“የቤት ሰራተኞች በሚንከባከቧቸው ህጻናት እና በሚጠብቁት ንብረት ላይ በሚያስከትሉት ማንኛውም ጉዳት ኃላፊነት እና ተጠያቂነት አለባቸው”፡፡
በስራ አጋጣሚ ሰዎች በመካከላቸው በሚያስሩት ውል መሠረት አንዱ አሰሪ ሌላው ደግሞ ሠራተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን አሰሪዎች በሰራተኞች ላይ ከመርህ የወጣ ከአሰሪ እና ሠራተኛ ግንኙነት መብት እና ግዴታዎች ውጭ የሆኑ፣ በሰራተኞች መብት እና ደኅንነት ላይ አደጋ የሚጥሉ ድርጊቶችን የመፈጸም ሥልጣን ይሰጣል ማለት አይደለም፡፡
ይሁንና መሬት ላይ ያለን ሀቅ ስንመለከት አሰሪዎች የቀጠሯቸውን ሰዎች ክብር በሚነካ መልኩ ሲይዟቸው፤ ለጉዳትም ሲያጋልጧቸው ይስተዋላሉ፡፡
ዛሬ ዛሬ ደግሞ እንግዳ የሆኑ ለሰሚም የሚከብዱ ድርጊቶች ሲፈጸሙ መስማት እየተዘወተረ ይገኛል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከፖሊስ ተቋማት ጋር በጋራ ባከናወናቸው የወንጀል ምርመራ ተግባራት በቤት ሰራተኞች ላይ የሚፈጸሙ ድብደባዎች፣ እንግልቶች ብሎም ግድያዎች በተጨባጭ እየተከሰቱ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል፡፡ ይህ ድርጊት ሰው ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ የተጎናጸፈውን መብት የመጣስ ተግባር ከመሆኑም በላይ በወንጀል ህጋችንም ከፍተኛ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው፡፡ ከቀናት በፊትም የቤት ሠራተኛቸውን ገድለው በሳጥን ለመቅበር ጥረት ሲያደርጉ በአካባቢው ህብረተሰብ ትብብር በቁጥጥር ስር ውለው በ25 ዓመት ጽኑ እስራት የተቀጡት አሰሪዎች ለዚህ ዋቢ ናቸው፡፡
በአሰሪ እና በሠራተኛ መካከል ያለመግባባት የተፈጠረ እንደሆነ ተነጋግሮ ችግሩን ለመፍታት መሞከር፣ ይህ ካልተቻለ በስምምነት ውሉን አቋርጦ ተገቢውን ክፍያ ፈጽሞ ሠራተኛውን ማሰናበት መፍትሄ ሆኖ እያለ ማንም አያየኝም፤ አይደርስብኝ ብሎ በማሰብ በአካልም ሆነ በስነ ልቦና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ድርጊቶችን መፈጸም በተጎጂው ላይ ከሚያደርሰው በደል ባሻገር በድርጊቱ ፈጻሚ ላይ በገንዘብ የማይተካ የነጻነት ማጣትን አለፍ ሲልም ለእስር መዳረግን ያስከትላል፡፡ በዚህ ሂደት የምንመራው ህይወት የምናሳድጋቸው ልጆች ሆኑ ማህበረሰቡ ከኛ ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም ያጣሉ፤ ግላዊ ህልማችንም ይጨልማል፡፡
ከመጸጸት እና ከመቆጨት እራስን ለመጠበቅ ብስጭትን መቆጣጠር እና በሰከነ እና በተረጋጋ መንፈስ ትክክለኛው ዘዴ መርጦ መወሰን መልካም ነው፡፡
ይህ ታዲያ ልጆችን በአደራ ተቀብለው እንዲጠብቁና እንዲንከባከቡ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው እና አላግባብ በመጠቀም የሚጠብቋቸውን እና የሚንከባቧቸውን ልጆች፣ በጥበቃቸው ስር ያለ የአሰሪያችውን ሀብት እና ንብረት ላይ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰራተኞችን የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስቀር አይደለም። ህጉ አጥፊው አሰሪ በሚሆንበት ወቅት ተጠያቂነትን እንደሚያሰከትለው ሁሉ ሰራተኞችም በሚንከባከቧቸው ህጻናት እና በሚጠብቁት ንብረት ላይ በሚያስከትሉት ማንኛውም ጉዳት ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ያለባቸው መሆኑን አውቀው በህጉ መሠረት እንዲመሩ ይጠበቃል።
ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የወንጀል ህጋችን እንደ ወንጀሉ ክብደት ከቀላል እስራት እስከ ሞት ሊያስቀጣ የሚችል የወንጀል ተጠያቂነትን ሊያስከትል እንደሚችል በማወቅ ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡
ማህበረሰቡም በአካባቢው ተቀጥረው የሚሰሩ የቤት ሰራተኞች ላይ የሚፈጸሙ በደሎችን ተመልክቶ ዝም ማለት የለበትም፡፡ ድርጊቱ እንዲቆም፤ አጥፊም እንዲጠየቅ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ማሳወቅ አለበት፡፡
የፍትሕ ተቋማትም የሚቀርብላቸውን ጥቆማ በመቀበል አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ መብቶች እንዳይጣሱ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው፡፡ በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በዚህ ረገድ የቤት ሰራተኞች የሚደርስባቸውን ጫና እና ጉዳት ለማስቆም የማህበረሰቡን አስተሳሰብ እና የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ በሚረዱ ተግባራት ላይ በስፋት መሰማራት አለባቸው፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር
ለሕግ ፣ ለፍትሕ ፣ ለርትዕ