ሰብዓዊ መብቶች

ማውጫ

Share this Article

የሰብዓዊ መብቶች ጅማሮ ከጥንታዊ የግሪክ ፍልስፍና እና ከኃይማኖቶች አስተምህሮ እንደሆነ ፅሑፎች ያወሳሉ፡፡ ከ6ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ የተለያየ ይዘት ያላቸው የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች የነበሩ ቢሆንም የሰብዓዊ መብት እንደ አንድ አጀንዳ (ጉዳይ) እራሱን ችሎ መቆም የቻለው ግን ከ18ኛው ክ/ዘመን (በዘመነ አብርሆት) ጀምሮ ነው፡፡ በአውሮፓ የአናሳ መብቶች ለመጠበቅ በሚደረግ ጥረት በሀገራት መካከል ተከታታይ ግጭቶች ይደረጉ ነበር፡፡ በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት የዓለማቀፍ ጣልቃ ገብነት እንዲኖርና አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ስርዓት እንዲዘረጋ አስገድዷል፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ ሰብዓዊ መብቶችን የተመለከቱ ጠቅላላ ፅንሰ ሀሳቦች ማለትም ስለሰብዓዊ መብቶች ምንነት፣ መገለጫ ባሕሪያት እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶችን ከማስከበር አኳያ የመንግስታት ኃላፊነት ምን እንደሚመስል እንዳስሳለን፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ምንነት

መብት የሚለውን ቃል የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል ባሳተመው የአማርኛ መዝገባ ቃለት “አንድ ሰው አስፈላጊ ሆኖ ሲያየው ሊያገኘው የሚገባ ነገር፣ አገልግሎት፣ ጥቅም…” በማለት ተርጉሞታል፡፡ የሰብዓዊ መብቶችም የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ምክንያት ያገኛቸው ጥቅሞች ናቸው ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ “ሰብዓዊ መብት” የሚለው ሐረግ አንድን መብት ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ከሕይወት የመኖር መብት ጀምሮ እስከ የባሕል መብት ድረስ ያሉትን በርካታ የመብት ዓይነቶችን አጠቃሎ የሚይዝ ጥቅል መጠሪያ ነው፡፡

የሰብዓዊ መብት መለያ ባህሪያት፡-

ሰብዓዊ መብቶች በርካታ መለያ ባህሪያት ያሏቸው ሲሆን ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • ፈጥሮአዊነት (Inherent)፡- ሰብዓዊ መብቶች በማንኛውም የመንግሥት አካል ወይም በማንኛውም ሰው የሚሰጡ ሳይሆን የሰው ልጅ በተፈጥሮ የሚያገኛቸው በመሆኑ ተፈጠሮአዊ ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች የሚገኙት በስጦታ፣ በግዢ ወይም በውርስ ሳይሆን የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ካለው ክብር እና ዋጋ የተነሳ ነው፡፡
  • ሁሉን አቀፋዊነት (universality)፡- ሰብዓዊ መብቶች በመላው አለም ለሚገኙ ሰብዓዊ ፍጡራን ተመሳሳይ ክብርና እውቅና የሚሰጡ መብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች ለሁሉም የዓለም ህዝቦች በሙሉ የተከበሩ እና እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን በማንኛውም መሠረት ልዩነት ሊደረግባቸዉ የማይችል የሰው ልጆች በሙሉ ሰው በመሆናቸው ሊጠቀሙባቸዉ የሚችሉ መብቶች ናቸዉ፡፡ ስለሆነም ሰብዓዊ መብቶች በዘር፣ በቀለም፣ በሀይማኖት፣ በጾታ፣ በልደት፣ በሀብት ደረጃ ወይም በሌላ ልዩነት ሳይደረግ መከበር አለባቸዉ፡፡
  • የማይገፈፉ ወይም የማይገረሰሱ ናቸው (inalienable)፡- ሰብዓዊ መብቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው ከማንም ሰው ላይ ሊገፈፉ ወይም ሊገረሰሱ አይችሉም፡፡ ማንም ሰው የማንንም ሰው ሰብዓዊ መብት ሊነጥቅ ካለመቻሉም በላይ ሰዎች እነዚህን መብቶችን አሳልፈው ሊሰጡም አይችሉም፡፡
  • የማይነጣጠሉና ተደጋጋፊ ናቸው (indivisible and interdependent)፡- ሰብዓዊ መብቶች እርስ በእርስ የተደጋገፉ እና የተያያዙ በመሆናቸው በሰብዓዊ መብቶች ውስጥ ተዘርዝረው የሚገኙ ሁሉም መብቶች በአንድነት መከበር እና እውቅና ማግኘት አለባቸው፡፡ እነዚህን መብቶች ነጣጥሎ ማክበር ወይም እውቅና መስጠት አይቻልም፡፡ ሰዎች ሙሉ ሆነው ይኖሩ ዘንድ ሁሉም ሰብዓዊ መብቶች ያለምንም መነጣጠል እና መሸራረፍ ሊከበሩላቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም የአንደኛው መብት መጣስ የሌላኛውንም መብት መጣስ ይዞ ስለሚመጣ እና ይህ መጣስ ከሰብዓዊነት ክብር ዝቅ ያለ ኑሮን ስለሚያስከትል ነው፡፡ እንዲሁም ለአንዱ መብት መሟላት የሌላኛው መብት መከበር ወይም መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
  • መሠረታዊነት (Fundamental)፡- የሰብዓዊ መብቶች መሠረታዊ በመሆናቸው የእነዚህ መብቶች አለመከበር የሰው ልጆች ክብርና ሕይዎት ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ተራ ፍላጎቶችና ምኞቶች ሳይሆኑ የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በክብር ይኖር ዘንድ ወሳኝ ናቸው፡፡

ሰብዓዊ መብቶችን ከማክበር አንፃር የመንግስታት ኃላፊነት፡-

ሀገራት ለሰብዓዊ መብቶች ተፈፃሚነት ከፍተኛ ሚና እና ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን ኃላፊነታቸውን ወይም ያለባቸውን ግዴታ በአጠቃላይ በሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡እነዚህም፡-

  • ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር ግዴታ (obligation to respect)፡- በሰብዓዊ መብቶች ተጠቃሚነት ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ አለባቸው፡፡ (refrain from interfering with the enjoyment of the right)
  • ሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅ ወይም የማስከበር ግዴታ (obligation to protect)፡- ሌሎች ሰዎች በሰዎች የሰብዓዊ መብት ተጠቃሚነት ጣልቃ እንዳይገቡ የመጠበቅ ወይም የመከላከል ግዴታ (prevent others from interfering with the enjoyment of the right)
  • ሰብዓዊ መብቶችን የማሟላት (obligation to fulfill)፡- የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶችን ተፈፃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ አለባቸው፡፡ (adopt appropriate measures towards the full realization of economic, social and cultural rights)

ማጠቃለያ

ሰብዓዊ መብቶች የሰው ልጆች ሰው በመሆናቸው ብቻ ያገኟቸው መብቶች እንደመሆናቸው ሳይሸራረፉ ሊከበሩ የግድ ነው፡፡ በመሆኑም ለመብቶቹ መከበር መንግሥትም ያለበትን የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነት ሊወጣ እንዲሁም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ