ይግባኝ በወንጀል ጉዳይ

ማውጫ

Share this Article

ይግባኝ ማለት ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ያየው ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ ጥፋተኛ መሆኑን በመፍረዱ፣ ለጊዜው የመለቀቅ ወይም ነፃ የመለቀቅ ፍርድ በመስጠቱ በፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ፍርድ ወይም ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወገን በሥልጣን እርከን ከፍ ወዳለው እና ይግባኙን ለማየት ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ቅሬታ የሚያቀርብበት ሥርዓት ነው። የይግባኝ መብት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ አንዱ የመብት ማስከበሪያ መንገድ ነው። የይግባኝ መብት በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች፣ በሀገራችን ከህገ መንግሥት እንዲሁም በሌሎችም ህጎች እውቅና ያገኘ መሠረታዊ መብት ነው። የህገ መንግስቱ አንቀጽ 20(6) መሠረት የተከሰሱ ሰዎች ክርክሩ በሚታይበት ፍርድ ቤት በተሰጠባቸው ትእዛዝ ወይም ፍርድ ላይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት አላቸው። በተጨማሪም የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲው ማንኛውም ሰው በወንጀል በተከሰሰበት ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤት በሰጠው ትእዛዝ ወይም ፍርድ የሕግ ወይም የፍሬ ነገር ስህተት አለ ብሎ ካመነ ቅሬታውን በሕግ ተለይቶ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በይግባኝ ለማየት ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችል ያስቀምጣል።

ፖሊሲው እንደሚያስቀምጠው ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ የሚጠይቀው የተሰጠው ትእዛዝ ወይም ውሳኔ የሕግ ወይም የፍሬ ነገር ስህተት ካለው እና በጉዳዩ ላይ ይግባኝ ባይቀርብበት የሕዝብ ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ካመነ ነው። የይግባኝ ሥርዓት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ የሚመራ ሲሆን ወንጀል ጉዳይ ይግባኝ ከጥፋተኝነት ውሳኔ በተጨማሪ በቅጣት መጠን ላይ ቅጣቱ በዝቷል ወይም ያንሳል በማለት በተከሳሽ ወይም በዐቃቤ ሕግ ሊጠየቅ ይችላል። በዚህ አጭር ጽሁፍ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህጉ ይግባኝን በተመለከተ የተካተቱ ጉዳዮችን እንመለታለን።

በወንጀል ጉዳይ ይግባኝ የሚቀርብባቸው ሁኔታዎች

የወንጀል ጉዳይ ክርክር የሚደረገው የወንጀል ተጎጂን በመወከል በዐቃቤ ሕግ እና ወንጀል በመፈፀም በተጠረጠረ ተከሳሽ መካከል ሲሆን ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ወይም ተከሳሽ ቅሬታ ሊኖራቸው ይችላል። ይህም ቅሬታ በተከሳሽ የሚቀርብ ከሆነ የተወሰነብኝ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተገቢ አይደለም ወይም የተላለፈብኝ ቅጣት ተገቢ አይደለም ወይም ተመጣጣኝ አይደለም በማለት ሊቀርብ የሚችል ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ደግሞ ተከሳሽ በነፃ በመለቀቁ ወይም ዝቅተኛ ቅጣት በመወሰኑ ቅሬታ ካለው ይግባኝ ማለት ይችላል። እንዲሁም ከሳሽም ይሁን ተከሳሻ የዋስትና መፈቀድ ወይም መከልከል ላይ፣ የዋስትና መጠን መብዛት ወይም ማነስ ላይ ይግባኝ ሊሉ ይችላሉ። በመሆኑም ከሳሽም ይሁን ተከሳሽ ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤት በሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ወይም ውሳኔ ላይ ቅሬታ ካለው ይግባኝ ማለት ይችላል።

ይግባኝ ማለት የማይቻልባቸው ሁኔታዎች

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህጉ ቁጥር 184 እንደተደነገገው በሥነ -ሥርዓት ሕግ ቁጥር 94 መሠረት ቀጠሮ መስጠት ወይም አለመስጠት ወይም በቁጥር 131 መሠረት ስለሚቀርብ መቃወሚያ ወይም በቁጥር 146 መሠረት ማስረጃን ስለ መቀበል ወይም ስላለመቀበል ፍርድ ቤት በሚሰጠው ትእዛዝ ላይ ይግባኝ ለማለት አይቻልም። ይሁንና የጥፋተኘነት ውሳኔ በተሰጠበት ለጊዜው በመለቀቅ ወይም ነፃ በመልቀቅ ፍርድ ተሰጥቶ ይግባኝ በተባለበት ጊዜ እነዚህ የተሰጡት ትዕዛዞች ይግባኝ ለማለት ምክንያቶች ለመሆን ይችላሉ።

የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት ወይም በቅጣቱ ይግባኝ ስለማለት

የተፈረደበት ሰው በጥፋተኛነት ውሳኔና በቅጣቱ ላይ ይግባኝ ማለት ይችላል። ነገር ግን ተከሳሽ የተከሰሰበትን ወንጀል ያመነ ሆኖ በእምነቱ መሠረት ጥፋተኝነቱ ከተወሰነ በኋላ ስለቅጣቱ ልክ ወይም ቅጣቱ ህጋዊ ላለመሆኑ ይግባኝ ማለት እንጂ የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት ላይ ይግባኝ ማለት አይችልም። ዐቃቤ ህጉ ወይም የግል ከሳሹ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ለጊዜው በመልቀቅ ወይም ነፃ በመልቀቅ ፍርድ ላይ ወይም ቅጣቱ በቂ አይደለም በማለት ይግባኝ ማለት እንደሚችል በሥነ-ሥርዓት ህጉ ቁጥር 185 ስር ተደንግጎ ይገኛል።

የጉዳት ካሳ ላይ ይግባኝ ስለማለት

በወንጀል ድርጊት ሳቢያ ለደረሰበት ጉዳት ፍርድ ቤቱ ካሳ ማግኘት አይገባውም ብሎ የፈረደ እንደሆነ የተበደለው ወገን በውሳኔው ይግባኝ ለማለት ይችላል። እንዲሁም ፍርድ ቤቱ የተበደለው ሰው ካሣ መቀበል ይገባዋል ብሎ በፈረደ ጊዜ ተከሳሽ በውሳኔው ይግባኝ ማለት ይችላል። ይግባኝ ሲባል የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት ወይም በቅጣቱ ውሳኔ ይግባኝ ሲቀርብ ይግባኙን የሚሰማው የወንጀል ይግባኝ ፍርድ ቤት ሲሆን የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት ወይም ስለ ቅጣቱ ይግባኝ ባልተባለ ጊዜ ወይም ይግባኙ በተተወ ጊዜ የካሳው ፍርድ ይግባኝ የፍትሐ ብሄር ይግባኝ ችሎት እንደሚሰማ የሥነ-ሥርዓት ህጉ ቁጥር 186 ስር ተደንጋጓል።

ይግባኝ ማለትን ስለማስታወቅና የይግባኝ ማመልከቻ

ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው ይግባኝ ማለቱን ለማስታወቅ የሚፅፈውን ማመልከቻ ፍርድ በተሰጠ በ15(አስራ አምስት) ቀናት ውስጥ ማቅረብ ያለበት ሲሆን ይግባኝ ማለቱን ለማስታወቅ የፃፈው ማመልከቻ ለፍርድ ለሬጂስትራሩ ሲደርሰው ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ አስገልብጦ ለይግባኝ ባዩ ወይም ለጠበቃው ይሰጠዋል። ይግባኝ ባዩ በእስር ቤት ያለ እንደሆነ ለይግባኝ ባዩ እንዲሰጥ ለማረሚያ ቤቱ ሹም ይልካል። ይግባኝ ባይም የፍርድ ግልባጭ በደረሰው በ30 (ሰላሳ ) ቀናት ውስጥ ፍርዱን ለሰጠው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ማቅረብ እንዳለበት የሥነ-ሥርዓት ህጉ ቁጥር 187/2 ይደነግጋል። በመጨረሻም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይግባኙን ከተቀበ መልስ ሰጪ የቀረበውን ይግባኝ ተረድቶ መልስ መስጠት እንዲችል የይግባኙ ማመልከቻ ግልባጭ ለመልስ ሰጪው እንዲደርሰው መደረግ አለበት።

ፍርድ እንዳይፈፀም ስለ ማገድ

ጥፋተኛ ሆኖ የተፈረደበት ይግባኝ ባይ የይግባኝ ማስታወቂያ የሰጠ እንደሆነ ይግባኙ ሳይሰማ ወይም ይግባኙን ይግባኝ ባዩ ካልተወ በቀር ይግባኙ እስኪወሰን ድረስ በዋስትና የተለቀቀ እንደሆነ የእስራት ቅጣቱ የይግባኝ ፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ አይጀምርም። ይሁንና ይግባኝ የተባለበት ፍርድ ቤት እንዲፈፀም ለጥንቃቄ የሰጣቸው ትዕዛዞች ይግባኝ የተባለባቸው ቢሆንም መፈፅም አለባቸው። ስለ ካሣ ወይም ስለ ኪሳራ ወጪ የተሰጠ ፍርድ ከመፈፀም የማይታገድ ሲሆን ይግባኝ ከመሰማቱ በፊት በማናቸውም ጊዜ ወይም ይግባኙ በሚሰማበት በማናቸውም ጊዜ ፍርዱ እንዲታገድ ለይግባኝ ፍርድ ቤት ማመልከት እንደሚቻል በሥነ-ስርዓት ህጉ ቁጥር 187/4 እና 5 ስር ተደንግጓል።

የይግባኝ ማመልከቻ ይዘት እና ለይግባኝ ፍርድ ቤት ስለሚላኩ መረጃዎች

የይግባኝ ማመልከቻ ይግባኝ በተባለበት ፍርድ ላይ ያሉትን እና እንዲታረሙለት የሚፈልጋቸውን ዋና ዋና የቅሬታ ነጥቦች ለይቶ በክርክር መልክ ሳይተች በዝርዝር ማቅረብ ያለበት ሲሆን ከይግባኝ ማመልከቻው ጋር ይግባኝ የተባለበት ፍርድ ግልባጭ መቅረብ አለበት። ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት የይግባኝ ማመልቻ እንደ ደረሰው ከ15 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የመዝገቡን ግልባጭና የይግባኝ መዝገብ ይግባኝ እላለሁ ሲል ያስታወቀበትንም ከይግባኙ ማመልከቻ ጋራ መረጃዎችም ጭምር ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት መላክ አለበት። የመዝገቡን መገልበጥ የነገሩን በይግባኝ መታየት የሚያዘገየው ሲሆን ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የመዝገቡ መገልጥ እንዲቀር በማድረግ ዋናው መዝገብ በትውስት እንዲቀርብለት ለማድረግ ይችላል።

የይግባኝ ጊዜ ካለፈ በኋላ ይግባኝ ለማቅረብ የሚቀርብ ማመልከቻ

ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት የይግባኙን ማስታወቂያ ወይም ማመልከቻ ጊዜው ካለፈ በኋላ በመቅረቡ ምክንያት አልቀበልም ያለ እንደሆነ ይግባኝ ባዩ የይግባኝ ጊዜ ካለፈ በኋላ ይግባኙን ለማቅረብ እንዲፈቀድለት ማመልከቻውን በጽሑፍ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ይደረጋል። በመሆኑም የይግባኙ ጊዜ ማለፉን የሚያውቅ ይግባኝ ባይ አስቀድሞ ይግባኙን ሲያቀርብ ጊዜው ካለፈ በኋላ ይግባኝ እንዲል እንዲፈቀድለት ማመልከቻውን ከይግባኙ ጋር ቢያቀርብ የተሻል ጉዳዩን በፍጥነት እንዲጨርስ ይረዳዋል። ይግባኝ ባይ በሚያቀርበው ማመልከቻም የይግባኙ ጊዜ ካለፈ በኋላ ነገሩ ሊሰማ ይገባል የሚልበትን አሳማኝ ምክንያት ገልፆ ማስረዳት ያለበት ሲሆን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የይግባኙ ጊዜ ያለፈው በአመልካቹ ጥፋት ባልሆነ ምክንያት መሆኑ ካላመነበት በቀር ጊዜው ያለፈ ይግባኝ እንዲሰማ አይፈቅድም።

ይግባኝ በሚሰማበት ቀን ከባለጉዳዮች አንዱ ስላለመቅረቡ

ይግባኝ እንዲሰማ በተቀጠረበት ቀን ይግባኝ ባዩ ይግባኙን በማስረዳት የሚጀምር ሲሆን መልስ ሰጪም መልስ ይሰጣል። ይግባኝ ባዩም የመልስ መልስ የመስጠት መብት አለው። ይህ እንዳለ ሆኖ ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው የይግባኙ ቀን ተነግሯቸው በተወሰነው ቀን ያልቀረቡ እንደሆነ ይግባኙ ይሰረዛል። ነገር ግን ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሳይቀርብ መቅረቱን ማስረዳት የቻለ እንደሆነ ይግባኙ እንዲሰማ ማድረግ ይቻላል። በሌላ በኩል መልስ ሰጪው ወይም ጠበቃው ያልቀረቡ እንደሆነ ጉዳዩ በሌሉበት መሰማቱን ይቀጥላል።

የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሥልጣን

ይግባኙ በሚሰማበት ጊዜ በነገሩ ውስጥ ለመግባት በቂ ምክንያት የሌለ መስሎ ከታየው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይግባኙን ያሰናብተዋል። በነገሩ ለመግባት በቂ ምክንያት ያለ በመሰለው ጊዜ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሚከተሉትን እንደሚፈፅም በቁጥር 195 ስር ተደንግጓል።

ተከሳሹ ነፃ በመልቀቅ ወይም ለጊዜው በመልቀቅ በተሰጠ ትእዛዝ ይግባኝ የተባለ ሲሆን ትዕዛዙን ሰርዞ ሥልጣን ያለው ሌላ ፍርድ ቤት ነገሩን እንደ ገና እንዲያይ ማዘዝ ወይም ጥፋተኛ ነው ብሎ እንደ ህጉ ሊፈርድበት ይችላል ወይም

ይግባኝ የቀረበው ጥፋተኛ ነው በተባለበት ውሳኔ እና በቅጣት ላይ ከሆነ

  • ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔና ቅጣቱን ሰርዞ ተከሳሹን በነፃ ሊለቅ ወይም
  • ፍርዱን ለውጦ ወይም ሳይለውጥ ቅጣቱን ሊያፀናል፣ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል።
  • ይግባኝ የቀረበው ጥፋተኛ ነው በተባለበት ውሳኔ ላይ ብቻ ከሆነ ፍርዱና ቅጣቱን ሰርዞ ተከሳሹን በነፃ ሊለቅ ይችላል።

ይግባኝ የቀረበው በቅጣቱ ላይ ብቻ ከሆነ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ቅጣቱን ሊያፀና፣ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል።

በሥነ-ሥርዓት ህጉ ቁጥር 195/3 ስር እንደተደነገገው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ አፅንቶ ቅጣቱን የለወጠ እንደሆነ ወይም ቅጣቱን አፅንቶ ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ የለወጠ እንደሆነ ጥፋተኛ ነው በተባለበት ወይም ቅጣቱ እንዲለወጥ በተወሰነው ላይ ብቻ ሁለተኛ ጊዜ ይግባኝ ለማለት ይቻላል።

በሌላ በኩል ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የቀረበው ይግባኝ ስለ ተፈረደባቸው ብዙ ሰዎች የሚመለከት ሆኖ ይግባኝ ያለው ግን አንድ ሰው ብቻ በሆነ ጊዜ በይግባኝ የተሰጠው ፍርድ ይግባኝ ባዩን የሚጠቅም በሆነ ጊዜ እና ተከሳሾቹ ይግባኝ ቢሉ ኖሮ በፍርዱ እነሱም ሊጠቀሙ ይችሉ ነበር የሚያሰኝ ሲሆን የይግባኙ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ፍርድ ይግባኝ ላላሉት ሰዎች ይግባኝ እንዳሉ ተቆጥሮ ይፈፀምላቸው ለማለት እንደሚችል በሥነ-ሥርዓት ህጉ ቁጥር 196/1 ሥር ተደንግጓል። ይሁንና ይግባኝ ባዩ ላይ ጉዳት የሚያመጣበት እንደሆነ ይግባኝ ባላሉ ሰዎች ላይ አይፈፀምም።

በአጠቃላይ በወንጀል ጉዳይ የሚቀርብ ይግባኝ በመጀመሪያ ደረጃ ጉዳዩን አይቶ ፍርድ ወይም ውሳኔ በሰጠው ፍርድ ቤት ፍርድ ወይም ውሳኔ ላይ የሚቀርብ ቅሬታ ሲሆን ይህም በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ወይም በተከሳሽ ሊቀርብ ይችላል። ይግባኝ በስር ፍርድ ቤት የተሰራን የሕግ ወይም የፍሬ ነገር ስህተት ለማረም የሚረዳ መሠረታዊ መብት በመሆኑ በፍርድ ቤት የመጨረሻ ፍርድ ወይም ውሳኔ ቅር የተሰተኘ ወገን ቅሬታውን በይግባኝ ለማቅረብ ይችላል።

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ