ጉዲፈቻ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ልጅ ወልዶና አሳድጎ ለወግ ለማእረግ ማብቃት የብዙ ሰዎች ህልምና ፍላጎት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ልጅ ለመውለድ ያልቻሉ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች የማደጎ ልጅ በመውሰድ ልክ እንደ ልጃቸው ተንከባክበው በማሳደግ የልጅ ፍላጎታቸውን ሲያሳኩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የማደጎ ልጅ ወይም ሕፃን ልጅን በጉዲፈቻ ወስዶ ማሳደግ ልጅ መውለድ ያልቻሉ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ የተፈጥሮ ልጅ ያላቸውም ቢሆኑ የኢኮኖሚ አቅሙና ችሎታ እስካላቸው ድረስ የማሳደግ አቅም ከሌላቸው ወላጆች ወይም ወላጅ አልባ የሆኑ ሕፃናትን ወስደው ያሳድጋሉ፡፡ ይህ በጎ ተግባር በተለይም ከሕፃናቱ የተሻለ ደኅንነት አንፃር ሲታይ ሁለንትናዊ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው፡፡

የጉዲፈቻን ታሪካዊ አመጣጥ ስናይ ከጥንታውያን ሮማውያንና ባቢሎናውያን ዘመን ጀምሮ እራሱን የቻለ የሕግ ድንጋጌዎች የነበሩት መሆኑን ረ/ፕሮፌሰር ነጋ እውነቴ “በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው መፍቀድ አስፈላጊነት” በሚለው ፅሑፋቸው አስፍረዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት ጉዲፈቻ ብዙ ዘመን ያስቆጠረ ማሕበራዊ እሴትና በብዙ ሀገራት የሚተገበር መሆኑንም መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ ስለ ጉዲፈቻ ምንነት፣ ቅድመ ሁኔታዎቹ እና የሚያስከትለው ውጤት ከተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አንፃር ይዳሰሳል፡፡

የጉዲፈቻ ምንነትና ፋይዳ

የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕጉ ጉዲፈቻን እንደ አንድ የዝምድና መፍጠሪያ ሥርዓት በመውሰድ “በአንድ ሰውና በአንድ ልጅ መካከል በሚደረግ ስምምነት የጉዲፈቻ ዝምድና ሊፈጠር ይችላል” ካለ በኋላ በውጤት ደረጃም በጉዲፈቻ ምክንያት የሚፈጠረው ዝምድና ልክ ከአብራክ እንደተፈጠረ ልጅ ዓይነት እንደሆነ ደንግጓል (የተሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 180 እና 181)፡፡ ጉዲፈቻ የሚለው ቃል ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀጥታ ወደ አማርኛ የተወሰደ እንደሆነና ትርጓሜውም ከሌላ ሰው አብራክ የተወለደን ልጅ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ ጥቅሙን ጠብቆ እንደ አብራክ ክፋይ ልጅ ማሳደግ ማለት ነው ሲሉ የሚገልፁት ፀሐፍያንም አሉ።

ጉዲፈቻ ከሕፃኑም ከጉዲፈቻ አድራጊውም አንፃር ቢታይ በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ማሕበራዊ እሴት ነው፡፡ ከሕፃኑ የወደፊት እጣ ፋንታ አንፃር ስንመለከተው በተለይም ወላጅ አልባ የሆኑ ሕፃናት ያለአሳዳጊ እንዳይቀሩ በማድረግ ቀጣይ ሕይወታቸው የተቃና እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ከጉዲፈቻ አድራጊው ወገንም ስናየው የአብራካቸው ክፋይ ልጅ የሌላቸው ሰዎች በሚያረጁበት ጊዜ ያለ ጧሪና ቀባሪ እንዳይቀሩ የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡

ጉዲፈቻ ለማድረግ ሊሟሉ የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች

የቤተሰብ ሕጉ የጉዲፈቻ ሥርዓት አፈፃፀም መሠረታውያንን ማለትም የዕድሜ ገደብ፣ የስምምነት አሰጣጥ፣ የባለድርሻ አካላትን (የሕፃናት አሳዳጊ ድርጅቶችና የሕፃናትን ጉዳይ የሚመለከተውን የመንግሥት አካልና የፍርድ ቤቶችን) ሚና በዝርዝር ደንግጓል፡፡

የመጀመሪያው መመዘኛ የዕድሜ ገደብ ሲሆን የጉዲፈቻ አድራጊው ዕድሜ ቢያንስ 25 ዓመት እንዲሆን የሚጠበቅ ሲሆን ባለትዳሮች በሚሆኑበት ጊዜ የአንዳቸው ተጋቢ ዕድሜ 25 ዓመት ከሆነ የሌላኛው የግድ መሙላት አለበት አይባልም (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 184)፡፡ የዕድሜ ገደብ የተቀመጠበት ምክንያት ጉዲፈቻ አድራጊዎቹ የበሰሉና የማመዛዘን አቅማቸው ከፍ ያለ እንዲሆንና በዚህም ለጉዲፈቻ ተደራጊው ሕፃን የተሻለ ነገር እንዲያደርጉለት ከሚል መነሻ ነው፡፡ ጉዲፈቻ የሚደረገው ልጅ እድሜም ከ18 ዓመት በታች የሆነና ከሞግዚት አስተዳደር ስር ነፃ ያልወጣ መሆን እንዳለበት እንዲሁም የተፀነሰ ልጅንም እንደሚያጠቃልል ተደንግጓል (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 185 እና 187)፡፡

ሁለተኛው መመዘኛ ስምምነትን የሚመለከት ሆኖ ስምምነቱን የሚያደርጉትም ጉዲፈቻ አድራጊውና የልጁ አሳዳሪ ናቸው (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 190)፡፡ የልጁ ወላጆች በሕይወት ያሉ ከሆነ ስለጉዲፈቻው ፈቃዳቸውን መስጠት ያለባቸው ሲሆን ከሁለቱ አንዱ ፈቃዱን ለመስጠት ያልፈለገ በሚሆንበትና የልጁ ዕድሜ 10 ዓመት የሞላው ከሆነ ፍርድ ቤቱ የአንደኛውን ወላጅ ፈቃድና የልጁን አስተያየት በመጠየቅ ጉዲፈቻውን ሊያፀድቅ ይችላል (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 191)፡፡ በአንፃሩ ጉዲፈቻ አድራጊዎቹ ባለትዳሮች በሚሆኑበት ጊዜ የሁለቱም ስምምነት የግድ አስፈላጊ ሲሆን ከሁለት አንዳቸው ካልተስማሙ ጉዲፈቻ ሊደረግ አይችልም (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 186)፡፡ ከወላጆችና ከአሳዳሪዎች በተጨማሪ ወላጅ አልባ ሕፃናትን የሚያሳድጉ የመንግሥትም ሆኑ የግል ድርጅት ተቋማትም እያሳደጉ ያሉትን ሕፃናት በጉዲፈቻ መስጠት ይችላሉ፡፡ ቢሆንም እነዚህ አካላት ከመስማማታቸው በፊት የሕፃናትን ጉዳይ ለሚከታተል የመንግሥት አካል ስለልጁ ማንነት፣ በምን ሁኔታ እንደተረከበውና ስለጉዲፈቻ አድራጊው ግላዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያ አቋም መግለጫ ማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 192)፡፡

ሌላኛው መስፈርት የስምምነቱ በፍርድ ቤት መፅደቅ ሲሆን ማንኛውም የጉዲፈቻ ስምምነት በፍርድ ቤት ካልፀደቀ ተፈፃሚነት የለውም (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 194(1))፡፡ ፍርድ ቤቱ የጉዲፈቻ ስምምነቱን ከማፅደቁ በፊት እንደሁኔታው የልጁን ወይም የአሳዳሪውን አስተያየት፣ ጉዲፈቻ አድራጊው ልጁን እንደልጁ አድርጎ ለማሳደግና ለመንከባከብ ያለው ብቃት እንዲሁም ለመጠቀሚያነት እንደማያደርገው ለመገመት የሚያስችል መረጃ መኖሩን እና ጉዲፈቻ አድራጊው ከአብራኩ የተገኙ ልጆች ያሉት ከሆነ በጉዲፈቻ ልጁ መልካም አስተዳደግና ጥቅም ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ተፅእኖ ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ተደንግጓል (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 194(3) እና 188(2))፡፡

የውጭ ዜጎች ሕፃናትን በጉዲፈቻ እንዳይወስዱ ስለመከልከሉ

የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ የውጭ ሀገር ዜጎች ኢትዮጵያውያን ሕፃናትን በጉዲፈቻ እንዲወስዱ ፈቅዶ የነበረ ቢሆንም በሂደት ባጋጠሙ አንዳንድ ችግሮች ምክንያት በአዋጅ ቁጥር 1070/2010 የቤተሰብ ሕጉ እንዲሻሻልና እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ምንም እንኳን በተጨማሪ ጥናቶች መደገፍ ቢኖርበትም የውጭ ዜጎች ጉዲፈቻ እንዳያደርጉ ከተከለከሉበት ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ የውጭ ዜጎች ሕፃናቱን በጉዲፈቻ ከወሰዷቸው በኋላ ህፃናቱ ለተለያዩ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውሶች ስለሚዳረጉ ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ለባርነት ወይም ለግዴታ አገልጋይነት፣ ለወሲብ ንግድና ብዝበዛ፣ ለኢ-ሰብዓዊ አያያዝና ላልተገባ ቅጣት፣ ባሕልና ወጋቸውን በሚገባ አለማወቅና የማንነት ቀውስ ውስጥ መግባት እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ጉዲፈቻ የሚያስከትለው ውጤት

የጉዲፈቻ ውጤትን ስንመለከት ጉዲፈቻ የተደረገ ልጅ ከጉዲፈቻ አድራጊው የአብራክ ልጅ እንደሆነ ስለሚቆጠር በጥቅሉ በወላጆችና በልጆች መካከል የሚኖር ግንኙነትና ውጤት በሙሉ በጉዲፈቻ ጊዜም ተፈፃሚነት ይኖረዋል (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 181)፡፡ ይህ ማለት የጉዲፈቻ ልጅ እንደማንኛውም የተፈጥሮ ልጅ ከጉዲፈቻ ቤተሰቦቹ ጋር ህጋዊ ትስስር የሚኖረው ስለሆነ ውርስን ጨምሮ ሌሎች ህጋዊ መብቶች ይኖረዋል፡፡

ምንም እንኳን የጉዲፈቻ ልጁ የጉዲፈቻ አድራጊው ልጅ እንደሆነ የሚቆጠር ቢሆንም ከተፈጥሮ ወላጆቹ ጋር የነበረውን ዝምድናና ትስስር ይዞ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ሆኖም አስገዳጅ ሁኔታ ቢፈጠርና ከሁለት አንዱን መምርጥ ካለበት ከተፈጥሮ በተሰቦቹ ይልቅ የጉዲፈቻ ቤተሰቦቹ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ህጉ ደንግጓል (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 183)፡፡

የጉዲፈቻ አድራጊው ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆችን ወይም ወደ ጎን የሚቆጠሩ ዘመዶችን በሚመለከት ጉዲፈቻውን በግልጽ የተቃወሙና ይህንን ተቃውሟቸዉን የጉዲፈቻ ስምምነቱ በፍርድ ቤት መጽደቁን ባወቁ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በፍርድ ቤት መዝገብ ካስመዘገቡ የጉዲፈው ስምምነት ወይም ዝምድና በእነሱ ላይ ውጤት አይኖረውም (የተ/ፌ/ቤ/ሕ.አ. 182)፡፡

በመርህ ደረጃ ጉዲፈቻ አንዴ ከተደረገ በኋላ ሊሰረዝ አይችልም፡፡ ነገር ግን ጉዲፈቻ የሚደረገው በዋናነት የሕፃኑን የተሻለ እጣ ፋንታ በማሰብ በመሆኑና ይህንን የሚቃረኑ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በተለይም የጉዲፈቻ ልጁን በባርነት ሁኔታ የተያዘ ሲሆን፣ ከግብረ ገብ ውጪ በሆኑ ተግባራት እንዲሰማራ ከተደረገ፣ ወይም በማንኛውም ሁኔታ የልጁን የወደፊት ሕይወት ክፉኛ በሚጎዳ አኳኋን የተያዘ ከሆነ በህጉ አንቀጽ 195 መሠረት በፍርድ ቤት ውሳኔ ሊሰረዝ እንደሚችል፡፡

ማጠቃለያ

ጉዲፈቻ ሰዎች ያልወለዱትን ልጅ እንደወዱት ልጅ ተቀብለው የሚያሳድጉበት ማኅበራዊ እሴት እንደመሆኑ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ እና ለጉዲፈቻ አድራጊውም ሆነ በጉዲፈቻ ለሚያድገው ልጅ ጠቃሚ እንዲሆን ህጉን ተከትሎ ሊፈፀም ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህተርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ