መግቢያ
ማንም ሰው ባደረገው ድርጊት ወይም ግድፈት በሌሎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ የፍትሐ ብሔር ወይም የወንጀል አለያም በሁለቱም ተጠያቂነት ሊያስከትልበት ይችላል። አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ ክስ ሊቀርብበት እና ሊቀጣ የሚችለው የተላለፈውን የወንጀል ድርጊት ሊያቋቁሙ የሚችሉት ህጋዊ፤ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ባንድ ላይ ተሟልተው ሲገኙ ብቻ እንደሆነ የኢ.ፌ.ድ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 23/2/ ይደነግጋል። በዚህ መሠረት የወንጀል ፈጻሚው የሀሳብ ክፍል (moral element) መረጋገጥ ያለበት አንዱ እና ዋናው የወንጀል ማቋቋሚያ መስፈርት ሊሆን የቻለው ሰውን ባላወቀውና መቆጣጠር በማይችለው ጉዳይ መጠየቅ ወይም መቅጣት ፋይዳ የሌለው ስለሆነ ነው። ስለዚህ የሀሳብ ክፍል አለመሟላት እንደመከላከያ ወይም ከኃላፊነት ነፃ ማድረጊያ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ የሚችልበት አግባብ ይኖራል።
በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ፅሑፍ ስለወንጀል ኃላፊነት እና ኢ-ኃላፊ መሆን እንዲሁም በስካር መንፈስ ስለተፈፀመ የወንጀል ድርጊት አስጠያቂነት ለመዳሰስ እንሞክራለን።
የወንጀል ኃላፊነት እና ኢ-ኃላፊነት
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ወንጀል ፈፃሚዎችን በወንጀል ከሶ ለማስቀጣት የሀሳብ ክፍላቸው መረጋገጥ ይኖርበታል። ይህ እንዳለ ሆኖ በወንጀል ሕግ የሀሳብ ክፍልን መሠረት በማድረግ ለፈፀሙት ድርጊት ኃላፊነት የሚኖርባቸውና የማይኖርቸባቸው ሰዎች አሉ። ላደረጉት ድርጊት ኃላፊ የሚሆኑት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? ኃላፊነት የማይኖርባቸውስ እነማን ናቸው? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ያለበት ወሳኝ ጉዳይ ነው። የኢ.ፌ.ድ.ሪ. የወንጀል ሕግ “በወንጀል ሕግ መደበኛ ድንጋጌዎች መሠረት የሚቀጣው ላደረገው ድርጊት ኃላፊ የሆነው ወንጀል አድራጊ ብቻ ነው” ሲል በጥቅሉ ደንግጎ ይገኛል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 48(1))። ከዚህ መረዳት የሚቻለው የተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወንጀል ፈፅመው ቢገኙ እንኳን ኃላፊነት የለባቸውም የወንጀል ቅጣትም አይተላለፍባቸውም እንደማለት ነው።
እነዚህ ሰዎች የወንጀል ኃላፊነት የማይኖርባቸው የድርጊታቸውን ባሕሪና የሚያስከትለውን ውጤት መገንዘብ የማይችሉ በመሆናቸው ነው። በመሆኑም በእድሜ፣ በህመም፣ ባልተለመደ የእድገት መዘግየት፤ ጥልቅ በሆነ የአእምሮ የመገንዘብ ወይም የማመዛዘን ችሎታ መቃወስ ወይም በማናቸውም ስነ ህይዎታዊ ዘዴ ድርጊቱ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ለመገንዘብ የማይችል እንደሆነ ይህም ፍርድ ቤት ቀርቦ ችግሩ ስለመኖሩ በበቂ ማስረጃ ሲረጋገጥ ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ እንደሚሆን የወንጀል ህጋችን አንቀጽ 48 ስር ተደንግጓል።
ይህ ችግር ማለትም እራስን ያለመቆጣጠር ወይም የድርጊትን ውጤት ያለመገንዘብ ችግር በከፊል ሲሆን የወንጀል ተጠያቂነቱም እንዲሁ በከፊል እንደሚተገበርበት ከአንቀጽ 49 መረዳት ይቻላል። ስለዚህ በአዋቂ ሰዎች ላይ የአእምሮ ጤናቸው ያልተስተካከለ በመሆኑ ወይም በስካር ምክንያት የተፈፀመ ድርጊት ሲሆን ከወንጀል ኃላፊነት በሙሉም ሆነ በከፊል ነፃ ሊሆኑ ሲችሉ በዕድሜ ምክንያትም እጅግም ሲያንሱ ከ9 ዓመት በታች ሲሆኑ አለያም በዕድሜ መጃጀት ምክንያት የድርጊታቸውን ውጤት ማገናዘብ የማይችሉ ከሆነ ኃላፊነት አይኖርባቸውም።
የወንጀል ኃላፊነት የሌለባቸው ሰዎች ከኃላፊነት ነፃ የሚሆኑት ለድርጊታቸው ኃላፊነት የማይወስዱ ስለመሆናቸው በማስረጃ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። የማስረዳት ሸክምን አስመልክቶ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን ልብ ልንል ይገባል። አንደኛው የወንጀል ድርጊት ስለመፈፀሙ እና በማን እንደተፈፀመ በበቂ ሁኔታ የማስረዳት ሸክም ያለበት አካል ከሳሹ (ዐቃቤ ሕግ) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለተፈፀመው የወንጀል ድርጊት ፈፃሚው አካል ኃላፊነት እንዳለበት የሕግ ግምት የሚወሰድበት ቢሆንም ይህ የሕግ ግምት ሊስተባበል የሚችል (Rebuttable Legal Presumption) የሕግ ግምት ስለሆነ ኃላፊነት የለብኝም የሚለው አካል በምን ምክንያት ኃላፊነት እንደማይኖርበት የማረጋገጥ ወይም የማስረዳት ሸክሙ የተከሳሹ ይሆናል።
በስካር የተፈፀመ ወንጀል ተጠያቂነት
ሰዎች በአልኮል መጠጦች ወይም አእምሮን በሚያደነዝዙ ንጥረ ነገሮች የማመዛዘን አቅማቸውን ሊያጡ እና በዛ ጊዜ የሚፈፅሙት ድርጊት ስለሚያስከትለው ውጤት በአግባቡ ላይረዱ ይችላሉ። ቢሆንም በስካር መንፈስ ተሁኖ የሚፈፀም የወንጀል ድርጊት ፈፃሚውን በኃላፊነት ሊያስጠይቅም ላያስጠይቅም የሚችልበት አግባብ ይኖራል።
ስለዚህ በአልኮል ወይም በሌላ አዕምሮን በሚያደነዝዝ ነገር መስከር የአእምሮ የመገንዘብ ወይም የማመዛዘን ችሎታ መቃወስ ሊያስከትል ቢችልም ከጉዳዩ ልዩ ባህሪ አንፃርም በመስከር በሚፈጸም ወንጀል ስለሚኖር በወንጀል ኃላፊነት፤ ፍፁም ወይም ከፊል ኢ-ኃላፊነት ሊያስጠይቅ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት በስካር ውስጥ ሆነው የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች እንደየሁኔታው ከሙሉ ኃላፊነት እስከ ከፊል ኃላፊነት ወይም ሙሉ በሙሉ ኢ-ኃላፊ ናቸው በሚል በፍርድ ቤቶች ውሳኔ ይሰጣል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ተከሳሾች ወንጀሉን የፈጸምኩት ሰክሬ ነው፤ ኃላፊነት የለብኝም በሚል የሚከራከሩ እና በዚሁ መሠረት ውሳኔ ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መከራከሪያ ከመቅረቡ በፊትም ሆነ በዚህ መከራከሪያ መሠረት ውሳኔ ለመስጠት የሚከተሉት ነጥቦች በሚገባ መታየት አለባቸው (አንቀጽ 50)። ይኸውም ግለሰቡ የሰከረው እና ድርጊቱን የፈፀመው፡-
• በራሱ ፍላጐት ወንጀሉን ለመፈፀም በማቀድ ወይም ሊፈፅም እንደሚችል እያወቀ መሆኑ፣ ወይም
• የመስከር ድርጊቱ ወንጀል ለመፈፀም እራሱን እንደሚያጋልጥ እያወቀ፣ ማወቅ እየቻለ ወይም ማወቅ እያለበት በራሱ ጥፋት ስለመሆኑ፣
• በቸልተኝነት እራሱን ወደ ከፊል ወይም ፍፁም ኢ-ኃላፊነት ካስገባ በኋላ ሊያደርግ ያልፈቀደውን ወይም ያላሰበውን ወንጀል ስለማድረግ አለማድረጉ 50/3/፤ 59 እና 491፣ ወይም
• ምንም ጥፋት ሳይኖረው (ተገዶ) በፍፁም ኢ-ኃላፊነት ውስጥ ባለበት ጊዜ የፈፀመው ድርጊት ስለመሆን አለመሆኑ የሚሉት ነጥቦች በሚገባ ግምት ውስጥ መግባት አለባቸው።
ከሁሉም በላይ ግን የተከሳሽን ፍፁም ወይም ከፊል ኢ-ኃላፊነት ማስረዳት ያለበት ማን እና በምን ሁኔታ ነው የሚሉትን ነጥቦች ከወንጀል ህጉ አንቀጽ 51 መሠረታዊ ሀሳቦች ማየት ተገቢ ይሆናል። እነዚህ ነጥቦች ባብዛኛው የሰውን ልጅ ውስጣዊ የእምሮ ማገናዘብ እና የማመዛዝን ደረጃን እና ሁኔታን የሚመዝኑ በመሆኑ የሚረጋገጡትም ጠንከር ባለ እና በበቂ ማሰረጃ አንዳንዴም በሞያ ማስረጃ (expertise witness) ሊሆን ይችላል፡፡ በመሠረቱ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 51(1) ድንጋጌ በግልፅ እንደሚያመለክተው አንድ ሰው በስካርም ይሁን በሌላ ምክንያት አንድን ድርጊት ሲፈፅም በከፊል ወይም በፍፁም ኃላፊ ስለመሆኑ አጠራጣሪ ነገር ሲኖር ልዩ የአዋቂ ምርመራ በፍ/ቤት ትእዛዝ መሠረት ሊጣራ የሚገባው ስለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው አልኮል አልኮል በመሽተቱ፣ በመኮላተፉ እና በመንገዳገዱ ምክንያት በፍፁም ኢ-ኃላፊነት ውስጥ እራሱን አስገብቶ ነበር ብሎ መደምደም ተገቢነት ያለው አይደለም፡፡ ይህም ተከሳሽ በመስከሩ እና ማገናዘብ ባለመቻሉ ምክንያት ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ፍ/ቤት አዝዞ በልዩ የአዋቂ ምርመራ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በግምት ተከሳሽ ፍፁም ኢ-ኃላፊነት ነበረው ወደሚለው መደምደሚያ ይወስደናል፡፡ በሌላ በኩል የተከሳሽን መስከር በምስክሮች ቃል አረጋግጫለሁ ቢባል እንኳን (ምስክሮች በጉዳዩ ላይ ልዩ አዋቂ አለመሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) ተከሣሽ ወደ ፍፁም ኢ-ኃላፊነት የገባው ከላይ በተገለፀው አግባብ ድርጊቱን ለመፈፀም በማቀድ፣ ወይም ሊፈፅም እንደሚችል እያወቀ አስቦ እራሱን ወደ ፍፁም ኢ-ኃላፊነት አስገብቶ ከሆነ እነዚህ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የማይሆኑለት እና በመደበኛ ድንጋጌዎች መሠረት ሊከሰስ እና ሊቀጣ የሚገባው ስለመሆኑ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 50/1/ ድንጋጌ ያስረዳል፡፡ በአንፃሩ ተከሣሽ የወንጀል ድርጊቱን ለመፈፀም እራሱን እንደሚያጋልጥ እያወቀ ወይም ለማወቅ እየቻለ ወይም ማወቅ እያለበት በራሱ ጥፋት ወደ ፍፁም ኢ-ኃላፊነት ወይም ከፊል-ኃላፊነት እራሱን ካስገባ በኋላ ድርጊቱን የፈፀመ እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 50/2/ እና 59 መሠረት በቸልተኝነት በፈፀመው ድርጊት ተጠያቂ ይሆናል። ይህም ሆኖ ግን በቸልተኝነት የተፈፀመ የወንጀል ድርጊት ከተደረገው ጥፋት ዓይነት፣ ከወንጀሉ ከባድነት ወይም ሊያደርስ ከሚችለው አደጋ አንፃር በተለይ በቸልተኝነትም ቢፈፀሙ ያስቀጣሉ ተብለው ከተደነገጉት ውጪ በሁሉም የወንጀል ዓይነቶች ላይ ስለማያስቀጣ ሆን ብሎ ሰክሮ ወንጀል መፈፀም ሁሌም የሚያስቀጣ ድርጊት ሳይሆን ከላይ በተገለፀው አግባብ እንደወንጀሉ ሁኔታ እየታዬ የሚፈፀም ይሆናል።
በሌላ በኩል አድራጊው በገዛ ጥፋቱ ወደ ፍፁም ኢ-ኃላፊነት እራሱን ካስገባ በኋላ ያልፈቀደውን ወይም ያላሰበውን የወንጀል ድርጊት ከፈፀመም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 491 መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆን የወንጀል ህጉ አንቀጽ 50/3/ ስር ተደንግጓል። ከዚህ ባለፈ ግን ግለሰቡ ምንም ጥፋት ሳይኖርበት ወይም በሌላ ሰው ተገዶ በፍፁም ኢ-ኃላፊነት ውስጥ ከገባ በኋላ የወንጀል ድርጊት ቢፈፅም የወንጀል ተጠያቂነት የሌለው ስለመሆኑ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 50/4/ ድንጋጌ ያስቀምጣል።
ስለሆነም አንድ ሰው በወንጀል ተከሶ ድርጊቱን የፈጸመው በስካር ውስጥ መሆኑ ቢረጋግጥ እንኳን ወደ ስካር የገባው ወንጀሉን ለመፈጸም አቅዶ ስለመሆኑ ወይም በሶስተኛ ወገን ተገፋፍቶ ስለመሆኑና አለመሆኑ ወይም ስለኃላፊነት መጠኑ በአግባቡ በማስረጃ መረጋገጥ ያለበት ይሆናል ማለት ነው።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በስካር የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች በመርህ ደረጃ ከወንጀል ተጠያቂነት የማያድኑ በመሆኑ ዜጎች ይህንን ተገንዝበው ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ስካር እና የወንጀል ኃላፊነት በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው እና የማስረጃ ደረጃውም ከተለመደው የማስረጃ አቀራረብ ላቅ ያለ የአዋቂ ማስረጃን የሚጠይቅ በመሆኑ ተከሳሾች፣ ዐቃቤያነ ህጎችም ሆነ ዳኞች በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው ማየት ተገቢ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።