መግቢያ
ሰዎች አስበውም ይሁን በቸልተኝነት የወንጀል ተግባር ውስጥ ይገባሉ፡፡ የወንጀል ተግባር ውስጥ የተሳተፈ ሰው እንደተሳትፎው ደረጃ፣ እንደ ድርጊቱ ድግግሞሽ ወይም እንዳስከተለው የጉዳት መጠንና የጣሰው የወንጀል ሕግ ድንጋጌ መሠረት ተደርጎ የተለያዩ ክሶች ሊቀርቡበት ይችላሉ፡፡ አንድ ተከሳሽ አንድ ወንጀል ብቻ ፈፅሞ በሚገኝበት ጊዜ አንድ የወንጀል ክስ ብቻ የሚቀርብበት ሲሆን የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈፅም ወይም በአንድ ድርጊት ተለያዩ የወንጀል ድንጋጌዎችን ሲጥስ በተደራራቢ ወንጀሎች ክስ ይቀርብበትና በዛ መሠረት ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ቅጣት የሚጣልበት ይሆናል፡፡
በዚህ አጭር ፅሑፍ ስለተደራራቢ ወንጀል ምንነት እና በተደራራቢ ወንጀል የተከሰሰ ሰው የቅጣት አሰላልን አስመልክቶ ሕጉ ምን ይላል የሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ፡፡
የተደራራቢ ወንጀል ምንነት
ስለተደራራቢ ወንጀል ምንነት ከማየታችን በፊት ስለወንጀል ምንነት ማየት ያስፈልጋል፡፡ ወንጀል ሕገ-ወጥነቱና አስቀጭነቱ በሕግ የተደነገገን ድርጊት መፈፀም ሲሆን ይህም በሕግ የተከለከለን ድርጊት ማድረግ ወይም በሕግ የታዘዘን አለማድረግ ነዉ፡፡ አንድ በወንጀልነት የተደነገገ ወንጀል ተፈፀመ የሚባለዉ በድንጋጌው የተመለከቱ ወንጀሉን የሚያቋቁሙ ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተዉ ሲገኙ ብቻ ነዉ፡፡ ወንጀል ታስቦበት (ሆን ተብሎ) ወይም በቸልተኝነት ሊፈፀም ይችላል፡፡
ተደራራቢ ወንጀሎች (Concurrence offences) አንድ ወንጀል ፈፃሚ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ወንጀሎች ፈፅሞ ሲገኝ ያለውን ሁኔታ የሚመለከት ሲሆን በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 60 መሠረት ማንም ሰው ተደራራቢ ወንጀል አድርጓል የሚባለው፡-
- ሁለት ወይም ከሁለት የሚበልጡ አንድ ዓይነት ወይም የተለያዩ ማናቸውንም ዓይነት ግዙፍ ወንጀሎችን አከታትሎ የተደረገ እንደሆነ ወይም
- በአንድ ድርጊት በአንድ ጊዜ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ የሕግ ድንጋጌዎችን በመጣስ ወይም በአንድ ድርጊት ልዩ ልዩ ግዙፋዊ ውጤት የሚያስከተሉ ወንጀሎችን በመፈፀም ጣምራ ወንጀሎችን ያደረገ እንደሆነ ወይም
- በአንድ የወንጀል ማድረግ አሳብ ወይም ቸልተኝነት ያደረገው ወንጀል አንድን የሕግ ድንጋጌ የሚጥስ ሆኖ ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆነ ሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ አንድ ዓይነት ጉዳት ያስከተለ እንደሆነ ነው፡፡
ተደራራቢ ወንጀል ከደጋጋሚነት ጋር የሚያመሳስል አንደምታ ያላቸው ቢሆንም በወንጀል ፍትሕ ስርዓት ሂደት ጊዜ በክስ አመሰራረትና በክርክር ወቅት የተለያየ መንገድ የሚከተሉ ናቸው፡፡ ደጋጋሚነት ማለት አንድ ወንጀል አድራጊ ከተፈረደበት በኋላ ቅጣቱን በሙሉ ወይም በከፊል ከፈፀመበት ወይም በይቅርታ ከቀረለት ቀን ጀምሮ ባለው በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መነሻ ቅጣቱ ስድስት ወር የሆነ ቀላል እስራት ማስቀጣት የሚችል አዲስ ወንጀል አስቦ ሲፈፅም በደጋጋሚነት ቅጣትን ማክበድ እንደሚቻል በአንቀጽ 67 ላይ ተደንግጓል፡፡ ተደራራቢ ወንጀል የሚባለው ግን ከላይ እንደተገለፀው አከታትሎ የተደረገ ወንጀል ወይም በአንድ የወንጀል ድርጊት ከአንድ በላይ የወንጀል ድንጋጌዎች ተጥሰው ሲገኙ ስለመሆኑ ከአንቀጽ 60 ላይ መረዳት ስለሚቻል በሁለቱም መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
የወንጀሎች መደራረብ በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ አንደኛው የወንጀል ድርጊቶች በመደጋገም የተፈፀሙ ሲሆን ግዙፋዊ ተደራራቢ (Material Concurrence) ይባላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ተጠርጣሪ አከታትሎ ሰው ቢገድል፣ የሰው ንብረት ቢሰርቅ እና ሴት አስገድዶ ቢደፍር ሦስት ግዙፍነት ያላቸው ተደራራቢ ወንጀሎችን በመፈፀሙ በሦስት ክሶች የሚከሰስ ይሆናል፡፡ ይህም በአንቀጽ 60(ሀ) የተገለፀው የወንጀል አፈፃፀም ግዙፋዊ ተደራራቢት ነው፡፡ ሁለተኛ ወንጀሎቹ የተፈፀሙት በአንድ የወንጀል ድርጊት ከአንድ በላይ የወንጀል ድንጋጌዎችን በመጣስ ሲሆን ደግሞ ሀሳባዊ (ጣምራ) ተደራራቢ (Notional Concurrence) በመባል ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለትዳር የቅርብ ዘመዱን በሕዝብ ፊት አስገድዶ ቢደርፍ በአንድ ድርጊት አራት የወንጀል ድንጋጌዎችን የጣሰ (አንቀጽ 620ን በመጣስ አስገድዶ መድፈር፣ አንቀጽ 654ን በመጣስ በዘመዳሞች መካከል የሚፈፀም የግብረ ስጋ ግንኙነት ወንጀል፣ አንቀጽ 652ን በመጣስ አመንዝራነት እና 639ን በመጣስ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ስራን በአደባባይ መፈፀም) በመሆኑ በአራት ተደራራቢ ወንጀሎች የሚከሰስ ይሆናል፡፡ ይህም በአንቀጽ 60 (ለ) እና (ሐ) ስር ከተገለፁት የወንጀል አፈፃፀሞች ሀሳባዊ ወይም ጣምራ ተደራራቢነት የሚመደብ ነው፡፡
የተደራራቢ ወንጀሎች የቅጣት አሰላል
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ላይ ተደራራቢ ወንጀሎች በሚሆኑበት
ጊዜ ቅጣቱ ከብዶ ሊጣል እንደሚገባውና የቅጣት አሰላሉንም ጭምር በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ በዚህም መሠረት፡-
- ከተደራራቡት ወንጀሎች ለአንደኛው የሚጣለው ቅጣት የቀሪዎችን የሚያጠቃልል በሆነ ጊዜ፡- ከተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ በአንደኛው ምክንያት የሞት ወይም የዕድሜ ልክ እስራት ወይም ወንጀሎቹ ተመሳሳይ ዓይነት የእስራት ቅጣት የሚያስቀጡ ሆኖ በአንደኛው ምክንያት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተደነገገው ከፍተኛ ቅጣት ከተወሰነ ይህ ውሳኔ ለሌሎች ተደራራቢ ወንጀሎች የሚወሰነውን ቅጣት ሁሉ አጠቃሎ ይይዛል (አንቀጽ 184(1(ሀ))፡፡ ይህም ማለት ከተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ በአንዱ ምክንያት የሞት ቅጣት ወይም የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም የ25 ዓመት ፅኑ እስራት ከተወሰነ በሌሎች ተመሳሳይ ዓይነት ቅጣት በሚያስፈርዱ ወንጀሎች ምክንያት ከተገለፀው ቅጣት በላይ መወሰን አይቻልም፡፡
- በእስራት የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲሆኑ፡- ጥፋተኛው የፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች በእስራት የሚያስቀጡ ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች ከሆኑ ለእያንዳንዱ በተደራራቢነት ለተፈፀመው ወንጀል ተገቢ የሆነው ቅጣት ተወስኖ ሁሉም እንዲደመር ይደረጋል (አንቀጽ184(1)(ለ))፡፡ የሚጣለው ቅጣት በእስራት እና በገንዘብ ወይም በገንዘብ ብቻም ቢሆን ከላይ በተገለፀው አኳኋን ለእያንዳንዱ በተደራራቢነት ለተፈፀመው ወንጀል ተገቢ የሆነው ቅጣት ተወስኖ ሁሉም እንዲደመር ይደረጋል፡፡ (አንቀጽ 184(1) (ሐ)እና (መ))፡፡ አንድ ሰው የፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ከፊሎቹ የሚያስቀጡት በቀላል እስራት ከፊሎቹ ደግሞ በፅኑ እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች በሚሆኑበት ጊዜ ቅጣቶችን ለመደመር እንዲያመች ሁለት ዓመት ቀላል እስራት እንደ አንድ ዓመት ፅኑ እስራት ይቆጠራል (አንቀጽ184(1)(ለ))፡፡
- ጣምራ ተደራራቢ ወንጀሎች በሚፈፀሙበት ጊዜ፡- አንድ ተጠርጣሪ በአንድ ድርጊት የጣሰው አንድን የሕግ ድንጋጌ ብቻ ቢሆንም ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ካደረሰ ተደራራቢ ወንጀሎችን እንደፈፀመ እንደሚቆጠር በአንቀጽ 60(ሐ) ላይ ተደንግጓል፡፡ ቅጣቱ የሚወሰነውም በሌላ አኳኋን ካልተደነገገ በቀር ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች በሚፈፀሙበት ጊዜ ቅጣት በሚወሰንበት መንገድ ነው (አንቀጽ 184(2))፡፡
- የተዛመዱ ወንጀሎች በተፈፀሙ ጊዜ፡- የተዛመዱ ወንጀሎች ተፈፀሙ የሚባለው አንዱ ወንጀል የተደረገው ሌላ ወንጀል እንዲፈፀም ለማድረግ ወይም ለማመቻቸት ወይም ለተደረገ ወንጀል ከለላ እንዲሆን ለማድረግ ታስቦ ሲሆን ነው (አንቀጽ 63)፡፡ በመርህ ደረጃ የተዛመዱ ወንጀሎች በተፈፀሙ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ቅጣትን የሚወስነው በአንቀጽ 184 መሠረት ማለትም ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች በሚፈፀሙበት ጊዜ ቅጣት በሚወሰንበት መንገድ ነው (አንቀጽ 185(1))፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የተዛመዱ ወንጀሎች እንደ አንድ ነጠላ ወንጀል የሚቆጠሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም የሚሆነው ወንጀል ፈጻሚው ዋናውን ወንጀል ከግብ ለማድረስ ሲል ሌላ ወንጀል የፈፀመ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ሕግ አውጭው ተዛማጅ ወንጀሎችን እንደ አንድ ነጠላ ወንጀል በመውሰድ በወንጀል ሕጉ ውስጥ በአንድ ድንጋጌ ቅጣቱን አክብዶ በሚደነግግበት ጊዜ ነው (አንቀጽ 185(2))፡፡
- ተነጣጥለው ተሠጥተው የነበሩ ውሳኔዎችን ስለማጣመር፡- ጥፋተኛው ተፈርዶበት ቅጣቱን በመፈፀም ላይ ሳለ ወይም ከፈፀመ በኋላ ከፍርዱ በፊት የፈፀመው ሌላ ተደራራቢ ወንጀል መኖሩ ሲደረስበት ፍርድ ቤት ጥፋተኛው በፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች በአንድ ጊዜ ቢፈረድበት ኖሮ ሊወሰንበት ይችል የነበረው ከፍተኛ ቅጣት ሳያልፍ ይወሰናል (አንቀጽ 186(1))፡፡ ተጣምረው መታየት የነበረባቸው ወንጀሎች በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ወይም በተለያዩ ችሎቶች ታይተው ውሳኔ አግኝተው ከሆነ የጠቅላላ ቅጣቱ አወሳሰን ከዚህ በላይ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት ይሆናል (አንቀጽ 186(3))፡፡
ማጠቃለያ
ሰዎች አንድ ወንጀል ብቻ መፈፀማቸው አልበቃ ብሎ ከአንድ በላይ ወንጀሎችን ፈፅመው ሲገኙ በፈፀሙት ተግባር ልክ ቅጣት ካልተጣለባቸው በፈፃሚዎችም ሆነ በሌላው ሕዝብ ዘንድ አስተማሪነቱ ያን ያክል ግቡን የሚመታ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈፅመው በሚገኙበት ጊዜ አጥፊዎችን ባጠፉት ልክ መቅጣትና ማስተማር ስለሚገባ በወንጀል ሕጉ ዝርዝር ድንጋጌ ተቀምጦለት እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት