በሀገራችን የበየነ-መረብ ተደራሽነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የበየነ መረብ ተጠቃሚ እንዳለ ይገመታል፡፡ የበየነ-መረብ አጠቃቀምን የሚመለከት በመደበኛ የወቅቱ የተደራጀ የስታስቲክስ መረጃን ከህጻናት አንጻር ተቃኝቶ ባይገኝም፤ ከተጠቃሚዎች ቁጥር ውስጥ ሕጻናትም ከዚሁ የበየነመረብ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ እየተቀላቀሉ መሆናቸው ከቤታችን እና ከአካባቢያችን ካሉ ህጻናት ውሎ ጀምረን መታዝብ እንችላለን፡፡
ህጻናት የበነ-መረብ ተጠቃሚ ሆነው ማደጋቸው በመላው ዓለም ዙሪያ ስላለው ክንውን ያላቸውን ግንዛቤ እንዲሰፋ፣ የፈጠራ ችሎታቸው እንዲዳብር እና የማኅበራዊ ትስስር ክህሎታቸው ለማሳደግ ዕገዛ የሚያደርግ ነው፡፡ በዛው መጠን አሉታዊ የሆኑ ተግባራትም በበየነ-መረብ አማካኝነት የሚተላለፉ በመሆኑ በህጻናቱ ሁለንተናዊ ደኅንነት ላይ ስጋት ይፈጥራል፡፡
እነዚህ ስጋቶች በማኅበራዊ ድረ–ገጾች ወይም በፈጣን የመልዕክት መለዋወጫዎች ውስጥ በገቡ ቁጥር በበየነ-መረብ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ለወሲባዊ ብዝበዛና በደል፣ ለጥላቻ ንግግር፣ ለህገ-ወጥ ዝውውር ወንጀሎች እና ለዓመጽ ይዘት ላላቸው ምስሎች ሊጋለጡ ይችላሉ ይህም በራስ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን ጨምሮ ሊደርሷቸው ይችላሉ፡፡
በህጻናት ላይ በበየነ-መረብ ስለሚፈጸም ወሲባዊ ብዝብዛና በደል ድርጊት የዲጂታል የበየነ-መረብ እና የተግባቦት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚፈጸም ሲሆን የወሲብ ዓላማ ያላቸው ፎቶዎች ቪዲዎችና ድምጾች ወይም ሌሎች ቀረጻዎች ማዘጋጀትና ማጋራት፣ በዲጂታል ዕገዛ የተዘጋጀ የህጻናት ላይ ወሲባዊ በደል ሲካሄድ ወይም ህጻናት ይህንን ድርጊት ሲፈጽሙ የሚያሳይ ማናቸውም አቀራረቦች እንዲሁም ህጻናቱን ለወሲብ በማስገደድ መጠቀም ወይም ይህንና መሰል ድርጊቶችን ለመፈጸም በማለም፤ ከህጻናት ጋር በቴክኖሎጂ አማካኝነት የሚደረግ መስተጋብር እንዲጋለጡ በማድረግ የወንጀል ጥቃት ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በመሆኑም ህጻናትን እንደዚህ ዓይነቱ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል እና ምላሽ ከመስጠት አንጻር ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሕግ አስከባሪ መስሪያ ቤቶች፣ ሌሎች ባለድርሻ የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ እና የተግባቦት ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ የእርምጃዎችን በመወሰድና በቅንጅት በመሥራት ለህጻናት ሁለንተናዊ ደኅንነት ኃላፊነታቸውን መወጣት መቻል ይኖርባቸዋል፡፡