ንግድ በርካቶች የኑሯቸው መሠረት ያደረጉት የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ ይህም በግለሰብ ነጋዴ ደረጃ እንዲሁም አንድ ላይ በመሆን የንግድ ሥራ ለማከናወን የተስማሙ ሰዎች በሚመሰርቷቸው የንግድ ማህበራት ሊከናወን ይችላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የንግድ ማህበራትን ምንነት፣ በሀገራችን እውቅና ያላቸው የንግድ ማህበርን እንዲሁም መሠረታዊ ባህሪያቸውን በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
የንግድ ማኅበር ምንነት
በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 172 መሠረት የንግድ ማኅበር ማለት ሰዎች መዋጮ አዋጥተው በሕብረት በኢኮኖሚያዊ እንቀስቃሴ በመሰማራት ከሚገኘው ትርፍ ተካፋይ ለመሆን በመመስረቻ ጽሁፍ አማካኝነት የሚያቋቁሙት ማኅበር ነው፡፡ የንግድ ማህበራት አንድና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን አዋጥተው በጋራ ለመሥራት ተስማምተው የሚመሰርቱት የንግድ ድርጅት አይነት ነው፡፡ የንግድ ማኅበር የንግድ ማኅበር ለመመስረት በሚዘጋጅ መመስረቻ ጽሁፍ የሚመሠረት ሲሆን ይህም በንግድ ማኅበር አባላት መካከል የሚደረግ የስምምነት ሰነድ ነው፡፡
የንግድ ማኅበራት አይነቶች
በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 174 መሠረት ሰባት ዓይነት የንግድ ማኅበራት አሉ፡፡ እነሱም
- የሕብረት ሽርክና ማኅበር (general partnership)
- ሁለት አይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበር (limited partnership)
- ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር (limited liability partnership)
- የእሽሙር ማህበር (joint venture)
- የአክሲዮን ማህበር (share company)
- ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (private limited company) እና
- ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (one-person private limited company) ናቸው፡፡
እነዚህ ማህበራት ከምስረታቸው ጀምሮ በማህበራቱ አባላት መካከል የሚኖረው ግንኙነት እንዲሁም ከሶስተኛ ወገኖች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እንደየማህበሩ አይነት የተለያየ መሆኑን ከንግድ ህጉ መረዳት ይቻላል፡፡
የንግድ ማኅበራት መሠረታዊ ባህርያት
የንግድ ማኅበራት መሠረታዊ ባህርያት አስመልክቶ በሕጉ ውስጥ ተደንግጓል፡፡ ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ የሕግ ሰውነት እና ዘለቄታዊነት ናቸው፡፡
የሕግ ሰውነት
በአዲሱ የንግድ ሕግ በአንቀጽ 175 ከእሽሙር ማኅበር በስተቀር ሁሉም የንግድ ማኅበራት በንግድ መዝገብ እንደተመዘገቡ የሕግ ሰውነት እንደሚያገኙ ደንግጓል፡፡ አንድ የንግድ ማኅበር የሕግ ሰውነት አለው ሲባል ማኅበሩ ከአባለቱ የተለየ የራሱ ህልውና፣ ንብረት፣ መብትና ግዴታ አለው ማለት ነው፡፡ በሕግ ሥርዓት ውስጥ የንግድ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ብዙ ድርጅቶች የሕግ ሰውነት እንዳላቸው በሕግ ሊደነገግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራት ወዘተ…የሕግ ሰውነት አላቸው፡፡ የሕግ ሰውነት ዋናው ዓላማ አንድን ግዙፍነት የሌለው ተቋም ህይወት እንዳለው በመቁጠር የራሱ መብት፣ ንብረት፣ ግዴታ ወዘተ.. ባለቤት ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ ሰዎች አባላት የሆኑበት ማኅበር በአንድ ስያሜና በአንድ ውክልና እንዲሰራ ያስችላል፡፡
ዘለቄታዊነት /Perpetuity/
ዘለቄታዊነት የሚለው አገላለጽ የምንጠቀመው የንግድ ማኅበር ከመስራቾች እድሜ በላይ የሚቆይበትን ሁኔታ ለመግለፅ ሲሆን ዘለቄታዊነት የሕግ ሰውነት የማግኘት ውጤት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የንግድ ማኅበር መስራቾቹ ካለፉ በኋላም ይቀጥላል፡፡ መስራች ያልፋል፣ ባለአክስዮንም ያልፋል፣ የንግድ ማኅበሩ ህልውና ግን ይዘልቃል፡፡ ይህ ባህሪው የንግድ ማኅበርን ከግል ንግድ የሚለየው ዋናው መገለጫ ነው፡፡ የግል ንግድ ባለቤቱ ሲያልፍ አብሮ ያልፋል፣ በውረስ ካልተላለፈ በቀር በውርስ ሊተላለፍም ወራሾች በራሳቸው ስም ይነግዳሉ እንጂ በበፊቱ እንደነበረ አይቀጥልም፡፡
የንግድ ማህበራት ትርጓሜና አይነት ከላይ የተገለፀው ሲሆን የንግድ ማህበር የሚመሰርቱ ሰዎች የሚመሰርቱትን የንግድ ማህበር አይነትና የሚያስከትለውን ውጤት ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ተዘጋጀ