የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ዜጎች ሰላምና ደህንነታቸው ተጠብቆ መብትና ነጻነታቸው ተከብሮ የመኖር መብት አላቸው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ማስጠበቅ እንዲሁም የዜጎችን መብትና ደኅንነት ማስከበር የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ከሰላምና ደኅንነት ጋር በተያያዘ የጦር መሳሪያ አጠቃቀም የሚነሳ እንደመሆኑ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን የሚመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ በሀገራችን የጦር መሳሪያ አያያዝ የሚመራበትን የሕግ አግባብ እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ ያለውን የሕግ ተጠያቂነት እንዳስሳለን፡፡

የጦር መሳሪያ ምንነት

የጦር መሳሪያ ማለት በአስነሺ ኃይል የሚፈነዳ ወይም በፍንዳታ ኃይል ጥይትን፣ አረርን፣ ቦምብን፣ ፈንጂን፣ ሚሳይልን፣ ሮኬትን እና ማናቸውም ተተኳሽ ነገር በማስፈንጠር በሕይወት፣ በአካል ወይም በንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መሳሪያ ሲሆን ጥይትን እና ተያያዥነት ያላቸውን አባሪዎችን የሚጨመር መሆኑን አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 2(2) ሥር ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ አባሪዎችን የተባሉት የመሳሪያ መያዣን፣ ማንገቻን፣ መለዋወጫ፣ ማፅጃ፣ መጠገኛ እንዲሁም የጥይት መያዣ መጋዘን ወዘተ የሚጨምር ነው፡፡ በሌላ በኩል አዋጁ በአንቀጽ 2(13) ስር ከጦር መሳሪያ ውጪ ላሉ ጉዳት አድራሽ ዕቃዎች ትርጓሜ የሰጠ ሲሆን ይህም በስለታማነታቸው ምክንያት ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም ወይም መርዛማ በመሆናቸው በሰው አካልና ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ እንደ ሳንጃ፣ ገጀራ፣ሜንጫ፣ ጦር፣ ቀስት ጎራዴ፣ ሴንጢ እና መሰል መሳሪያዎችን የሚያጠቃልል እንደሆነ ከአዋጁ መረዳት ይቻላል፡፡

የጦር መሳሪያ የሚሰጥበት አግባብና ይዘቱ

በግለሰብ ደረጃ የሚያዙ የጦር መሳሪያዎች ለመያዘ የፀና ፍቃድ ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች የጦር መሳሪያ ፍቃድ ከማግኘታቸዉ በፊት የተለያዩ መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለዉ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ የመኖር ፍቃድ ያለው መሆን፣ የአደገኛ ዕፅ ወይም የመጠጥ ሱስ የሌለበት መሆን፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ወይም በሕግ ችሎታውን ያላጣ ሰው መሆን፣ የተስተካከለ አእምሮ ያለው ወይም የሐይል አጠቃቀም ባህሪ የሌለው መሆኑ በተቆጣጣሪ ተቋም የታመነበት መሆን፣ የመሳሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ ሥልጠና እንዲወስድ ሲጠየቅ ፍቃደኛ መሆን፣ ለጦር መሳሪያ ፍቃድና እድሳት አስፈላጊውን ክፍያ መክፈል፣ መልካም ሥነ ምግባር ያለው ለመሆኑ ከሚኖርበት አካባቢ አስተዳደር የትብብር ደብዳቤ ማቅረብ መቻል ወዘተ በአዋጁ የተጠቀሱ መስፈርቶች ናቸው፡፡

የተጠቀሱትን መስፈርቶች ለሚያሟላ ሰው የሚሰጠው የጦር መሳሪያ ፍቃድ የባለፈቃዱን ሰው ሙሉ ስም፣ ፎቶ፣ የትውልድ ቀን፣ አሻራ፣ አድራሻ፣ የጦር መሳሪያውን አይነት፣ የውግ ቁጥር፣ የጥይት ብዛት፣ ተዛማጅ እቃ፣ ፍቃዱን የሰጠው ባለሥልጣን ስም፣ ፊርማ፣ ማህተም፣ ፍቃደ የተሰጠበት ቀን እና ፍቃድ የሚያበቃበት ቀን እንዲሁም ሌሎች ተቆጣጣሪው ተቋም በመመሪያ የሚያወጣቸውን መስፈርቶችን የሚያካትት መሆን አለበት፡፡ ይህም ያስፈለገበት መሠረታዊ ዓላማ በፍቃድ ተቀባዩም ሆነ ሰጪዉ ላይ የሕግ ተጣያቂነት ለማስፈን እንዲሁም የተደራጀ መረጃ መያዝ ወንጀልን በመከላልም ረገድ ጠቃሚ በመሆኑ ነው፡፡

የጦር መሳሪያ አጠቃቀምንና አያያዝን አስመልክቶ የተከለከሉ ተግባራት

ማንኛውም ሰው የፀና ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ፣ አባሪ እቃዎችን እና ለልማት ሥራ የሚውሉትን ሳይጨምር የጉዳት አድራሽ እቃዎችን ወደ ሀገር ማስገባት፣ ከሀገር ማስወጣት፣ መያዝ፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ ማሳየት፣ መደለል፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝና ማምረት የተከለከሉ ተግባራት ናቸው፡፡ በተጨማሪም በአምራቹ ወይም በተቆጣጣሪ ተቋም የተሰጠ የጦር መሳሪያ የውግ ቁጥርን በሙሉ ወይም በከፊል መቀየር፣ ማጥፋት ወይም በማናቸውም አይነት ሁኔታ ተለይተው እንዳይታወቁ ማድረግ እንዲሁም የጦር መሳሪያን ወይም የጦር መሳሪያን የተመለከተ አገልግሎት ማስተዋወቅ የተከለከለ ነው፡፡

በሌላ በኩል አያያዝን በተመለከተ ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው ስፍራዎች፣ የምርጫ ሥራዎች የሚከናወኑበት ቦታዎች፣ በሆቴሎች፣ በሲኒማና ትያትር ቤቶች፣ በሙዚየሞችና ተመሳሳይ በሆኑ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ በትምህርት፣ በሀይማኖትና እምነት ተቋማት ግቢ ውስጥ፣ በሆስፒታሎችና ክልኒኮች፣ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ የሕዝብ አገልግልት በሚሰጥባቸው ስፍራዎች፣ ፓርኮች ወይም በዱር እንስሳት መጠለያዎች ወዘተ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት የተከለከለ ተግባር ነው፡፡

በተያያዘም የጦር መሳሪያ ፍቃድ የተሰጠው ሰዉ ፈቃድ ከተሰጠው ክልል ውጪ ባሉ የክልልና ትላልቅ ከተሞች ለሕዝብ በሚታይ መልኩ ታጥቆ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ሆኖም በሥራ ላይ ላሉ የሕግ አስከባሪዎች ለስራቸዉ ዓላማ የጦር መሳሪያ ታጥቆ መንቀሳቀስ የተፈቀደ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፈቃድ ተሰጠው ሰው በአዋጁ አንቀጽ 18 ሥር የተመለከቱት ግዴታዎች ያሉበት ሲሆን ለአብነትም የጦር መሳሪያውን ይዞ የሚንቀሳቀስ ሰው የፍቃድ ወረቀቱን አብሮ መያዝ የሚጠበቅበት ከመሆኑም በተጨማሪ መሳሪያው ሲበላሽ፣ ሲጠፋ፣ ሲሰረቅ፣ ሲቀማ ወይም በማንኛውም ምክንያት ከቁጥጥሩ ውጪ ሲሆን በ15 ቀናት ውስጥ ለተቆጣጣሪው ተቋም ማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

የጦር መሳሪያ ፍቃድ ስለሚታደስበት፣ ስለሚታገድበት፣ ስለሚሰረዝበት እና ስለሚወረስበት አግባብ

በአዋጅ አንቀጽ 13፣ 14 እና 15 መሠረት የጦር መሳሪያ ፍቃድ የተሰጠው ማንኛውም ሰው የፍቃድ አገልግሎት ጊዜው ከማብቃቱ ከ60 ቀናት በፊት የእድሳት ጥያቄውን ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወይም ውክልና ለተሰሠጠው የክልል ፖሊስ ኮሚሸን ተቋም ማቅረብ አለበት፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ቀርቦ ተቆጣጣሪው ተቋም የእድሳት ጥያቄው ላይ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የቀድሞው ፍቃድ እንደፀና ይቆያል፡፡ ፍቃድ የተሰጠው ሰው ያቀረባቸው ማስረጃዎች አጠራጣሪ ሆነው ሲገኙና ጉዳዩን ማጣራት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ከተሰጠው ፍቃድ ውጭ መሳሪያውን ለሌላ ተግባር ያዋለው ስለመሆኑ በቂ ጥርጣሬ ሲኖር እንዲሁም የአገልግሎት ጊዜው ያበቃና ያልታደሰ ከሆነ ፈቃዱ ይታገዳል፡፡ ነገር ግን ባለፈቃዱ በ60 ቀናት ውስጥ በቂ ምክንያት አቅርቦ ማስታካከል ከቻለ እግዱ ይነሳለታል፡፡ ነገር ግን ማስታካከል ካልቻለ የጦር መሳሪያው በተቆጣጣሪ ተቋሙ ይወረሳል፡፡

በተጨማሪም መሣሪያው ወንጀል የተፈጸመበት ስለመሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ፣ ባለፍቃዱ ሲሞት፣ ያለበት አድራሻ ሳይታወቅ ሲቀር ወይም በፍርድ ወይም በሕግ ችልታውን ሲያጣ፣ ፈቃድ የተሰጠው ድርጅት ከሆነ ድርጅቱ ከፈረሰ ወይም ከተዘጋ፣ በራሱ ፍላጎት ፍቃዱን ሲመለስ፣ ፍቃዱን ለማግኘት ከሚያስፈለጉ መስፈርቶች አንዱ የተጓደለ ከሆነ፣ ሀሰተኛ ማስረጃ ያቀረበ መሆኑ ሲታወቅ እንዲሁም መሳሪያ ከተበላሸና ሊጠገን የማይቻል ከሆነ ፈቃዱ ተሰርዞ ይወረሳል፡፡

የወንጀል ተጠያቂነት

  • በጦር መሳሪያ መነገድ ወንጀል በሚመለከት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 481 ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
  • ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ ከላይ የተመለከተውን ክልከላ እና ግዴታ በመተላለፍ የፀና ፈቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ ወደ ሀገር ካስገባ፣ ከሀገር ካስወጣ፣ ካስቀመጠ፣ ከተገለገለ፣ ከደለለ፣ ከገዛ፣ ከሸጠ፣ ካጓጓዘ፣ ካመረተ…ወዘተ ከ1 እስከ 3 ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት እና ከ5,000 እስከ 10,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  • በህጋዊ መንገድ የታጠቀውን የጦር መሳሪያ ተቆጣጣሪው ተቋም ሳይፈቅድ የሸጠ ሰው ከ1ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡
  • የተሸጠው ለአሸባሪ ወይም ለህገ-ወጥ ቡድን ከሆነ ቅጣቱ 1 ዓመት እስከ 3 ዓመት ወይም እንደነገሩ ሁኔታ እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ይሆናል፡፡
  • በህጋዊ መንገድ የታጠቀውን የጦር መሳሪያ በማስያዣነት የተጠቀመ ወይም በትውስት ለሶስተኛ ወገን ያስተላለፈ ከ1 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡
  • የመሳሪውያን የውግ ቁጥር በሙሉ ወይም በከፊል የቀየረ፣ ያጠፋ ወይም በማናቸውም አይነት ሁኔታ ተለይተው እንዳይታወቁ ያደረገ ማንኛውም ሰው ከ6 ወር እስከ 2 ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት የሚቀጣ ሲሆን ሌሎች ጥፋቶችም አንደጥፋቱ አይነት የቅጣት መጠን ተቀምጦላቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

ዜጎች ሰላምና ደህንነታቸው ተከብሮ የመኖር መብት እንዳላቸው ሁሉ በሕግ የተጣሉባቸውን ግዴታዎች ማክበር አለባቸው፡፡ የጦር መሳሪያ በግለሰብ ደረጃ የሚፈቀደው ዜጎች ለሰላማቸው አስጊ ሁኔታዎች ሲያጋጥማቸው ራስን መካላክል እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡

ሆኖም የጦር መሳሪያ ለጥፋት ዓላማ ሊውል ስለሚችልና ገዳይ መሳሪያ ስለሆነ ጥንቃቄ እና ቁጥጥር ሊደረግለት ይገባል፡፡ በመሆኑም የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚስፈልገው በመሆኑ ፍቃድ የተሰጠው አካል በህጉ ላይ የተቀመጡትን የጥንቃቄ እርምጃዎችንና ግዴታዎችን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ