የስርቆት እና የመሸሸግ ወንጀሎች ተጠያቂነት

ማውጫ

Share this Article

ስርቆት በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መካከል በስፋት የሚፈፀምና በርካቶች ንብረታቸውን እንዲያጡ የሚያደርግ የወንጀል ተግባር ነው፡፡ ይህ ድርጊት በሀገራችን የወንጀል ሕግ በወንጀል የሚያስጠይቅ ከመሆኑም በተጨማሪ በስርቆት የተገኘን ንብረት መሸሸግም በተመሳሳይ ተጠያቂነት ያስከትላል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የስርቆት እና የመሸሸግ ወንጀሎችን ምንነትና የሚያስከትሉትን የወንጀል ተጠያቂነት እንመለከታለን፡፡

የስርቆት ወንጀል ምንነት

በወንጀል ሕግ አንቀጽ 665 መሠረት ስርቆት ማለት የማይገባን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላ ሰው ንብረት የሆነውን ተንቀሳቃሽ እቃ ወይም ከማይንቀሳቀስ ንብረት የተነጠለን እቃ አንስቶ መውሰድ፣ በቀጥታ የራስ ንብረት ማድረግ ወይም በተዘዋዋሪ ከራስ ንብረት ጋር እንዲቀላቀል ማድረግ ነው፡፡

የስርቆት ወንጀል የሚያስከትለው ቅጣት

በወንጀል ሕግ አንቀጽ 665 መሠረት ማንም ሰው የማይገባን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላ ሰው ንብረት የሆነውን ተንቀሳቃሽ እቃ ወይም ከማይንቀሳቀስ ንብረት የተነጠለን እቃ አንስቶ የወሰደ፣ በቀጥታ የራሱ ንብረት ያደረገ ወይም በተዘዋዋሪ ከራሱ ንብረት ጋር እንዲቀላቀል ያደረገ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እስራት ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ቀላል አስራት ሲባል በወንጀል ህጉ ጠቅላላ ክፍል በአንቀጽ 106 እንደተደነገገው ከ10 ቀን እስከ ሶስት ዓመት በልዩ ሁኔታ ደግሞ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ነው፡፡

ይህ የስርቆት ወንጀል የተፈፀመው ተንቀሳቃሹን ዕቃ ሰራቂው እራሱ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ነጥሎ በመውሰደው ከሆነ ወይም በወንጀሉ ምክንያት በተንቀሳቃሹ ወይም በማይንቀሳቀሰው ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ከሆነ ከስርቆት ወንጀሉ በተጨማሪ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 689 እስከ 691 በተደነገገው በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል በተደራቢነት በተጨማሪነት ይጠየቃል፡፡

በተጨማሪም በህጉ አንቀጽ 667 መሠረት በጋራ ንብረት፣ የሽርክና ወይም በወራሽነት ምክንያት የጋራ ሀብት በሆነ ንብረት ላይ የሚፈፀም የስርቆት ወንጀል የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ የሚያስቀጣ ነው፡፡

የስርቆት ወንጀል በህይወት ባለ ሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በሞተ ሰው ላይም ሊፈፀም ይችላል፡፡ በዚሁ መሠረት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 668 መሠረት ማንም ሰው ተገቢ ያልሆነ ብልፅግናን ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ከሙታን መቃብር ላይ ወይም ከመቃብር ቤት ውስጥ ወይም ከተቀበረ ወይም ካልተቀበረ አስከሬን ላይ እቃ የወሰደ እንደሆነ እንደ ወንጀሉ አፈፃፀም በቀላል እስራት ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ያስቀጣል፡፡

ከላይ ያነሳነው የስርቆት ወንጀል በመደበኛው ሁኔታ ሲፈፀም ስለሚኖር የሕግ ተጠያቂነት ነው፡፡ ከዚህ በከበደ መልኩ የስርቆት ወንጀል በተለየ አደረጃጀት እና በተጠና ሁኔታ ሲፈፀም ወንጀሉ ከባድ የሚሆንበትን ሁኔታ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 669 በዝርዝር ድንግጎ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት እንደወንጀሉ ክብደት እና በተሰረቀው እቃ አይነትና በአሰራረቁ አይነት ወዘተ ቅጣቱ የሚከብድ ይሆናል፡፡ እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከተዋለን፡፡

ወንጀሉ የሚመለከታቸው

  • የተሰረቀው እቃ የሀይማኖት ሥርአት የሚፈፀምበት ስፍራ ውስጥ የሚገኝ የሀይማኖት እቃ፣ በቤተመዘክር ውስጥ የተቀመጠ እቃ፣ ለሕዝብ ክፍት በሆነ ሕንጻ ውስጥ የተቀመጠ ሳይንሳዊ፣ ኪነጠበባዊ ወይም ታሪካዊ ዋጋ ያለው እቃ ከሆነ
  • የተለየ ጥበቃ የሌለው እንሰሳ ወይም ሰብል ወይም ቴሌኮሚኒኬሽን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለውሃና ፍሻስ ወይም ለማንኛም ሌላ ድርጅት አገልግሎት የሚውል ጠባቂ የሌለው መሳሪያ ወይም እቃ ወይም እንዲቀመጥ ወይም እንዲላክ ለእቃ ማከማቻ ፣ ለአንድ ድርጅት ወይም የመንግሥት መስሪያ ቤት በተለይም ለፖስታ ቤት ወይም ለማመላለሻ ድርጅት የተሰጠ ሸቀጥ ወይም እቃ እንደሆነ

ወንጀል የተፈፀመበት ሁኔታ

  • የመከላከያ ሰራዊት አባል ሆኖ ወንጀሉን የፈፀመው በጓደኞቹ ወይም በአለቆቹ ላይ ሲሆን ወይም የተሰረቀው እቃ ሰራዊቱን የሚያገለግል ሲሆን ወይም እንዲያገለግል የተመደበ ሲሆን
  • የመንግሥት ሠራተኛ ወይም አንድ የንግድና ይህን የመሳሰሉ ልዩ ሥራ የሚያከናውን ሰው የባንክ ሠራተኛ፣ ጠበቃ፣ ውል አዋዋይ፣ ወኪል፣ የተሰጠውን የንግድ ሥራ እያከናወነ የሚገኝ የንግድ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ድርጊቱን የፈፀመው በተለይ በተሰጠው ሥልጣን ምክንያት በእጁ በገባው የመንግሥት፣ የሕዝብ ወይም የግል ንብረት ላይ ሲሆን
  • በሆቴል፣ የቤት አከራይ፣ እቃ አመላላሽ፣ ተሸካሚ ወይም ይህን የመሳሰለ ሥራ የሚያካሂድ ሆኖ የተሰረቀው ንብረት የደንበኛው ሲሆን፣
  • የቤት ሠራተኛ፣ ሠራተኛ ወይም ሥራ ለማጅ ሆኖ ሥራውን ምክንያት በማድረግ በአሳዳሪው ወይም በአሰሪው ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ ሲሆን

ወንጀል አድራጊው

  • በሰዎች ወይም ንብረት ላይ ወንጀል ለመፈፀም የተቋቋመ ቡድን አባል ሲሆን
  • ስርቆቱን የፈፀመው በተለይ አደገኛ መሆኑን በሚያሳይ በማናቸውም ሌላ ሁኔታ ይልቁንም የማጥቂያ ወይም የመከላከያ የጦር መሳሪያ ወይም የቤት መሰርሰሪያ በመያዝ ሲሆን፣ ወይም በሌሊት ወይም ቅጥር በመጣስ፣ አጥር በመዝለል፣ በር በመስበር፣ ግድግዳ በመሰርሰር፣ በቡድን በመሆን ሲሆን ወይም ያልተጠበቀ አደገኛ ሁኔታን፣ የሕዝብ ብጥብጥን ወይም መቅሰፍትን ይልቁንም እንደግርግር፣ ቃጠሎ፣ ጎርፍ፣ ማእበል የመሳሰለውን ሽፋን በማድረግ የተፈፀመ ሲሆን

ድርጊቱ ከባድ የስርቆት ወንጀል የሚሆን ሲሆን ቅጣቱም እንደ ወንጀሉ አፈፃፀም ከአንድ ዓመት የማያንስ ቀላል እስራት ወይም ከአስራ አምስት ዓመት የማይበልጥ ፅኑ እስራት ይሆናል፡፡

የመሸሸግ ወንጀል ምንነት

በአንፃሩ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 682 መሠረት የስርቆት ወንጀል ማለት በንብረት ላይ በተፈፀመ ወንጀል የተገኘን ንብረት መሆኑን እያወቁ ይህንኑ እቃ መግዛት፣ በተውሶ፣ በስጦታ ወይም በመያዣነት መቀበል፣ በመሰል አኳኋን መውሰድ፣ መገልገል፣ ማስቀመጥ፣ መደበቅ፣ አሳልፎ መሸጥ፣ በመሸጥ መለወጡ ውስጥ አገናኝ ሆኖ መርዳት፣ በስርቆት ወንጀል በተገኘው እቃ ምትክ በልዋጩ የተገኘን ወይም በሽያጩ ዋጋ የተገዛን ሌላ ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ መቀበል ነው፡፡

የመሸሸግ ወንጀል የሚያስከትለው ቅጣት

በወንጀል ህጉ አንቀጽ 682 መሠረት ማንም ሰው በንብረት ላይ በተፈፀመ ወንጀል የተገኘን ንብረት መሆኑን እያወቀ ይህንኑ እቃ የገዛ፣ በተውሶ፣ በስጦታ፣ በመያዣነት የተቀበለ፣ በመሰል አኳኋን፣ የወሰደ፣ የተገለገለ፣ ያስቀመጠ፣ የደበቀ፣ አሳልፎ የሸጠ፣ በመሸጥ መለወጡ ውስጥ አገናኝ ሆኖ የረዳ፣ በወንጀል ተግባር በተገኘው እቃ ምትክ በልዋጩ የተገኘን ወይም በሽያጩ ዋጋ የተገዛውን ሌላ ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ ተቀብሎ ከላይ የተገለፁትን ድርጊቶች ከፈፀመ እንደ ወንጀሉ አፈፃፀም በቀላል አስራት ወይም ነገሩ ከባድ ሲሆን ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ ያስቀጣል፡፡

የመሸሸግ ድርጊቱ የተፈፀመው በቸልተኝነት ከሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል፡፡ የመሸሸግ ወንጀሉ በተደራጀ ቡድን ሲፈፀም፣ የንግድ ሥራ ፈቃድን እንደሽፋን በመጠቀም ከሆነ፣ ንብረቱን የሸሸገው፣ የውንብድና፣ የዘረፋ፣ የቅሚያ፣ የማስፈራራት ፍሬ ወይም እቃው ከመከላከያ ሰራዊት ንብረት ወይም ከመንግሥት ሀብት ውስጥ መሆኑን እያወቀ ከሆነ በህጉ አንቀጽ 683 መሠረት የእስራት ቅጣቱ እስከ አስራ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት መቀጮውም እስከ ብር ሃያ ሺህ የሚደርስ ይሆናል፡፡

የስርቆት ሆነ የመሸሸግ ወንጀሎች ከባህል፣ ከሞራል፣ ከእምነት እና ከሕግ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ማህበረሰቡ እራሱን ከወንጀሎቹ ማቀብ፣ ልጆቹን በሥነ ምግባር ማሳደግ እና ለፍትሕ ሂደቱ የበኩሉን እርዳታ ማድረግ የሚጠበቅበት ሲሆን የፍትሕ አካላትም ወንጀሎቹን በመከላከል እና አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ