የአደንዛዥ እፆች የሰውን ልጅ ግንዛቤ እና የተፈጥሮ ባህሪይ በመቀየር ሰዎችን ለተለያዩ ችግሮች ሲዳርጉ ይስተዋላል። ህገ-ወጥ የአደንዛዥ እፆች ፣ የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድሀኒቶች ምርት፣ ዝውውር እና አጠቃቀም በእያንዳንዱ የዓለም ሀገራት ላይ ለተለያዩ ወንጀሎች መስፋፋት እና ለማህብረሰብ ሰላም፣ ፀጥታ እና ደኅንነት መደፍረስ ስጋት ከመሆን አልፈው ከፍተኛ የጤና፣ የኢኮኖሚዊ እና ማኅበራዊ ችግሮችን እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ መድሀኒቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋሉ በህክምናው አለም ለሰው ልጅ ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በመሆኑም የእነዚህን ንጥረ ነገሮች ምርት፣ ዝውውር እና አጠቃቀም በሕግ እና በጥንቃቄ መያዝ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል እና ለመቆጣጥር ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች እና አገራዊ ህጎች ለጉዳዩ ሽፋን ሰጥተው ይገኛሉ። በዚህ ጽሑፍ የአደንዛዥ እፆች ምንነት፣ የአደንዛዥ እፆች ተፅዕኖ፣ አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች እና ሀገራዊ ህጎች እንዲሁም ከአደንዛዥ እፆች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የሚያስከትሉትን የሕግ ተጠያቂነት እንመለከታለን።
የአደንዛዥ እፅ ምንነት
አድንዛዥ እፅ ማለት ከምግብ እና መጠጥ ውጪ የሆነ ወደ ሰውነት ውስጥ በሚገባ ጊዜ በሰውነት ሥራ ላይ አካላዊ ወይም ሥነ-ልቦናዊ ለውጥ የሚያስከትል ማንኛውም ንጥረ ነገር ነው፡፡ እፆች ህጋዊ የሆኑትን እንደ አልኮል፣ ካፌን እና ትንባሆ እንዲሁም ህጋዊ ያልሆኑ ወይም የተከለከሉ እንደ ካናቢስ፣ ኮኬን እና ሄሮኢን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሳይኮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች (Psychoactive drugs) በማዕከላዊ የአዕምሮ ክፍል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር የሰዎችን አመለካከት እና ባህሪይ ይቀይራሉ፡፡
እነዚህ ንጥረ ነጥሮች በአራት ሊከፈሉ የሚችሉ ሲሆን እነሱም ድብርት ፈጣሪ (Depressants)፣ አነቃቂ ወይም ቀስቃሽ (Stimulants)፣ ሀሉሲኖጅንስ (Hallucinogens) እና ሌሎች (Other) ናቸው፡፡ ድብርት ፈጣሪ ንጥረ ነገሮች የማዕከላዊ አዕምሮ ክፍልን እንቅስሴ ዝቅ በማድረግ ንቃትን ይቀንሳሉ (decrease alertness)፡፡ ቀስቃሽ ንጥረ ነገሮች ደግሞ በተቃራኒው አዕምሮን በማነቃቃት የሰውነትን መነቃቃት ይጨምራሉ (increase the body’s state of arousal):: ሃሉሲኖጅንስ በበኩላቸው የሰዎችን ግንዛቤ (perception) በመለወጥ ሰዎች የሌሉ ነገሮችን እንዲሰሙ እና እንዲያዩ ሊያደርጉ ወይም ከእውነት የራቀ ሃሳብ እንዲያስቡ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ የሌሎች (Other) የንጥረ-ነገሮች አይነት ስር የሚመደቡት ደግሞ ከላይ የተገለፁት ንጥረ ነገሮች ከአንድ በላዩን ባህሪዎች በአንድ ጊዜ ይዘው ሲገኙ ነው፡፡
የአደንዛዥ እፆች ተፅዕኖ (effects of drugs)
አደንዘዥ እፆች በሰዎች ላይ የሚያስከትሉት ውጤት በሰዎች ሁኔታ ማለትም አካላዊ ሁኔታ፣ እድሜ፣ ጾታ፣ ስሜት፣ አመጋገብ፣ አካላዊ ብቃትና የጤና ሁኔታ እንዲሁም እንደሚወሰዱበት ሁኔታ ከሰው ሰው የሚለያይ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ድብርታም፣ ተናዳጅ፣ ቁጡ፣ እንቅልፋም፣ የማይነቃቃ (unmotivated)፣ ጭንቀታም፣ ወሬኛ፣ የምግብ ፋላጎት የሌለው፣ አለፍ ሲልም ለአካላዊና አዕምሮ ጤና ችግር የተጋለጡ ይሆናሉ፡፡ በዚህም አደንዛዥ እፆች በተጠቃሚዎች ላይ ስሜታዊ እና ማኅበራዊ ችግሮችን በማስከተል ከቤተሰባቸው እና ከማህበረሰቡ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳይኖራቸው ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
በአደንዛዣ እፅ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ-ነገሮች ተጠቃሚዎችን ሱስ ውስጥ በማስገባት የእፆቹ ጥገኛ ያደርጋሉ፡፡ የአደንዛዥ እፅ ሱስ ማለት አንድ ሰው ራሱን መቆጣጠር እስኪያቅተው ድረስ የሱስ አምጭ ንጥረ ነገሮችን ለመውሰድ ፍላጎት ሲያድርበት እና ችግር የሚያስከትሉ እንደሆነ እያወቀ እነዚህን ንጥረ ነገሮች ሲወስድ ነው፡፡ ሱሰኛ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ለጤና ችግሮች መጋለጣቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ንጥረ ነገሮቹን ካላገኙ እራሳቸውን ማዘዝና ሥራ ማከናወን ይቸገራሉ፡፡ ይህም ሱሳቸውን ለማስተገስ አዘውትረው ወጪ እንዲያወጡ ስለሚያስገድዳቸው እራሳቸውም ሆነ ቤተሰቦቻቸው በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደርጋል፡፡
በአጠቃላይ አደንዛዥ እፆች በተጠቃሚዎች ጤና፣ የማኅበራዊ ግንኙነት እና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡
አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ዓለም ዓቀፍ ህጎች
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አደንዛዥ ዕፆችን መቆጣጠርን በተመለከት ሶስት ዋና ዋና ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ፡-
- የናርኮቲክ ንጥረ ነገር ነጠላ ኮንቬክሽን (the Single Convention on Narcotic Drugs of 1961 (as amended in 1972),
- የሳይኮትሮፒክ ንጥረ ነገሮች ኮንቬክሽን (the Convention on Psychotropic Substances of 1971), እና
- የተባበሩት መንግስታት ህገ-ወጥ የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ እፆች ዝውውር ቁጥጥር ኮንኔክሽን (the United Nations Convention against Illicit Traffic in Narcotic Drugs and Psychotropic Substances of 1988) ሲሆኑ ስምምነቶቹ እርስ በእርስ ተደጋጋፊ እና አንዱ አንዱን የሚያሟሉ (mutually supportive and complementary) ናቸው፡፡
በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት የአደንዛዥ እፅና ወንጀል ቢሮ (United Nations office on drugs and crime (UNODC)) በተባበሩት መንግስታት ስር የአለምን ሰላምና ፀጥታ፣ የሰብዓዊ መብቶች እና እድገትን ለማረጋገጥ አለምን ከአደንዘዥ እፅ፣ ከወንጀል፣ ከሙስናና ከሽብርተኝነት የመጠበቅ ተልዕኮን ይወጣል፡፡
በሀገራት ደረጃም አብዘህኛው የአለም አገራት የአደንዛዥ እፆችን ጥፋት (offenses) በተለያየ የወንጀል መለኪያ (standard) ቢሆንም በህጎቻቸው ውስጥ አካተው ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም የተጠቀሱት ስምምነቶች ፈራሚ ሀገር ከመሆኗም በላይ በህጎቿ ውስጥ ስለ አደንዛዥ እፆች ጥፋት አካታ ትገኛለች።
ጥፋቶቹ የአቅርቦት (supply) እንደ እርሻ፣ ማምረት (በፋብሪካ) እና ማዘዋወር እንዲሁም የፍላጎት (demand) እንደ መጠቀም እና መያዝን የሚያካትቱ ናቸው፡፡ ህጎች ተለይተው ጎጂ ናቸው የተባሉ ንጥረ ነገሮችን ወይም አደንዛዥ ዕፆችን ማምረትን፣ ማዘዋወርን፣ መጠቀም እና መያዝን ወንጀል የሚያደርጉ ሲሆን አተገባበራቸው ከሀገር ሀገር የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና ብሔራዊ ህጎቹ የዓለም ዓቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን መዋቅር የተከተሉ መሆን አለባቸው፡፡
አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ህጎች በኢትዮጵያ
በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ አደንዛዥ እፆችን ጨምሮ በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮችን ማምረትና ማሰራጨትን የተመለከቱ ወንጀሎችን አካቷል፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 525 መሠረት እንደተደነገገው መርዛማ ወይም የናርኮቲክና ሣይኮትሮፒክ መድኃኒቶችን ወይም እፆችን ማምረት፣ መሥራት፣ ማዘዋወር ወይም መጠቀም የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ደንግጓል፡፡ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች በድንጋጌው ሥር የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህም፡-
ማንም ሰው ልዩ ፍቃድ ሳይኖረው መርዛማ ነገሮችን ወይም ናርኮቲክ ወይም ሳይኮትሮፒክ መድሀኒቶችን ወይም እፆችን
- ያበቀለ፣ ያመረተ፣ የሰራ፣ የለዋወጠ ወይም የፈበረከ
- ንጥረ ነገሮቹን ይዞ የተገኘ፣ ወደ ሀገር ያስገባ ወደ ውጪ አገር የላከ፣ ያጓጓዘ፣ ያከማቸ፣ የደለለ፣ የገዛ፣ ለሽያጭ ያቀረበ፣ ያሰራጨ፣ ያዘዋወረ፣ አሳልፎ የሰጠ ወይም ለሌላ ያስገኘ፤
- ንጥረ ነገሮቹን ለማምረት፣ ለማቀነባበር ወይም ለመፈብረክ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን የሠራ፣ ይዞ የተገኘ፣ ወደ ሀገር ያስገባ ወይም ወደ ውጭ የላከ
- ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሆነበትን ቤቱን፣ ግቢውን ወይም ቦታውን ለንጥረ ነገሮቹ መስሪያነት፣ ማቀነባበሪያነት፣ ማምረቻነት፣ መሸጫነት ወይም ማከፋፈያነት የሰጠ፣ ያከራየ ወይም የፈቀደ
እንደሆነ ከ5 ዓመት በማያንስ ፅኑ እስራትና ከ100 ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል (አንቀጽ 525/1)፡፡
ቅጣቱን የሚያከብዱ ሁኔታዎ በአንቀጽ 525/2 ስር የተቀመጡ ሲሆን እነዚህም፡-
- ወንጀሉ የተፈፀመው ለዚሁ ንግድ ወይም በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወንጀል ለመፈፀም በተደራጀ የቡድን ወይም የማህበር አባል በሆነ ወይም ይህን ህገ-ወጥ ድርጊት ሙያው አድርጎ በያዘ ሰው እንደሆነ
- ጥፋተኛው የተከለከለውን ህገ-ወጥ ነገር ወይም ለዚሁ ዓይነቱ ነገር መጠቀሚያ ቦታ እያወቀ የሰጠ ወይም የፈቀደው በአፍቅሮ ንዋይ፣ በወራዳነት ወይም አግባብ በሌለው ሌላ ዓላማ እንደሆነ፣ ወይም ተጠቃሚው ህፃን፣ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ወጣት ወይም አዕምሮው ያልተስተካከለ ወይም የእፅ ሱስ ያለበት እንደሆነ
- ወንጀለኛው ወንጀሉን የፈፀመው ሕፃናትን ወይም አዕምሮው ያልተስተካከለ ሰውን ለወንጀል ድርጊቱ አፈፃፀም መጠቀሚያነት በማድረግ እንደሆነ
- ወንጀሉ የተፈፀመው በማረሚያ ቤት፣ በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ማኅበራዊ አገልግሎት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ ሕፃናት ወይም ወጣት ተማሪዎች ለትምህርት፣ ለስፖርት ወይም ለሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በሚጠቀሙበት ቦታ እንደሆነ ወይም
- ወንጀለኛው ከዚህ ቀደም በፈፀመው ተመሳሳይ ወንጀል ምክንያት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎበት የነበረ እንደሆነ
ከ10 ዓመት በማያንስ ፅኑ እስራት እና ከ200 መቶ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
መርዛማ ነገሮቹ ወይም ናርኮቲክ ወይም ሳይኮትሮፒክ መድሀኒቶቹ ወይም እፆቹ የተገኙት ከላይ በተዘረዘረት የወንጀል ተግባሮች በአንዱ አማካይነት መሆኑን ወይም ከተዘረዘሩት የወንጀል ተግባሮች አንዱን ለመፈፀም የታቀዱ መሆኑን እያወቀ እነዚህን ነገሮች ይዞ የተገኘ፣ ያጓጓዘ፣ ያከማቸ ወይም አሳልፎ የሰጠ እንደሆነ 5 ዓመት በማያንስ ፅኑ እስራትና ከ100 ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
በሌላ በኩል ለራሱ ወይም ሌላ ሰው በግል እንዲጠቀምበት በማሰብ ንጥረ ነገሮቹን ያበቀለ፣ የገዛ፣ የተቀበለ፣ የሰራ፣ ይዞ የተገኘ፣ የሸጠ፣ የሰጠ ወይም ከነዚህ ነገሮች በአንዱ ያለሕክምና ፈቃድ ወይም በማናቸውም ሌላ ህገ-ወጥ መንገድ የተጠቀመ ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀምባቸው ያደረገ እንደሆነ ከ7 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከ50 ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ የወንጀል ህጉ እንቀጽ 525/4 ይደነግጋል፡፡
ናርኮተክ ወይም ሳይኮትሮፒክ ነገሮችን ለህገ-ወጥ ዓላማ ለማዋል በማሰብ የህክምና ባለሞያን በማጭበርበር ማዘዣ እንዲሰጠው ያደረገ ወይም በህጋዊም ሆነ ህገ-ወጥ መንገድ ያገኘውን ማዘዣ ላልተፈቀደለት ሦስተኛ ወገን ያስተላለፈ ሰው ወይም የናርኮቲክ ወይም የሳይኮትሮፒክ ነገሮች ማዘዣ አስቦ በህገ-ወጥ መንገድ የፃፈ የህክምና ባለሞያ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡
ሌላው ለአደንዛዥ እፅ ሽፋን የሰጠው ሕግ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ሲሆን የናርኮቲክ እና የሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶች እንዲሁም የፕሪከርሰር ኬሚካል ለማምረት፣ ለማስመጣት ወይም ለመላክ እንዲሁም ለታካሚ ለማዘዝ ከሚመለከተው አካል የተለየ ፍቃድ እንደሚያስፈልግ በመዘርዘር ያስቀምጣል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 31 ስር ማንኛውም ሰው የናርኮቲክ መድኃኒት፣ የሳይኮትሮፒክ መድኃኒት ወይም የፕሪከርሰር ኬሚካል ለማምረት፣ ለማስመጣት፣ ለመላክ፣ ለማከፋፈል፣ ለማከማቸት፣ ለማጓጓዝ፣ ለመያዝ ወይም ለመሸጥ ከአስፈፃሚ አካሉ ልዩ ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት እና ይህን አዋጅ እና አዋጁን ለማስፈጸም የሚወጣን ደንብ እና መመሪያ በጥብቅ መከተል እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
እነዚህን መድሀኒቶች በፖስታ ቤት ወይም በመርከብ ወይም ከሌሎች መድኃኒቶች ወይም ዕቃዎች ጋር አንድ ላይ በማሸግ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት እና ማጓጓዝ ወይም ወደ ውጭ ሀገር መላክ የተከለከለ ነው፡፡ እንዲሁም በእነዚህ ንጥረ ነገሮች ሥራ ላይ የተሰማራ አምራች፣ አስመጪ፣ አከፋፋይ ወይም የችርቻሮ ድርጅት እና ጤና ተቋም በአስፈፃሚ አካሉ በሚወጣ መመሪያ መሠረት ከሥራው ጋር የተያያዙትን መረጃዎች መያዝ፣ የፍላጎት ትንበያ እና ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ ያለበት ሲሆን የግዥ ፈቃድ ከአስፈፃሚ አካሉ የወሰደ ማንኛውም ሰው ምርቱን ስለማስመጣቱ እንዲሁም በማንኛውም ምክንያት ምርቱን ያላስመጣ ከሆነ ለአስፈፃሚ አካሉ የግዥ ፈቃዱ ባበቃበት በአሥር ቀናት ውስጥ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 32 ስር የናርኮቲክ እና የሳይኮትሮፒክ መድኃኒት አስተዛዘዝ ሥርዓት በዝርዝር ተደንግጎ ይገኛል። በአዋጁ አንቀጽ 67 ደግሞ የአዋጁን ድንጋጌዎች መተላለፍ የሚያስከትለውን ቅጣት በዝርዝር አካቶ ይገኛል።
ለአብነት ያክል ማንኛውም ሰው ቁጥጥር የሚደረግበትን ምርት ደረጃውን ያልጠበቀ ወይም ያስተሻሸግ ጉድለት እንዲኖረው በማድረግ ወይም አስመስሎ በመሥራት ያመረተ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ያከማቸ፣ በጅምላ ያከፋፈለ ወይም በችርቻሮ የሸጠ ወይም በማንኛውም መንገድ ለኅብረተሰቡ ለአገልግሎት ያቀረበ፣ እንዲሰራጭ ያደረገ እንደሆነ ከ3 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና ከብር 200 ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ይህ ድርጊት በሰው አካል ወይም ጤና ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ቅጣቱ ከ7 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 20 እስከ ብር 300 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል። በሰው ላይ ሞት ያስከተ እንደሆነ ደግሞ ከ10 እስከ 20 ዓመት ፅኑ እስራት እና ከብር 30 ሺህ እስከ ብር 400 መቶ ሺህ ይቀጣል።
የአደንዛዥ እፆች በዘፈቀደ ጥቅም ላይ መዋል ዜጎችንም ሆነ ጠቅላላ ማህበረሰቡን ለጤና እክል፣ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚዳርግ በመሆኑ ህጉ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ደንግጓል፡፡ ስለሆነም ህጉ በአግባቡ እንዲፈፀም እና በአደንዛዥ እፆች ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን መከላከል እንዲቻል ማህበረሰቡም ሆነ ሕግ አስፈፃሚ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ