በማስገደድ መጠቀም የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት

ማውጫ

Share this Article

መግቢያ

ከሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶች መካከል ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ ሆኖ የመኖር መብት አንዱ ነው፡፡ ወንጀል በሰው ልጆች ነጻነት፣ አካል ወይም ንብረት ላይ ሊፈፀም የሚችል እኩይ ተግባር ሲሆን የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ጉዳትን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል አንደኛው እና ዋናው የፍትሕ አካላት እና የህብረተሰብ ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የወንጀል ድርጊት ተፈፅሞ ሲገኝ ደግሞ ተገቢውን ህጋዊ የእርምት እና የቅጣት እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም የወንጀል ሕግ ወንጀል ናቸው ብሎ እንዳይፈፀሙ የከለከላቸውን ወይም ደግሞ ያለመፈፀም ወይም ያለማድረግ የወንጀል ኃላፊነት እንደሚያስከትል የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ማክበር ግድ ይላል፡፡ በ1996ዓ.ም በወጣው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ለንብረት ጥበቃ ከሚያደርጉ እና በንብረት እና በነጻነት ላይ ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎች ከሚዘረዝሩ ድንጋጌዎች መካከል በሞራል ወይም በቁሳቁስ ማስፈራራትን የሚያካትት በማስገደድ መጠቀም ወንጀል አንዱ ነው፡፡ በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ጽሑፍ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ የተካተቱ በማስገደድ መጠቀም ወንጀል ምንነትና የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት ይዳሰሳል፡፡

በማስገደድ መጠቀም ወንጀል ምንነት

አውደ ጥበባዊ የሕግ መዝገበ ቃላት ማስገደድ የሚለውን ቃል ትርጉም ሲሰጠው ማስገደድ (Coercion) አንድን ሰው በኃይል ድርጊት ወይም ከባድ አደጋ ለማድረስ በመዛት ወይም ህገ ወጥ በሆነ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ በተበዳዩ ነጻነት ላይ ጣልቃ በመግባት አንድን ነገር እንዲያደርግ ወይም እንዳያደርግ ወይም አንድ ነገር መደረጉን እንዲፈቅድ ወይም እንዳይፈቅድ ማስገደድ ነው በማለት ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ በተጨማሪም አንድ ሰው የስራ ግዴታው የሆነውን ተግባር እንዳያከናውን በዛቻ ፣በማስገደድ ወይም በኃይል ድርጊት ማሰናከል ወይም ይህን ግዴታውን እንዳያከናውን ወይም ማድረግ የሌለበትን እንዲፈጽም ማድረግ ወይም ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ባለው ሰው ላይ የዛቻ ፣የኃይል ድርጊት ወይም በማናቸውም የማስገደድ መንገድ በመጠቀም ተግባሩን ማሰናከል ወይም የማስገደድ ተግባር መፈጸም ነው በማለት ትርጉም ተሰጥቶት እናገኛለን፡፡

በንብረት ላይ በማስገደድ መጠቀም

በ1996 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 713 የሞራል ወይም የቁሳቁስ ማስፈራራትን የሚያካትቱ ወንጀሎች አንዱ ነው፡፡ አንድ አጥፊን በአንቀጽ 713 ስር ተጠያቂ ለማድረግ አጥፊው የማይገባውን የንብረት ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ሲል በተበዳይ ላይ የማንገላታት ተግባር ወይም ከባድ ዛቻ ፈፅሞ የተበዳይ ገንዘብን ወይም ዋጋ ያለውን ነገር ወይም ሰነድ ወይም መብት የሚሰጥ ወይም ዕዳ የሚያስቀረውን ወይም ማናቸውንም ይህን የመሳሰለ ጥቅም ያለበትን ነገር እንዲሰጠው ማድረጉን መረጋገጥ አለበት፡፡

በወንጀል ሕግ አንቀጽ 713 መሠረት ተከሣሽ የማይገባ የንብረት ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ሲል በሌላ ሰው ላይ የሚፈጽመው የኃይል ወይም ከፍ ያለ የዛቻ ድርጊት ገንዘቡ ወይም ንብረቱ እንዲሰጠው መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ባሻገር በወንጀል ሕግ አንቀጽ 713 የተጠቀሰው ወንጀል በዋናነት በሰነዶችና ሰነድን ከመሳሰሉ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ላይ ሊፈጸም ይችላል፡፡ በማስገደድ መጠቀም በንብረት ላይ ወንጀል ተብሎ የተፈረጀ ቢሆንም የማስገደድ እና ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን ሊያካትት ይችላል። በማስገደድ መጠቀም የሚከሰተው አንድ ሰው በህገ-ወጥ መንገድ ሌላ ሰውን በማስፈራራት ወይም በሥልጣን አላግባብ በመጠቀም ንብረትን፣ ገንዘብን ወይም ማንኛውንም ጥቅም እንዲወስድ ሲያስገድድ ነው። ይህም የግል ተበዳዩን ተጋላጭነት መሠረት በማድረግ ማስፈራራትን ፣ሃይልን ወይም ጉልበትን በመጠቀም የሚፈጸም ነው፡፡

አንድ ድርጊት በማስገደድ መጠቀም ነው ለማለት የድርጊቱ ፈጻሚ

  1. ዛቻ ወይም ጥቃትን መጠቀም (ጉዳትን ማድረስ) ፡- የግል ተበዳዩ ሊከሰት የሚችለውን ቅጽበታዊ ወይም ወደ ፊት ሊደርስ የሚችለውን ዛቻ ወይም ጉዳት መፍራት አለበት
  2. ወንጀለኛው ተጎጂውን ጉዳት እንደሚያደርስበት በማስፈራራት ንብረቱን እንዲሰጥ ሊያስገድደው ይገባል። ንብረት ማስረከብ ሊኖር ይገባል፡፡ ጉዳትን ማንም ሰው ሊፈራ ይችላል ይህ ፍራቻ የተጎጂውን አእምሮ እንዳይረጋጋ በማድረግ የተጎጂው ድርጊት ፈቃደኝነት እንዲቀይር በሚያስችል ሁኔታ ዛቻው እውን መሆን አለበት። ማስፈራራት ብቻውን በቂ አይደለም የተፈለገውን እቃ ለፈጻሚው ሊሰጠው ይገባል።
  3. ኢ-ፍትሃዊ ጥቅምን የማግኘት ፍላጎት፡ ድርጊቱ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ራስን ወይም ሌላውን ለማበልጸግ በማሰብ መሆን አለበት።

በማስገደድ መጠቀም ከሌሎች ንብረት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር ያለው ልዩነት

ውንብድና እና ስርቆት ንብረት ለመውሰድ ከሚፈጸሙት የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን አፈጻጸማቸውን ስንመለከት በማስገደድ መጠቀም ወንጀል በግል ተበዳይ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ ስነልቦናዊ ተጽእኖ በመፍጠር የሚፈጸም ሲሆን፤ ውንብድና ግን ቅጽበታዊ አካላዊ ጉዳት (immediate physical damage) በማድረስ ወይም ለማድረስ በመቃጣት የሚፈጸም ነው፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ እንደተገለጸው ዛቻ፣ ማስፈራራት ወይም ማስገደድ ዋጋ ያለውን ነገር (ንብረት፣ ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም) ከሌላ ሰው ማግኘትን ያካትታል። ስርቆት በሌላ መልኩ ያልተገባ ብልጽግና ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላ ሰውን ተንቀሳቃሽ እቃ ወይም ከማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የተነጠለን እቃ አንስቶ መውሰድ፤ በቀጥታ የራስ ንብረት ማድረግ ወይም በተዘዋዋሪ ከራስ ንብረት ጋር እንዲቀላቀል ማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ ውንብድና አንዱ የስርቆት አካል ቢሆንም ማንም ሰው በመበልጸግ ሀሳብ የሌላው ሰው ንብረት የሆነውን ተንቀሳቃሽ እቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው ወይም በሚወስድበት ጊዜም ሆነ ከወሰደ በኋላ የገጠመውን ተቃውሞ ለመቀልበስ በሌላ ሰው ላይ የኃይል ድርጊት መፈጸም ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ይህን ሰው ለመከላከል እንዳይችል ማድረግ የውንብድና ተግባር እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 670 ላይ ተቀምጦ ይገኛል፡፡

ስለሆነም ስርቆትና ውንብድና ላይ ንብረቱን የሚወስደው ራሱ ፈጻሚው ሲሆን በማስገደድ መጠቀም ላይ ግን ንብረቱ ከግል ተበዳዩ ወይም ከተጎጂው የሚወጣው በመገደዱ ምክንያት ንብረቱን አሳልፎ ሰጪው ተጎጂው ነው፡፡

በማስገደድ መጠቀም የሚያስከትለው ተጠያቂነት

በወንጀል ህጉ አንቀጽ 713 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው የማይገባውን የንብረት ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ሲል ገንዘብን ወይም ዋጋ ያለውን ነገር ወይም ሰነድ ወይም መብት የሚሰጥ ወይም እዳ የሚያስቀረውን ወይም ማናቸውንም ይህን የመሳሰለ ጥቅም ያለበትን ነገር እንዲሰጠው ለማድረግ ከወንበዴነት ወንጀል ውጭ (አንቀጽ 670) የሃይል ወይም ከፍ ያለ የዛቻ ድርጊት በሌላው ሰው ላይ የፈጸመ ወይም እንዳይከላከል ያደረገ እንደሆነ እጅግ ቢያንስ በ 3 ወር ቀላል እስራት ፣ወይም እንደ ወንጀሉ ከባድነት ከ 5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 715 መሠረት ቅጣቱ ከ 10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከ 10ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ሊቀጣ የሚችለው የማስገደድ መጠቀሙ የተፈጸመው

1. ህጋዊ ፈቃድ ያገኘበትን ሙያ ወይም ስራ ያለአግባብ በመሥራት ወንጀሉ የፈጸመው እንደሆነ ወይም

2. ወንጀሉን የፈጸመው ለአካለመጠን ያልደረሰውን ወይም ችሎታ የሌለውን ወይም መንፈሰ ደካማ የሆነውን ለመጉዳት እንደሆነ ፤ ወይም

3. አስቀድሞ ውጤቱን እየገመተ ድርጊቱን በመደጋገም በተበዳዩ ላይ የሀብት መራቆት እንዲደርስበት ወይም ተበዳዩ እራሱን እንዲገድል ገፋፍቶ እንደሆነ ነው፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ህብረተሰቡ በንብረቱ ላይም ሆነ በነጻነቱ ላይ በዛቻ በማስፈራራትና ከፍ ያለ ጉዳት በማድረስ ንብረታቸውን ሊነጠቁ የሚችሉበት ሁኔታ ስላለ ስለወንጀሉ አፈጻጸም በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ወንጀልን እንዲከላከል ማስቻል ነው ፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶት የተዘጋጀ