የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት በአለማቀፍ ህጎችም፤ ስምምነቶች እንዲሁም በአገራችን ህገ መንግሥት እና ህጎች ጥበቃ እና እውቅና ያሚሰጠው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እነዚህ መብቶች ፍጹም እና ምንም አይነት ገደብ የማይደረግባቸው አይደሉም፡፡ የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት አንዳንድ አስገዳጅ እና አሳማኝ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብሔራዊ ደኅንነትን፤ የሕዝብ ሰላምን፤ ወንጀልን ለመከላከል እና ተፈፅሞ ሲገኝ ወንጀልን ለመመርመር፤ የሕዝብን ጤናና ሞራልን ለመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብት እና ነጻነትን ለማስከበር ሲባል ሊገደቡ እና ሊጣሱ ይችላሉ፡፡
ከዚህም ውስጥ ወንጅልን ለመከላከል እና ተፈፅሞ ሲገኝ ወንጀልን ለመመርመር ሲባል በግለሰብ እና በመኖሪያ ስፍርዎች ላይ ሚደረግ ብርበራ የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት ከሚገድቡ ሁኔታዎች አንዱ ነው፡፡ ይህም በአለማቀፍ ህጎች በአገራችን ሕግ መንግስቱ እና በሌሎች የአገራችን ህጎች ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ የወ/መ/ሥ/ሥ ህጉ፣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 እና ሌሎች ህጎች ላይ ብርበራ የሚደረግባቸውን ሁኔታዎች በመዘርዘር የሚያስቀምጥ ሲሆን ይህም ጹሁፍ ብርበራ የሚደረግበትን ህጋዊ ሂዳት፣ የብርበራ አይነቶችን፤ በብርበራ ወቅት ሊደረግ የሚገባን ጥንቃዌዎችን በአጭሩ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡
ብርበራ እና የግል ሕይወት የመከበር እና የመጠበቅ መብት
የሰው ልጅ የግል ሕይውት፣ ሰውነቱ፤ ማኖሪያ ቤቱ፤ ቤተሰቡ፤ ክብሩ፤ የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች ሊከበሩ እና ሊጣሱ እንደማይገባ፡፡ እንዲሁም ማንኛውም የመንግሥት አካል እነዚህን መሠረታዊ መብቶች ማጣስ እንዳሌለበት እና እንዳይጣሱም ጥበቃ ማድረግ እንዳለበት የዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 12 እና በአለማቀፍ የፖለቲካ እና የሲቪል መብቶች ኮንቬንሽን አንቀጽ 17 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ነገር ግን እነዚህ መብቶች ፍጹም ያማይነኩ እና ገደብ ያማይደረግባቸው አይደሉም፡፡ በ1995 የወጣው የኢ.ፊ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት በአንቀጽ 26 ስር የግል ሕይወት የከመበር እና የመጠበቅ መብት ላይ ማንኛውም ሰው የግል ሕይወቱ፤ ግላዊነቱ የመከበር መብት እንዳለው፤ ይህም መብት መኖሪያ ቤቱ፤ ሰውነቱ እና ንብረቱ ከመመርመር እንዲሁም በግል ይዞታው ያለን ንብረት ከመያዝ የመጠበቅ መብት እንዳላው ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም በግል የሚጻጻፋቸው እና የሚጽፋቸው፤ በፖስታ የሚላላካቸው ደብዳቤዎች፤ እንዲሁም በቴሌፎን፤ በቴሌ ኮሚኒኬሽን እና በኤሌትሮኒክስ መሳሪዎች የሚያደርጋቸው ግኑኝነቶች እንደሚጠበቁ እና እንደማይደፈሩ የሚያስቀምጥ ሲሆን የመንግሥት ባለስልጣኖችም እነዚህን መብቶች የማክበር እና የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ነግር ግን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 26/3 መሠረት ወንጀልን ለመከላክል እና ተፈፅሞ ሲገኝ ወንጀልን ለመመርመር ሲባል የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት ሊጣሱ እና ብርበራ ሊካሄድ እንደሚችል የሚያስቀምጥ ሲሆን ለዚህም ሶስት ሁኔታዎች ሊሟሉ የሚገባ ሲሆን ይህም፡-
- የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብቶችን ለመገደብ የሚፈቅድ ግልጽ የሆነ የሕግ ድንጋጌ ሲኖር
- የሚደረገው ገደብ ብሔራዊ ደኅንነትን፤ የሕዝብ ሰላምን፤ ወንጀልን ለመከላከል፤ የሕዝብ ጤናና ሞራልን ለመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብት እና ነጻነትን ለማስከበር ዓላማዎች ሲሆን
- የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብቶችን ለመገደብ ሚያስችሉ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲኖሩ እና ሲፈጠሩ ብቻ ነው በማለት ድንግጎ ይገኛል፡፡
ብርበራ በአገራችን ሕግ
ብርበራ የሚደረገው በዘፈቀደ ሳይሆን በቅድሚያ ወንጀል ከተሰራ ወይም ወንጀል ተሰርቶል ብሎ በተጠረጠረ ጉዳይ ግዙፍነት ያላቸው ማስረጃዎች ፍለጋ ነው፡፡ ይህም ብርበራ በሰው፤ በተሸከርካሪ፤ በቤት ወይም ግቢ ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ ብርበራ የሚካደው ግለሰቡ በወንጀል ተከሶ ወይም ወንጀል ስርቶል ተብሎ በተጠረጠረበት ጊዜ ወይም ወንጀል ሊሰራ ማቀዱ በተደረሰበት ጊዜ እንደሆነ በወ/መ/ሥ/ሥ ህጋችን ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በአገራችን የወ/መ/ሥ/ሥ ህገ አንቀጽ 32 መሠረት ማንኛውም መርማሪ ፖሊስ ወይም የፖሊስ ባልደረባ የሰውን ቤት መበርበር ወይም እቃን መያዝ ያሚችለው አንድ ሰው በተከሰሰበት ወንጀል ወይም ወንጀል ሰርቷል ተብሎ በተጠረጠረበት ነገር ማስረጃ የሚሆን በሰውነቱ፤ በማኖሪያ ቤቱ ወይም በሱ ይዞታ ስር ባለ ቦታ ደብቆል ሚያሰኝ በቂ ምክንያት ሲኖር ብቻ፡፡ ይህንም ብርበራ ማድረግ የሚችልው በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ ሲሆን በህጉ ላይ ያተቀመጠው ያለፍርድ ቤት ትዛዝ ብርበራ ያሚደረግባቸው ሁኔታዎች ሲያገጥም ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ብርበራውን መድረግ እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡
የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 42 ላይ ስለሚደረግ የልዩ የምርመራ ዘዴን ስለመጠቀም ያስቀመጠ ሲሆን በሀገር እና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል የሽብር ወንጀል ስጋት ሲኖር ፖሊስ በመደበኛው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ማስረጃ ማሰባሰብ ሳይቻለው ሲቀር ልዩ የምርመራ ዘዴዎች በመጠቀም ማስረጃ ለመሰብሰብ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ከነዚህም የምርመራ ዝዴዎች ውስጥ ተጠርጣሪው በፖስታ፣ በደብዳቤ፣ በቴሌፎን፣ በፋክስ፣ በራድዮ፣ በኢንተርኔት እና በሌሎች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የሚያደርጋቸውን ልውውጦች ወይም ግንኙነቶች በመመርመር ወይም በመጥለፍ ሲሆን ፖሊስ ልዩ የማስረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው ፍርድ ቤት የምርመራውን አስፈላጊነት አምኖ ሲፈቅድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ፖሊስ አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመው በአካባቢው ያለውንና የሚመለከተውን የዓቃቤ ሕግ ተቋም ኃላፊ በማስፈቀድ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በልዩ የምርመራ ዘዴ ማስረጃ ሊሰበስብ ይችላል፡፡ ሆኖም ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በልዩ የምርመራ ዘዴ ማስረጃ ለመሰብሰብ በጀመረ በ 48 ሰዓት ውስጥ ምክንያቶቹንና በዐቃቤ ሕግ የተሰጠውን ጊዚያዊ ፈቃድ ጨምሮ ለፍርድ ቤት በጽሑፍ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ፍርድ ቤቱም የጥያቄውን አግባብነት መርምሮ ለመቀበል ወይም ውድቅ ለማድረግ ይችላል፡፡ በተሰጠው ትእዛዝ ላይም ይግባኝ አይቀርብበትም በማለት በአዋጁ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የብርበራ አይነቶች
በእኛ ሀገር ሕግ ውስጥ በግልጽ ያተጠቀሰ ቢሆንም በሌሎች አገራት ሕግ ውስጥ ጠቅላላ ብርበራ እና ውስን ብርበራ በማለት በሁለት ይከፈላል፡፡ ጠቅላላ ብርበራ ትእዛዝ በፍርድ ቤት በተሰጠ ጊዜ ፖሊስ የሚበረብረው ቦታ ወይም ሰው ማንነት መጠን የተገደበ አይደለም፡፡ ጠቅላል ብርበራ ሰዎችን መሠረታዊ መብት ሚጥስ በመሆኑ በርካታ ሀገራት ይህን ብርበራ አይነት ከሀገራቸው ህገ ውስጥ አውጥታዋል፡፡
በአገራችን ሕግ መሠረት ብርበራ በሁለት አይነት መንገድ ሊከናወን ይችላል እናዚህም በወ/ሥ/ሥ/ህጉ አንቀጽ 32 እና 33 ላይ የተገለጹ ሲሆኑ በፍርድ ቤት ትእዛዝ እና ያለፍርድ ቤት ትዛዝ ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡
1ኛ በፍርድ ቤት ማዘዣ የሚከናወን ብርበራ
የፍርድ ቤቱ ማዘዣ መሠረት ያሚደረግ ብርበራ ፖሊስ ለማያዝ ያቀደውን ግዙፍነት ያለው ማስረጃ እና ከምን ቦታ ለማግነት እንዳሰበ በግልጽ ለፍርድ ቤቴ ጥያቄ በማቅረብ ያሚያደርገው የብርበራ አይነት ሲሆን ፤ ብርበራውም የሚከናወነው ፖሊስ ፍርድ ቤትን ጠይቆ በፍርድ ቤት በተፈቀደለት ጊዜ ያሚከናውን የብርበራ አይነት ነው፡፡
2ኛ ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ የሚከናወን ብርበራ
ይህ የብርበራ አይነት አንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲገጥሙት ፖሊስ ያለ የፍርድ ቤቱ ማዘዣ ብርበራ ያሚያደርግበት ሁኔታ ነው፡፡ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህጉ አንቀጽ 32/2 ሀ እና ለ መሠረት የሚደረግ ብርበራ ሲሆን ይህውም ፡-
- ፖሊስ ወንጀለኛውን እጅ ከፊንጅ ተከታትሎ እቤት ውስጥ ሲገባ
- ወንጀሉን የሰራበትን ነገር እቤት ውስጥ ያስቀመጠ ሲሆን ወይም
- ከሶስት ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ክስ ወይም አቤቶታ ቀርቦበት ለተፈጸመ ወንጀል ለማስረጃ ሚሆን ወንጀሉ የተፈጸመበት ነገር በአንድ ቦታ የተደበቀ ወይም የተቀመጠ መሆኑ ለመርማሪ ፖሊስ ወይም ለፖሊስ ባልደረባ በተነገረው መሠረት ተገቢ ጥርጣሬ የሚያሳደር ሲሆንና ያብርበራውን ማዘዣ ኢስኪቀበል ድረስ ወንጀል ተሰራበት የተባለው ነገር ካለበት ቦታ ይወሰዳል ተብሎ በበቂ ምክንያት የታመነ ሲሆን ነው፡፡
በብርበራ ወቅት ሊደረግ የሚጋባ ጥንቃቄ
ከተፈቀደላት ሰው እና ቦታ ውጪ ተበርበሮ የተገኘ መረጃ ከማርዛማ ዛፍ ላይ የተገኘ ጣፋጭ ፍሬ ይሉታል ፡፡ይሄውም የተገኘው ማስራጃ ከድርጊቱ ጋር ግንኙነት ያለው ሆኖም ግን ከሕግ ውጪ የተገኘ ማስረጃ ህጋዊ ስለማይሆን በፍርድ ቤት ውድቅ ይሆናል፡፡
የፍርድ ቤቱ ማዘዣ ጥያቄ ፖሊስ ለማያዝ ያቀደውን ግዙፍነት ያለው ማስረጃ እና ከምን ቦታ ለማግነት እንዳሰበ በግልጽ ለፍርድ ቤት ጥያቄ በሚያቀርብበት ጊዜ በመጠይቀው ላይ መግለጽ አለበት ፡፡ይህ ማለት ፖሊስ በርብሮ ለማግኘት የፈለገው ሕግ ወጥ መሳሪያ ከመኝታ ቤት ከሆነ በብርበራ ወቅት አደንዛዥ እጽ ቢያገኝ ወይም ብርበራ ማዘዣ ላይ ያልተፈቀደለት ቦታ ጭምር ቢያደርግና ከዚህም ካልተፈቀደለት ቦታ ለወንጀሉ የሚፈለገውን ማስረጃ ቢያገኝ ህጋዊ ማስረጃ አይሆንም ፡፡በተጨማሪም በትዛዙ ውስጥ ከተገለጸው ማስረጃ ከመሰብሰብ ውጪ ሌላ የተለየ ማስረጃ ፈልጎ ቢያገኝና ማስራጃውን ለፍርድ ቤት ቢያቀርብ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ያረገዋል፡፡ በመሆኑም ብርበራ በሚደረግበት ወቅት ፡-
- ማንም ሰው በተከሰሰበት ወንጀል ወይም ወንጀል ሰርቷል ተብሎ በተጠረጠረበት ነገር ማስረጃ የሚሆን በሰውነቱ ደብቋል ሚያሰኝ በቂ ምክንያት መኖሩን ማረጋጋጥ አለበት
- ብርበር ያሚደረገው ከተያዘው ሰው ጋር የተመሳሰለ ጾታ ባለው ሰው ብቻ መሆን አለበት፡፡
- ፍርድ ቤቱ ለፍትሕ ዓላማ ወይም ለማንኛውም ምርመራ ለክሱ መሰማት ወይም በህጉ መሠረት ለሌላው ክስ ሥነ ሥርዓት የማዘዣው መሰጠት የሚጠቅም መሆኑን ካልተረዳው በቀር የብርበራ መዘዣ መስጠት አይችልም፡፡
- ማንኛውም የብርበራ ማዘዣ ሚበረበረውን እና የሚያዘውን እቃ ማመልከት አለበት፡፡ በማዘዣው ውስጥ ከተመለከተው በቀር መርማሪው ፖሊስ ወይም ያፖሊስ ባልደረባ ሌላውን እቃ መያዝ አይችልም፡፡
- መርማሪ ፖሊስ ወይም ያፖሊስ ባልደረባ እቃውን በሚይዝበት ጊዜ የተያዘውን እቃ ዝርዝር መጻፍ አለበት ፡፡ ቢችል በጉዳዩ ነጻ የሆነ ሰው እቃው ዝርዝር ሊስት ትክክል መሆኑን እንዲያረጋግጥ እና እንዲፈርምበት ያስፈልጋል፡፡
- ለክሱ መሰማት አስፈላጊ የሆነው የተያዘው እቃ፤መረጃ ፤ኢግዚቢት ሆኖ ለፍርድ ቤቱ እስቲሰጥ ድረስ ጠንቃቃ ቦታ መቀመጥ አለበት፡፡ የማያስፈልገው ማንኛውም እቃ ግን ደረሰኝ በመቀበል ለተወሰደበት ሰው ተመላሽ ይሆናል፡፡
- መርማሪ ፖሊስ ወይም ያፖሊስ ባልደረባ ብርበራ በሚያደርግበት ጊዜ አስፈላጊ የሆነውን ኀይል ብቻ መጠቀም ይችላል፡፡
- ከፍርድ ቤት በተለየ ካልታዘዘ በቀር ብርበራ ሚደረገው ከጥዋቱ 12 አዓት ጀምሮ እስከ ማታ 12 ስዓት ድረስ ብቻ ነው፡፡በማለት በህጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት በአለማቀፍ ህጎች፤ስምምነቶች እንዲሁም በአገራችን ሕግ መንግሥት እና ህጎች ጥበቃ እና እውቅና ያተሰጠው በመሆኑ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ብርበራን በሚያደርግበት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድርግ ያለበት ሲሆን ከሕግ አግባብ ውጪ ብርበራን ያደረገ እንደሆነ በወንጅል ህጉ አንቀጽ 422/ 1 እና 2 መሠረት እከከ ሰባት 7 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ