የዜጎች መብት እና የመንግስት ግዴታ በፌደራል አሰተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

በፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብት መሠረታዊ የሆነ መብት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመንግሥት የአሠራር ፍትሀዊነት እና ግልፅነት ጭምር የሚገለፅ ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 12 የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት እና ማንኛውም ኃላፊና የሕዘብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን ደንግጓል፡፡ በዚህ መነሻነትም የፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 የወጣ ሲሆን አዋጁ ለዜጎች የተለያዩ መብቶችን የሚሰጥ እና በመንግሥት ላይ ደግሞ ግዴታዎችን የሚጥል ነው፡፡ ይህ አዋጅ የወጣበት ምክንያት ይህን ሕገ መንግሰታዊ መርሆ መሠረት በማድረግ የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉትን ጣልቃ ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ለማራጋገጥ፣ የእነዚህ ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና መመሪያ አወጣጥ መርሆችንና ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰው የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ሥርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትሕን ማስፈን በማስፈለጉ ነው፡፡ በአዋጁ መሠረት ዜጎች የተለያዩ መብቶች ያሏቸው ሲሆን አገልግሎት የማግኘት መብት፣ የመሳተፍ መብት፣ ቅሬታ የማቅረብ መብት፣ በፍርድ ቤት ክለሳ የመጠየቅ መብት የሚሉት እና ሌሎች መብቶች አሏቸው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ለዜጎች የተሰጡ መብቶችን እና የመንግሥት ግዴታዎችን የምንመለከት ይሆናል፡፡

የዜጎች መብት በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ

የአስተዳደር ተቋማት ወሳኔ ሲሰጡም ሆነ መመሪያ ሲያወጡ በሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉት ተጽዕኖ በሕግ የሚመራ እና ለሕግ የሚገዛ መሆን እንዳለበት ከላይ በመግቢያው ያየን ሲሆን ጉዳዩ የፍርድ ቤት ክለሳንም ይጨምራል፡፡ በመሆኑም ዜጎች የሚከተሉት መብቶች አሏቸው፡-

መመሪያን በተመለከተ

መመሪያ እንዲወጣ የመጠየቅ መብት

ማንኛውም ሰው መብቱን ወይም ጥቅሙን በሚመለከት የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ያላወጣ ቢሆንም የአስተዳደር ውሳኔ እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት ያለው ስለመሆኑ በፌደራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ አንቀጽ 4(3) ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ እንዲሁም አንድ የአስተዳደር ተቋም ሊያወጠው የሚገባውን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ሳያወጣ ቢቀር መመሪያውን እንዲያወጣ ማንኛውም ሰው በጽሁፍ መጠየቅ ይችላል (አንቀጽ 6)፡፡

አስተያየት የመስጠት መብት

አንድ የአስተዳደር ተቋም በአዋጁ አንቀጽ 8 መሠረት በሚያቀርበው ረቂቅ መመሪያ ላይ ዜጎች አስተያየት የመስጠት መብት አላቸው፡፡

የመሳተፍ መብት

የአስተዳደር ተቋሙ በመመሪያው ረቂቅ ላይ የጽሁፍ አስተያየት ከበቃ በኋላ መመረያው ከመጽደቁ በፊት በሚያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዜጎች የመሳተፍ መብት አላቸው (አንቀጽ 10(1))፡፡

መመረያውን የማግኘት መብት

በአዋጁ አንቀጽ 17(3) መሠረት ማንኛውም የመመሪያውን ቅጂ ማግኘት የሚፈልግ ሰው መመሪያውን ባለበት ሁኔታ የመመልከት ወይም ወጪውን ሸፍኖ ከአስተዳደር ተቋሙ የማግኘት መብት አለው፡፡

የአስተዳደር ውሳኔን በተመለከተ

አቤቱታ የማቅረብ መብት

የአስተዳደር ውሳኔ እንዲሰጥ የሚቀርብ ጥያቄን ዜጎች በራስ ወይም በተወካይ አማካኝነት የማቅረብ መብት ያለቸው መሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 20 ተደንግጓል፡፡

የመደመጥና የመሰማት መብት

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠው ሰው የአስተዳደር ወሳኔ ከመስጠቱ በፊት የሚመለከተውን ሰው ፍሬ ነገር እና ማስረጃ በሚገባ ማዳመጥ እና መመርመር እንዲሁም እንደነገሩ ሁኔታ የሦስተኛ ወገን ተቃዋሚን እና የሕዝብን አስተያየት ማድመጥ አለበት (አንቀጽ 28)፡፡ ማንኛውም አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ጉዳዩ በሚገባ መሰማት አለበት (አንቀጽ 36) ፡፡

የእኩልነት መብት

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 25 ላይ ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑ ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም በፌደራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አንቀጽ 32 የአስተዳድ ውሳኔ የሚሰጠው ሰው ሁሉንም ተገልጋዮች በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት መጠን፣ በትውልድ ሁኔታ ወይም በሌላ ምክንያት ልዩነት ሳያደርግ መወሰን እንዳለበት ደንግጓል፡፡

የአስተዳር ውሳኔውን የማግኘት መብት

በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ አንቀጽ 39 ላይ በተደደነገገው መሠረት ማንኛውም የአስተዳደር ውሳኔ ከነምክንያቱ ለተገልጋዩ በጽሁፍ መሰጠት አለበት፡፡

ቅሬታ የማቅረብ መብት

ማንኛውም ሰው በተላለፈበት የአስተዳደር ውሳኔ ላይ ለአስተዳደር ተቋሙ ቅሬታ የማቅረብ መብት አለው (አንቀጽ 43)፡፡ የአስተዳደር ተቋሙ የሰጠውን ውሳኔ በአዋጁ አንቀጽ 47 መሠረት ወዲያውኑ ለቅሬታ አቅራቢው በጽሁፍ መስጠት አለበት፡፡

የውሳኔ እገዳ ጥያቄ የማቅረብ መብት

ዜጎች ለአስተዳደር ተቋሙ ማንኛውንም ሕጋዊ አቤቱታ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡ የአስተዳደራዊ ውሳኔ ወዲያውኑ መፈፀም በመብቱ ወይም በጥቅሙ ላይ የማይመለስ ጉዳት የሚያደረስበት ሰው ውሳኔው እንዲታገድለት ውሳኔውን ለሰጠው ተቋም አቤቱታ ማቅረብ ይችላል (አንቀጽ 41)፡፡

በፍርድ ቤት የሚደረግ የአስተዳደር መመረያዎች እና ውሳኔዎች ክለሳ

  • የክለሳ አቤቱታ የማቅረብ መብት
  • ማንኛውም ጉዳዩ የሚመለከተው ሰው የአስተዳደር መመሪያ በፍርድ ቤት እንዲከለስ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡ እንዲሁም ማንኛውም በአስተዳደር ውሳኔ ጥቅሙ የተነካበት ሰው ውሳኔው በፍርድ ቤት አንዲከለስ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል (አንቀጽ 48)፡፡
  • የአስተዳደር መመሪያ ወይም ውሳኔ እንዲከለስ አቤቱታ የሚቀርበው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔም የመጨረሻ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የአስተዳደር መመሪያን በተመለከተ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለቀርብበት ይችላል (አንቀጽ49)፡፡
  • የአስተዳደር መመሪያ በፍርድ ቤት የሚከለሰው በሶስት ምክንያቶች ሲሆን ይህም
    • በአዋጁ የተመለከቱትን የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች ሳይከተል የወጣ መሆኑ ሲረጋገጥ፣
    • ከተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ የወጣ ሲሆን
    • ከመመሪያ በላይ ከሆኑ ሌሎች ሕጎች የሚቃረን ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡

በሌላ በኩል የአስተዳደር ውሳኔ የሚከለሰው በአዋጁ የተደነገጉትን መርሆዎች የጣሰ ሲሆን ነው (አንቀጽ 50 (1 እና2) ፡፡

ቅሬታው መመሪያው ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር በ90 ቀናት ጊዜ ውስጥ መቅረብ የሚገባው ሲሆን የአስተዳደር ውሳኔን የተመለከተ ከሆነ ውሳኔ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የ30 ቀናት ጊዜ ውስጥ መቅረብ እንዳለበት ተመላክቷል፡፡ ነገር ግን የክለሳ ምክንያት የሆነው ከአስተዳደር ተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ የወጣ መመሪያ ሲሆን ወይም የወጣው መመሪያ በእርከን ከመመረያ በላይ ከሆኑ ሌሎች ሕጎች የሚቃረን ሲሆን የአስተዳደር መመሪያው በፍርድ ቤት እንዲከለስ የሚቀርብ አቤቱታ በማናቸውም ጊዜ ሊቀርብ ይችላል (አንቀጽ 53)፡፡

የጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት

ከአስተዳደር መመሪያ ወይም ውሳኔ ጋር በተያያዘ ጥፋት ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም ሰው መመሪያውን ያወጣው ወይም ውሳኔ የሰጠው የአስተዳደር ተቋም አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ካሳ እንዲከፍለው የመጠየቅ መብት አለው፡፡

የመንግሥት ግዴታ (ኃላፊነት) በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ

መንግስታት ለዜጎች መብቶች ተፈፃሚነት ከፍተኛ ሚና እና ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን ኃላፊነታቸውን ወይም ያለባቸውን ግዴታ በዋናነት የማክበር፣ የመጠበቅ እና አስቻይ ሁኔታዎችን የሟሟላት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም በፌዴራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ለዜጎች አገልግሎት የመስጠት፣ ቅሬታ ሲቀርብ የመፍታት፣ የእኩልነት መብት እና ሌሎችን መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታዎች መንግሥት ያሉበት ሲሆን በአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጁ የሚከተሉት በተጨማሪነት በግልጽ ተደንግገው እናገኛለን፡፡

  • መረጃ የመስጠት ግዴታ
  • ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም ከመመሪያ ማውጣት ወይም ከአስተዳደር ውሳኔ መስጠት እና እነዚህን ከመፈፀም ጋር በተያያዘ በሌላ ሕጋዊ አካል ሲጠየቅ መረጃ የመሰጠት ግዴታ አለበት (አንቀጽ 60)
  • የአስተዳደር ጉዳይ ችሎት ማደራጀት
  • የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክለሳ አቤቱታዎችን የሚያስተናግድ የአስተዳደር ጉዳይ ችሎት የመደራጀት ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ለተደነገጉት የዜጎች መብቶች ተፈፃሚነት በሁሉም ደረጃ ያሉ የፌደራል መንግሥት አካላት፣ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ዜጎችም መብትና ግዴታ የማይነጣጠሉ እንደመሆናቸው መብትና ግዴታቸውን ተረድተው መብታቸውን መጠየቅና ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ