊነት ለማኖር የተቀበለ ሰው ላይ ነው፡፡
ቀለብ የመስጠት ግዴታን አለመፈፀም
ማንም ሰው ያለበቂ ምክንያት በቤተሰብ ሕግ መሠረት ሊሰጥ የሚገባውን ቀለብ ለባለመብቶች፣ የፍቺ ውሳኔ እስከሚሰጥ ጊዜ ድረስ የፍቺ ጥያቄ ላቀረበ የትዳር ጓደኛም ቢሆን፣ አልሰጥም ያለ ወይም መስጠትን ያስተጓጎለ እንደሆነ ወይም በሕግ ወይም በውል በገባው ግዴታ መሠረት ከጋብቻ ውጪ ላስረገዛት ሴት ወይም ከጋብቻ ውጪ በግብረስጋ ግንኙነት አብሮት ለኖረው ሰው ወይም ከጋብቻ ውጪ ለተወለደ ልጅ ሊያሟላ የሚገባውን የገንዘብ ግዴታ ያልተወጣ እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በመቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚቀጣ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 658 ይደነግጋል። ይህ ድንጋጌ ተጠያቂነት የሚያስከትለው በሕግ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ተጥሎበት ግዴታውን ባልተወጣ ሰው ላይ ነው፡፡
ልጅ የማሳደግ ግዴታን አለመፈፀም
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 659 ላይ እንደተደነገገው ማንም ወላጅ ወይም የአሳዳሪነት ወይም የሞግዚትነት ሥልጣን ያለው ሌላ ሰው ጥቅምን በመፈለግ ወይም ያለበትን ግዴታ ቸል በማለት በኃላፊነቱ ሥር የሚገኘውን ልጅ በከባድ ሁኔታ ያለ በቂ ጥንቃቄና ክብካቤ የተወ ወይም ለሥነ ልቦናዊ ወይም አካላዊ አደጋ ያጋለጠ እንደሆነ ወይም አካላዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንደሚያደርስበት ለሚያውቀው ወይም መገመት ለሚችለው ሰው፣ ድርጅት ወይም ተቋም ልጁን ለረጅም ጊዜ የሰጠ እንደሆነ ነገሩ ከባድ ሲሆን ከቤተዘመድ ሥልጣኑ መሻሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል። በዚህ ድንጋጌ ተጠያቂ ለመሆን ወላጅ ወይም የአሳዳሪነት ወይም ሞግዚትነት ሥልጣን መኖር ግድ ስለሚል ይህ ባለማድረግ የሚፈፀመው ወንጀል የሚያስጠይቀው ማንንም ሰው ሳይሆን ይህ ኃላፊነት የተጣለባቸውን ሰዎች ብቻ ይሆናል ማለት ነው።
በአጠቃላይ በወንጀል ሕግ መሠረት ባለማድረግ የሚያስጠይቁ ወንጀሎች በሕግ የማድረግ ግዴታ የሚጥሉ ድንጋጌዎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ሲሆን ከዚህ የወንጀል ተጠያቂነት ለመዳን ሕግ የጣለብንን ኃላፊነት ማወቅና መወጣት ይገባል።
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ