ቼክ ምንድን ነዉ? በቂ ስንቅ የሌለዉ ቼክ መፃፍ በወንጀል ያስጠይቃልን?

ማውጫ

Share this Article

በ1952 ዓ.ም የወጣው የሀገራችን የንግድ ሕግ በርከት ላሉ የንግድ ሰነዶች እውቅና የሰጠ ቢሆንም በተግባር ላይ ሰፋ ባለ መልኩ አገልግሎት ላይ እየዋለ ያለው ቼክ የሚባለው የንግድ ሰነድ ነው፡፡ ቼክ ውስብስብ በሆነ የንግድ ሥርዓት ውሰጥ በጥሬ ገንዘብ በመገበያየት ምክንያት የሚከሰቱ ወንጀሎችንና የንብረት ጉዳቶችን በማስቀረት የተቀላጠፈ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ቼክ ምንድን ነዉ ?

የቼክን ምንነትና ሊይዝ ስለሚገባው ዝርዝር ጉዳይ በሚመለከት የንግድ ህጋችን አንቀጽ 827 ላይ የተገለፀ ሲሆን ከዚህ አንቀጽ ጠቅላላ ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው ቼክ ማለት የከፋዩን ስም፣ የሚከፈልበትን ቦታ፣ ቼኩ የወጣበት ቀንና ቦታ እንዲሁም የአውጪውን ፊርማ የያዘ የተገፀው ባንክ ወይም ሕግ የባንክን ስራ እንዲያከናውን ሥልጣን የተሰጠው መስሪያ ቤት የተወሰነ ገንዘብ ለሶስተኛ ወገን ወይም ለአምጭው ለራሱ እንዲከፍለው የሚያዝ ሐተታ የሌለበት የንግድ ሰነድ (Commercial instrument) ነው ሊባል ይችላል;; በንግድ ሕግ ውስጥ አራት አይነት የቼክ አይነቶች ማለትም የስርዝ ምልክት ያለበት ቼክ (Crossed cheque)፣ ከሒሳብ ውስጥ የሚገባ ቼክ (Cheque payable in account)፣ የመንገድ ቼክ (Travellers cheque) እንዲሁም መደበኛ ቼክ የሚባሉት የቼክ አይነቶች የሚገኙ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን የመጀመሪያ ሶስቱን የቼክ አይነቶች ወደጎን በመተው አራተኛው የቼክ አይነት ላይ ማለትም መደበኛ የቼክ አይነት ላይ ይሆናል፡፡

መደበኛውን የቼክ አይነት ምንነት በሚመለከት የንግድ ህጋችን አንቀጽ 827 እና በሚከተሉት አንቀጾች ላይ ተንግጎ ይገኛል፡፡
ከእነዚህ ድንጋጌዎች አጠቃላይ ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው መደበኛ ቼክ ማለት መጠኑ በግልፅ ተለይቶ የተጠቀሰ የገንዘብ መጠን ለአንድ ግለሰብ ወይም ሶስተኛ ወገን እንዲከፈል ለአንድ ባንክ ቤት ወይም ቼክ መከፈልን ጨምሮ በሕግ የባንክ ቤት ስራን ለማከናወን ሥልጣን ለተወጠዉ ተቋም ሐተታ የሌለበት ትእዛዝ የያዘ የንግድ ሰነድ ነዉ፡፡
አንድ ቼክ ህጋዊ ነው ተብሎ ክፍያ ሊፈጸምበት የሚችለው በንግድ ህጉ አንቀጽ 827 ላይ የተገለጹትን መግለጫዎች ካሟላ ብቻ ነው;;

በዚህ የሕግ ድንጋጌ መሠረት አንድ ቼክ ህጋዊ ቼክ ነው እንዲባል አምስት መሠረታዊ መግለጫዎችን ሊይዝ የሚገባ ሲሆን እነዚህ መግለጫዎችም፡-

  1. የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ሃተታ የሌለበት ትእዛዝ;; ይህም ሲባል በቼኩ ላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወይም መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ሳይዘረዝር ሊከፈል የሚገባውን የገንዘብ መጠን በግልጽ ሊጻፍበት ይገባል;;
  2. ከፋይ የሆነው ተቋም ስም፡፡ በንግድ ህጋችን አንቀጽ 829 መሠረት ቼክን ተቀብሎ ክፍያ ሊፈጽም የሚችለው ባንክ ቤት ወይም በሕግ የባንክ ቤትን ስራ ለማከናወን ሥልጣን የተሰጠው ተቋም ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ቼኩን ተቀብሎ በቼኩ ላይ የተገለጸውን የገንዘብ መጠን እንዲከፍል የታዘዘው ተቋም በግልጽ በቼኩ ላይ ሊኖር ይገባል;;
  3. ገንዘብ የሚከፈልበት ቦታ
  4. ቼኩ የወጣበት ቦታና ጊዜ
  5. ቼኩን ያወጣው ሰው ፊርማ ናቸው።

በሕግ የተቀመጡትን መግለጫዎች ያላሟላ ቼክ የሚኖረው የሕግ ውጤት

በመርህ ደረጃ አንድ ቼክ እንደ ህጋዊ ቼክ ተቆጥሮ ክፍያ የሚፈጸምበት ከላይ የተገለጹትን አምስት መግለጫዎች የያዘ እንደሆነ ብቻ ነው;; ነገር ግን በንግድ ህጉ አንቀጽ 828 ላይ ሁለት ልዩ ሁኔታዎች ተቀምጠዋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ቼክ የሚከፈልነት ቦታ ያልገለፀ እንደሆነ በከፋዩ ስም አጠገብ የተቀመጠው ቦታ የመክፈያ ቦታ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ከከፋዩ ስም አጠገብ ከአንድ በላይ ቦታዎች የተገለፁ እንደሆነ በመጀመሪያ የተመለከተዉ ቦታ ቼኩ ተከፋይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ቼኩ ምንም አይነት ቦታ ያልገለፀ እንደሆነ የከፍዩ ዋና ስራ ማካሔጃ /ዋና መስሪያ ቤት/ የቼኩ የክፍያ ቦታ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
ክዚህ የሕግ ግምት ውጪ የተቀሩትን ከላይ የተገለፁትን መስፈርቶችን ያላሟላ ቼክ እንደህጋዊ ቼክ የሚቆጠር ባለመሆኑ ቼክ ከፋዩ ለመክፈል አይገደድም፡፡በመሆኑም የቼክ ተከፋይ የሆነዉ ግለሰብ ቼኩ እንደ ህጋዊ ቼክ ተቆጥሮ ከፋዩ በቼኩ ላይ የተገለፀዉን የገንዘብ መጠን እንዲከፈለዉ ለማስገደድ የሚችለዉ ቼኩ በህጉ ላይ የተገለፁትን መስፈርቶች አሟልቶ የተገኘ እንደሆነ ብቻ በመሆኑ ማንኛዉም ግለሰብ አንድን ቼክ ከመቀበሉ በፊት ቼኩ ከላይ የተገለፁትን ዝርዝር መግለጫወችን የያዘ ስመሆኑ ማረጋገጥ ይኖርበተል፡፡

ከቼክ ጋር ተያይዘዉ የሚፈፀሙ ወንጀሎችና የሚያስከትሉት ቅጣት

ቼክ በርከት ያለ ጥሬ ገንዘብን ከበታ ቦታ ይዞ በመዘዋወር የሚከሰተዉን የአደጋ ተጋላጭነትና በመገበያያ ገንዘብ ላይ የሚደርሰዉን ጉዳት በማስቀረት የንግድ ስርአቱ በተቀላጠፈ መልኩ አንዲከናወን ጉልህ ሚና የሚጫወት ቢሆንም ከቼክ ጋር ተያይዘዉ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የንግዱ ማኅበረሰብ በቼክ ላይ ያለዉን እምነት በመቀነስ ቼክ ለተቀላጠፈ የንግድ ሥርዓት የሚያበረክተዉ ጉልህ አስተዋፅኦ ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡

ከቼክ ጋር በተያያዘ በዋናነት የሚፈፀመዉ የወንጀል አይነት ደረቅ ቼክ ማዉጣት ወንጀል ሲሆን ደረቅ ቼክ ወይም በቂ ስንቅ ሳይኖር ቼክ ማዉጣት ወንጀል ማለት ቼኩ በሚወጣበት ወይም ለባንክ በሚቀርብበት ወቀት የሚያዝበት በቂ ስንቅ በሒሳብ ወስጥ ሳይኖር ቼክ ማዉጣት ወንጀል እንደሆና ይህ የወንጀል ድርጊት ተፈፅሞ ሲገኝም እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት እንደሆነ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 693 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ሌላኛዉ ከቼክ ጋር በተያያዘ የሚፈፀመዉ የወንጀል አይነት ደግሞ ሀሰተኛ ወይም ህጋዊ ያልሆነ ቼክ የማዉጣት ወንጀል ነዉ፡፡ ሀሰተኛ ቼክ ማለት ቼክን ለማተም ሥልጣን ባለዉ ባንከ ቤት ታትሞ ያልተሰጠ ወይም ታትሞ ከተሰጠዉ ጋር ተመሳስሎ የተሰራ ቼክ መሳይ ሰነድ ሲሆን ማንም ሰዉ ይህንን ሀሰተኛ ቼክ የሰራ ፣ የተገለገለ ወይም ህጋዊ አስመስሎ ለሶስተኛ ወገን ያስተላለፈ አንደሆነ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 375ና በሚከተሉት አንቀፆች እንዲሁም በተደራቢነት በወ.ህ.ቁ 692 መሠረት በማታለል ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ህጋዊ ቼክ ሊኖረዉ ስለማገባ አስገዳጅ መግለጫዎችና ከቼክ ጋር በተያያዘ ስለመፈሙ ወንጀሎች በአግባቡ በመገንዘብ እራሳችንን ከአደጋ እንጠብቅ የእለቱ መልእክታችን ነዉ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት፡፡

በንቃተ ሕግ፤ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት