በህይወት መኖር ከሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶች ወይም ሰብዓዊ መብቶች በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያለው መብቶች ናቸው፡፡ በኢ.ፌ.ድ.ሪ. ህገ መንግሥት አንቀጽ 14 ስር ስለ የህይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብት እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በህይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብት አለው፡፡ በመሆኑም የሰው ልጆች በህይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነቻቸው የመጠበቅ መብት፣ የነጻነት መብት፣ ከኢ-ሰብዓዊ አያያዝ የመጠበቅ እና በህገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተዘረዘሩት ሰብዓዊ መብቶች አሏቸው፡፡ ሌሎች ሰዎች በሰው ህይወት ወይም አካል ላይ ጉዳት አድርሰው ቢገኙ በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
በህገ መንግስቱ የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነጻነት ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሠነዶች መርሆች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ፡፡ እነዚህ ሰብዓዊ መብቶች በህገ መንግስቱ ሽፋን ከማግኘታቸው በተጨማሪ በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ሕግ ውስጥ በስፋት እና በዝርዝር መብቶቹን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀል የሆኑትን ድርጊቶች እና የሚያስከትሉት ቅጣት ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም ሰዎች በየእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው እነዚህን ድንጋጌዎች ላለመተላለፍ እና የሰዎችን መብት ለማክበር ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ትምህርታዊ ጽሑፍ በወንጀል ህጉ ውስጥ የተካተቱ በሰው ህይወት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ምን ምን እንደሆኑ እና የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነትና ቅጣት እንመለከታለን፡፡
በሰው ህይወት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች
ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር መብት እንዳለው እና በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ህይወቱን እንደማያጣ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 15 ስር ሰፍሯል፡፡ የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ሕግ ለዚህ መሠረታዊ የሰው ልጆች መብት ጥበቃ ለማድረግ የወንጀል ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡ በሰው ህይወት ላይ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መካከል አንደኛው የሰው መግደል ወንጀል (Homicde) ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡
ከወንጀል ህጉ አንፃር የሰው መግደል ወንጀል ሆን ተብሎ (ታስቦ) የሚፈፀም የሰው መግደል ወንጀል፣ በቸልተኝነት የሚፈፀም የሰው መግደል እና ህፃንን መግደል በሚል ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ማንም ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት በማናቸውም መሳሪያ ወይም ዘዴ ሌላውን ሰው የገደለ እንደሆነ ነፍሰ ገዳይ ነው ( የወ/ሕግ አንቀጽ 538/1) ፡፡ አስቦ ወይም በቸልተኝነት ሰውን በመግደል ጥፋተኛ የሆነ ሰው ላይ የሚጣለው ቅጣት እንደ አገዳደሉ ሁኔታ በቀላልነት እና በከባድነት ይወሰናል፡፡ አስቦ ወይም በቸልተኝነት ሰውን የገደለ ሰው ሁሉ የሚቀጣው ሕጋዊ በሆኑ የፍርድ ሂደቶች እና በውሳኔዎች መሠረት ብቻ ይሆናል፡፡
ታስቦ የሚፈፀም የሰው መግደል ወንጀል
በወንጀል ህጉ እንደተደነገገው ታስቦ የሚፈፀውን የሰው መግደል ወንጀል በሶስት ተከፍሎ እናገኘዋለን፡፡ ይኸውም በአንቀጽ 539 ከባድ የሰው ግድያ፣ በአንቀጽ 540 ተራ የሰው ግድያ እና በአንቀጽ 541 ቀላል የሰው ግድያ ተብለው በንፅፅር ዓይነት ተመልክተዋል፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 539 ቅጣትን የሚያከብዱ ምክንያቶች በሚኖሩበት ጊዜ ያለውን የሚመለከት ሲሆን የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 541 ደግሞ ቅጣት የሚያቀሉ ምክንያቶች (በራሱ በድንጋጌ ውስጥ የተመለከቱት ሁኔታዎች) በሚኖሩበት ጊዜ ያለውን የሚመለከት ነው፡፡
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 541 ከተመለከቱት ሁኔታዎች ውጪ ሆን ተብሎ የሚፈፀሙ የሰው መግደል ወንጀሎች ደግሞ ተራ የሰው ግድያ በሚለው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 540 ድንጋጌ መሠረት የሚሸፈን ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር ተራ የሚለው ቃል የግድያውን ቀላልነት የሚያሳይ ሳይሆን በከባድ ግድያና በቀላል ግድያ መካከል የሚገኝ የግድያ ዓይነት መሆኑን ለማሳየት የተቀመጠ ነው፡፡
የሰው መግደል ድርጊት በራሱ ጨካኝነት፣ ነውረኝነት፣ አደገኝነት፣ የሚያሳይ ተግባር ስለሆነ በወ/ህ/አ 539 ላይ ገዳዩ በተለይ ጨካኝ፣ ነውረኛ ወይም አደገኛ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ የሚለው ግድያው ሆን ተብሎ መፈፀሙን ብቻ ሳይሆን መሠረት የሚያደርገው የግድያውን አፈፃፀም እና የአገዳደሉን ሁኔታ ነው፡፡ ስለሆነም ጨካኝነት፣ ነውረኝነት እና አደገኝነት ወንጀሉን ለማቋቋም ሊኖር የሚገባው መመዘኛ መሠረት የሚያደርገው ምክንያት የህብረተሰቡን ማኅበራዊ እድገት እና ባህላዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፡፡
ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል (አንቀጽ 539)
ማንም ሰው ፡-
- ሀ) ሰውን ለመግደል አስቀድሞ የነበረው አሳብ፣ ወይም ምክንያት፣ ለመግደል የተጠቀመበት መሳሪያ ወይም ዘዴ፣ የገዳደሉ ሁኔታ ወይም ግድያው የተፈፀመበት ቅጣትን የሚያከብድ ጠቅላላ ምክንያት /አንቀጽ 84/ ወይም ሌላ ምክንያት /አንቀጽ 86/ ሲታይ ገዳዩ ጨካኝ ፣ ነውረኛ ወይም አደገኛ መሆኑን በሚገልፅ ሁኔታ፣
- ለ) ሰውን ለመግደል ወይም የውንብድና ወንጀልን ለመፈፀም የተደራጀ የወንበዴ ቡድን አባል በመሆን፣
- ሐ) ሌላ ወንጀል ለመፈፀም እንዲመቸው ወይም የተፈፀመ ወንጀል እንዳይገለፅ ለማድረግ ሲል አስቦ ሰው የገደለ ሰው በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል፡፡
በተራ የሆነ የሰው ግድያ ወንጀል (በአንቀጽ 540)
ማንም ሰው አገዳደሉ በአንቀጽ 539 የተመለከተውን ያህል ከባድ ወይም በአንቀጽ 540 የተመለከተውን ያህል ቀላል ባልሆነ ሁኔታ አስቦ ሰውን የገደለ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ ሀያ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡
ቀላል የሆነ የሰው ግድያ ወንጀል (በአንቀጽ 541)
የአስገዳጅ ሁኔታ ወሰንን በመተላለፍ ወይም ህጋዊ መከላከልን ከመጠን በማለፍ ወይም ከፍ ባለ ደም በሚያፈላ ምክንያት ወይም ባልተጠበቀው ሕሊናን በሚያውክ ድንገተኛ ምክንያት ወይም በከፍተኛ ስሜት ወይም በብርቱ ዝንባሌ የተነሳ ሆኖ፣ በአዕምሮ ግምት ይህን ለማድረግ በሚያደርስና በከፊል ይቅርታን በሚያሰጡ ሁኔታዎች አስቦ ሌላ ሰው የገደል እንደሆነ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል፡፡
በቸልተኝነት የሚፈፀም የሰው መግደል ወንጀል
ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 543 አኳያ በቸልተኝነት ሰው በመግደል የሚፈፀሙ ወንጀሎች በሶስት ተከፍለው ይታያሉ፡፡ እነሱም፡-
- ማንኛውም ሰው የሚፈፅመው የቸልተኝነት ግድያ ፡- ከ6 ወር እስከ 3 ዓመት ሊደርስ በሚችል ቀላል እስራት ወይም ከ 2ሺ እስከ 4ሺ ብር ሊደርስ በሚችል መቀጮ ያስቀጣል፡፡
- በተለየ ህይወት፣ ጤንነት ወይም ደኅንነት የመጠበቅ የሙያ ወይም የሌላ ግዴታ ያለበት ሰው ግዴታውን በመጣስ የሚፈፅመው የቸልተኝነት ግድያ፡- ከ1 ዓመት እስከ 5 ዓመት ሊደርስ በሚችል ቀላል እስራት እና ከ3 ሺ እስከ 6ሺ ብር ሊደርስ በሚችል መቀጮ ይቀጣል፡፡
- ጥፋተኛው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን የገደለ ወይም ወንጀሉን የፈፀመው ግልፅ የሆነ ደንብ ወይም መመሪያን ተላልፎ እንደሆነ ወይም የሚያሰክሩ ወይም የሚያፈዙ ንጥረ ነገሮችን ወይም መጠጦችን በመውሰድ እራሱን ከኃላፊነት በሚያስወጣ ሁኔታ ካስገባ በኃላ የተፈፀመ ግድያ ፡- ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት ለመድረስ በሚችል ፅኑ እስራት እና ከብር 10 ሺ እስከ 15 ሺ በሚደርስ መቀጮ የሚቀጣባቸው ናቸው፡፡
ሕፃንን መግደል
በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ መንግሥት ለሕፃናት ከተሰጡ መብቶች መካከል በህይወት የመኖር መብት ቀዳሚው ነው፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 36/1/ሀ ስር ማንኛውም ህፃን በህይወት የመኖር መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ የሕፃናትን የህይወት እና የአካል ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ በዋናነት የወላጆች እና ያሳዳሪዎች ነው፡፡ ለሕፃናት ህይወት በህገ መንግስቱ ከተደረገላቸው ጥበቃ በተጨማሪ የወንጀል ህጉ ይህንን ጠበቃ በመጣስ የሕፃናት ህይወት ላይ ጉዳት ያደረሰ ሰው የሚከተሉት የወንጀል ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡
የወንጀል ሕግ አንቀጽ 544 ህፃንን መግደል
- አንዲት እናት ለመውለድ ምጥ በተያዘች ጊዜ ወይም የምጥ ስሜቷ ሳያልፍ ልጇን የገደለች እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እስራት ትቀጣለች፡፡
- አንዲት እናት በዚህ አንቀጽ 1 ከተመለከቱት ሁኔታዎች ውጭ ልጇን አስባ ወይም በቸልተኝነት የገደለች እንደሆነ፣ ግድያን የሚመለከቱት መደበኛ የህጉ ድንጋጌዎች ማለትም የወ/ህ/አ 539፣ 540፣ 541፣ 543 ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 በተመለከተው ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በአነሳሽነት ወይም በአባሪነት ተካፋይ የሆነ ሌላ ሰው የህጉ ልዩ አስተያየት ሳይደረግለት እንደነገሩ ሁኔታ እንደ ጥፋቱ መጠን ሰው ስለመግደል በተመለከቱት መደበኛ የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ይቀጣል፡፡
በመጨረሻም በወንጀል ህጉ በሰው ህይወት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ከተቀመጡ ድንጋጌዎች ውስጥ በፅንስ ላይ የሚደረግ ፅንስ የማስወረድ ወንጀል ይገኝበታል፡፡ በማንኛውም የእርግዝና ደረጃ የሚገኝን ፅንስ በሕግ ከተፈቀደው ምክንያት ውጪ ማስወረድ የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ፍርድ ቤት የቅጣቱን ዓይነትና መጠን የሚወስነው የማስወረድ ተግባሩ የተፈፀመው በእናቲቱ ወይም በሌላ ሦስተኛ ወገን መሆኑን፣ ድርጊቱ የተፈፀመው በሦስተኛ ወገን ከሆነ እናቲቱ ፈቅዳ ወይም ሳትፈቅድ መሆኑን ከግምት በማስገባት ይሆናል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 545) ፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ