ወንጀል የማኅበረሰብን አጠቃላይ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት ከመሆኑ አንፃር ማህበረሰቡ ወንጀል ፈፃሚዎች እንዲለዩ እና የሕግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይፈልጋል፡፡ በአንፃሩ በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎች በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እስካልተባሉ ድረስ ነፃ ሆነው የመገመት መብት ያላቸው በመሆኑ የማኅበረሰቡን ፍላጎት እና የተጠረጠሩ ሰዎችን መብት ባማከለ መልኩ መፍትሔ መስጠት ይቻል ዘንድ የዋስ መብት የሕግ ጥበቃ ተሰጥቶታል፡፡ ፖሊስ በመያዣ ትእዛዝ ወይም በህጉ በተቀመጠ ልዩ ሁኔታ ያለመያዣ ትእዛዝ የያዘውን ሰው በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ አለበት። የቀረበለት ፍርድ ቤትም የተያዘው ሰው በማቆያ እንዲቆይ ወይም በዋስትና እንዲለቀቅ ይወስናል። በዚህ አጭር ጽሁፍ የዋስ መብት ምንነትን እና የዋስ መብትን በተመለከተ ያለው የሕግ ማዕቀፍ የምንመለከት ይሆናል፡፡
የዋስ መብት ምንነት
የዋስ መብት አንድ በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው ወደፊት ሲፈለግ እንዲቀርብ ወይም ክስ የተመሰረተበት ሰው ክሱን በውጪ ሆኖ እንዲከታተል የሰው፣ የገንዘብ ወይም የንብረት ማስያዣ ወይም ማረጋገጫ በማቅረብ ጉዳዩን በውጪ ሆኖ እንዲከታተል የሚደረግበት ሂደት እንደሆነ ከሕጉ መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም የዋስ መብት በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በማስረጃ ተረጋግጦ ጉዳዩ የመጨረሻ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የገንዘብ ወይም በቂ የሰው ዋስ በማቅረብ ከእስር ነፃ ሆኖ ጉዳዩን በቀጠሮ እየቀረበ ለመከታተል የሚያስችል መብት ነው።
የዋስ መብት የሕግ ማዕቀፍ
የዋስ መብት ሀገራችን ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች እንዲሁም በኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ-መንግሥት የሕግ ጥበቃ ከተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአለም አቀፉ ሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን አንቀጽ 9(3) መሠረት የተያዙ ሰዎች የዋስ መብት እንዳላቸው በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በድንጋጌዎቹ መሠረት የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እና የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው የመጠየቅ መብት ያላቸው ሲሆን ፍርድ ቤትም የዋስ መብትን የማስከበር ወይም በሕግ የተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች በተገኙ ጊዜ ደግሞ ዋስትና ሊነፍግ እንደሚችልም ያመለክታል፡፡ በመሆኑም የዋስ መብት መርህ ሲሆን መብቱ ሊነፈግ የሚችለው በልዩ ሁኔታ በሕግ ሲደነገግ ብቻ ነው፡፡
በሀገራችን የዋስ መብት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 19(6) ሥር እንዲሁም በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 59 ላይ ተደንግጎ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች በህገ መንግሰቱ አንቀጽ 9(4) መሠረት የሀገራችን ሕግ አካል ናቸው፡፡
በነዚህ ሕግጋት መሠረት የዋስ መብት በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በምርመራ ወቅትም ሆነ ክስ ከቀረበበት በኋላ በዋስ ከእስር ተለቆ ጉዳዩን የሚከታተልበት አሠራር መርህ /Principle/ ሲሆን ተጠርጣሪው የተጠረጠረበት የወንጀል ዓይነት፣ ክብደትና የተጠርጣሪውን ባህሪ ከግምት በማስገባት ሕጉ ውስጥ የተመለከቱ የተወሰኑ ሁኔታዎች በተሟሉ ጊዜ የዋስትና መብት ሊገደብ እንደሚችል በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና በተለይ በወጡ ሌሎች ህጎች ተመልክቷል፡፡
የዋስትና መብት የሚፈቀድበት ሂደት
በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርአት ህጉ መሠረት የዋስ መብት በዋናነት በፍርድ ቤት የሚፈፀም ሲሆን በልዩ ሁኔታ በመርማሪ ፖሊስ የሚፈፀምበት ሁኔታም በህጉ ተካቶ ይገኛል፡፡
ፍርድ ቤት የሚሰጥ ዋስትና
ፖሊስ አንድን ተጠርጣሪ በያዘ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡ ፍርድ ቤት የቀረበው ተጠርጣሪም የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለት ፍ/ቤቱን ሊጠይቅ የሚችል ሲሆን ፍ/ቤቱም የቀረበለትን አቤቱታ በመመርመር በዋስ ሊለቀው ወይም የተጠርጣሪው በዋስ መውጣት ፖሊስ ለሚያደርገው ምርመራ እንቅፋት የሚሆን ከሆነ ወይም ተርጣሪው የፈፀመው ወንጀል በዋስ የማያስለቅቀው ከሆነ የምርመራ ጊዜ በመስጠት ተጠርጣሪ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ሊያደርግ ይችላል፡፡
በፖሊስ የሚሰጥ ዋስትና
ፖሊስ በወንጀል ጠርጥሮ የያዘውን ሰው በራሱ ማለትም በተጠርጣሪው ዋስትና ወይም በገንዘብ ዋስ ሊለቀው የሚችልበት ሁኔታ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 28 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በድንጋጌው መሠረት ፖሊስ ተጠርጣሪን በዋስ ሊለቅ የሚችለው
- ተጠርጣሪው የተጠረጠረበት ወንጀል በፅኑ እስራት ወይም በመሰል ቅጣት የማያስቀጣ ሲሆን ወይም
- ወንጀል የተሰራ ለመሆኑ ወይም ተጠርጣሪው የተባለውን ወንጀል መፈፀሙ የሚያጠራጥር እንደሆነ ነው፡፡
በዚህ መልኩ ፖሊስ ተጠርጣሪን በዋስ ሲለቅ የገንዘብ ወይም የራስ ዋስትና እንዲያቀርብ ካደረገ በኋላ ተጠርጣሪው በተፈለገ ሰዓት መቅረብ እንዲችል በማስፈረም ተጠርጣሪን ሊለቅ ይችላል፡፡ ከላይ በተገለፀው መሠረት በዋስ ያልተለቀቀን ተጠርጣሪ ፖሊስ በ48 ሰአታት ውስጥ ፍርድ ቤት ማቅረብ የሚጠበቅበት ሲሆን ፖሊስ በዋስ ያለቀቀው ወይም ፍርድ ቤት ያላቀረበው ተጠርጣሪው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 64 መሠረት በዋስ እንዲወጣ በማመልከቻ ፍርድ ቤትን የመጠየቅ መብት እንዳለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 28(2) በግልፅ ተደንግጓል፡፡
የዋስትና መብትን የሚያስነፍጉ ሁኔታዎች
ዋስትና በህገ-መንግሥት እንዲሁም ሀገራችን ባፀደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች መርህ ሆኖ የተረጋገጠ መብት ቢሆንም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ሊከለክል እንደሚችል ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 19(6) ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና በተሻሻለው የጸረ-ሙስና ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 882/2007 ላይ የተቀመጡትን ዋስትና የሚያስከለክሉ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
አንደኛ፡-የመጀመሪያው እና ዋነኛው በወንጀል ሥነ ሥርአት ህጉ ላይ የተመለከተው ሲሆን
በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 63 መሠረት
የተያዘው ሰው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት ወንጀል በሞት ወይም በአስራ አምስት ዓመት ወይም ከዛ በላይ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ከሆነ እና ወንጀል የተፈፀመበት ሰው በተፈፀመበት ወንጀል የሞተ ከሆነ እንዲሁም
በየወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 67 መሠረት ዋስትና
- ተጠርጣሪው ወይም የተያዘው ሰው በዋሰትና ወረቀቱ ላይ የተቀመጡትን ግዴታዎች የሚፈፅም የማይመስል እንደሆነ
- ተጠርጣሪው በዋስ ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ሊፈጽም ይችላል ተብሎ ሲገመት
- ተጠርጣሪው ምስክሮችን በማባበል ወይም በመግዛት ማስረጃዎችን ሊያጠፋ እንደሚችል የተገመተ እንደሆነ ተጠርጣሪው በዋስ ሊለቀቅ አይችልም፡፡
በተሻሻለው የጸረ-ሙስና ሥነ-ሥረዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ላይ የተቀመጠውን ሲሆን በሙስና ወንጀል
የተያዘ ሰው በዋስትና እንዲለቀቅ ፍርድ ቤት ቀርቦ የመጠየቅ መብት ያለው ቢሆንም የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት ወንጀል፡-
- ከአስር ዓመት በላይ በሆነ ፅኑ እስራት የሚስቀጣ ከሆነ
- ከአራት ዓመት በላይ እና ከአስር ዓመት በታች የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲደመሩ ከአስር ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ሲሆን ነው፡፡
የዋስትና ግዴታዎችና የዋስትና ወረቀት ውጤት
የዋስ መብት በተፈቀደ ጊዜ የሰው ወይም የገንዘብ ዋስ ማቅረብ የሚቻል ሲሆን የዋሶች ግዴታም በማንኛውም ጊዜና ቦታ በቀጠሮው ቀን ዋሱ በዋስትና ወረቀት የተለቀቀውን ተከሳሽ ወደ ፍርድ ቤት የማቅረብ ኃላፊነት ነው። በዋስትና ወረቀቱ ላይ የፈረመው ዋስ የሞተ እንደሆነ ዋስተናው ውድቅ ሆኖ የተያዙትን መያዣዎች ለዋስ ወገን ተመላሽ እንዲሆኑ ይደረግና በዋስትና ወረቀቱ የተለቀቀው ተከሳሽ ሌላ ዋስ እንዲጠራ ይታዘዛል። በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 71 የዋስትናው ወረቀት ወይም ግዴታ የሚቆይበት ጊዜ ወሰን ያለው ነው። ዋስትና ወረቀት ፍርድ ቤት ለወሰነው ጊዜ ዋጋ ያለው ሆኖ የሚቆይ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማራዘም ይቻላል። ሆኖም በዋስትና በተለቀቀው ተከሳሽ ላይ የቀረበው ክስ የተተወ፣ ውሳኔ ያገኘ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ወረቀቱ ቀሪ እንዲሆን ይደረጋል።
በሌላ በኩል በዋስትና ወረቀት የተለቀቀው ተጠርጣሪ (ተከሳሽ) ይጠፋል ተብሎ የሚጠረጠር በሆነ ጊዜ ዋሶች ለፍርድ ቤት አመልክተው ዋስትናቸው እንዲወርድላቸው ለመጠየቅ ይችላሉ። ተከሳሹ ተይዞ እንደቀረበም ይጠፋል ተብሎ በተጠረጠረ ጊዜ የቀረበ የዋስትና ይውረድልኝ ጥያቄ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ዋስትናውን የመከልከል ወይም ግዴታውን የማክበድ ትእዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል በቁጥር 77 ካለው የሕግ መንፈስ ለመረዳት ይቻላል። ዋሶች የዋስትና ግዴታቸው በጋራ ወይም የተወሰኑት እንዲወርድላቸው በጠየቁ ጊዜ ተከሳሹ በቂ ተተኪ ዋስ እንዲያቀርብ እና ይህን ማቅረብ ያልቻለ ከሆነ የዋሶች ግዴታ እንዲወርድ በማድረግ ተከሳሹ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ በማለት ትእዛዝ ይሰጣል።
በአጠቃላይ የዋስ መብት በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በሕግ የተረጋገጠላቸው መብት ሲሆን በልዩ ሁኔታ በሕግ በግልፅ በተደነገገው መሠረት ካልሆነ በስተቀር ሊነፈግ የማይችል በመሆኑ የሕግ አስከባሪ አካላት መብቱን አክብረው የማስከበር ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እና ዜጎችም ለመብቱ መከበር የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ