የአረጋውያን መብቶች

ማውጫ

Share this Article

አረጋውያን በእድሜ ዘመናቸው ዘርፈብዙ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ የኖሩ የሀገር ባለውለታዎች መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ሆኖም እድሜ በገፋ ቁጥር አቅም እየተዳከመ መሄዱ ተፈጥሯዊ ነውና አረጋውያን የሌሎች እንክብካቤ እያስፈልጋቸው የሚሄድ በመሆኑ ምክንያት ለጥቃት ወይም ለጉዳት ከተጋለጡ እና ልዩ ጥበቃ ከሚደረግላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች (Vulnerable Groups) መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ አረጋውያን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እና በሀገራዊ ሕግጋት ያላቸውን የሕግ ጥበቃ እንዲሁም የአረጋውያንን መብቶች መጣስ የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነት እንመለከታለን፡፡

አረጋውያን የሚባሉት እንማን ናቸው?

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትርጓሜ መሠረት እድሜአቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች አረጋውያን (old persons) ይባላሉ፡፡ በሀገራችንም በመንግሥት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 አንቀጽ 18(1)(ሐ) እንዲሁም በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014 አንቀጽ 18(1) መሠረት የጡረታ እድሜ 60 ዓመት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ይህም አንድ ሰው ለሀገር በቂ አግልግሎት አበርክቷል ተብሎ ከጡረታ መብት የሚጠበቅበትን እድሜ የሚያመላክት ነው፡፡

አለምአቀፍ እና አህጉራዊ የአረጋዊያን መብት ጥበቃ ሰነዶች

ሀገራችን ኢትዮጵያ ያፀደቀችው አለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ በተለይ አንቀጽ 22 እና 25(1) በቀደምትነት የሚጠቀስ ሲሆን አረጋውያን ደህንነታቸው የመጠበቅ እና መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው ማለትም የምግብ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳት እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የጤና ማኅበራዊ አግልግሎት የማግኘት መብት አላቸው፡፡ የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ ዲሴምበር 16/1991 የተባበሩር መንግስታት የአረጋዊያን መብቶች መርሆ (United nations Principles for Older Persons) በውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 46/91 አፅድቋል፡፡ ይህ የውሳኔ ሀሳብ (መርሆ) አምስት ዐበይት ክፍሎችና 18 አንቀፆችን ያካተተ ሲሆን አረጋውያን የሚከተሉት መብቶች በዋናነት እንዲከበሩላቸው ያበረታታል፡፡

ከጥገኝነት መላቀቅ (Independence)

ይህ መመሪያ አረጋውያን የምግብ፣ የውሃ፣ መጠለያ፣ ልብስንና የጤና አጠባበቅ ሁኔታ የመሳሰሉ መሠረታዊ የሰው ልጆች ፍላጎቶች በበቂ መጠን ማግኘት እንዲችሉ ማድረግን ወይም ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው ስልት መቀየስን የሚያካትት ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ደግሞ አረጋውያን ዕድሜያቸውና አቅማቸው በፈቀደ መጠን ክፍያ በሚያስገኝላቸው የሥራ መስክ የመሰማራት፣ ትምህርትና ሥልጣና የሚያገኙበትን መንገድ የማመቻቸትና ዕድል እንዲያገኙ ማስቻል መሆኑን ያመለክታል፡፡

ተሳትፎ (Participation)

አረጋውያን ለማህበረሰቡ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ መኖሩ ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው አሠራር አረጋውያን ማህበረሰባዊ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ በተለይም የአረጋዊያንን ጉዳይ በሚመለከቱ ፖሊሲዎች አቀራረፅና አፈፃፀም ረገድ የአረጋውያን ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን፣ አረጋዉያን በዕድሜ ያካበቱትን ዕውቀት፣ ችሎታ፣ ልምድና ሙያ ለወጣቱ ትውልድ ማስተላለፍ የሚችሉበትን አንዲሁም አረጋውያን ከፍላጎታቸውና አመለካከታቸው ጋር በሚጣጣሙ ማኅበራት ተደራጅተው ተሳትፎ የሚያደርጉበት ማኅበራዊ ስብስብ እንዲኖራቸው በማበረታታት አረጋውያን ማኅበረሰባዊ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ተግልጿል፡፡

እንክብካቤ (Care )

አረጋውያን የቤተሰብ አንክብካቤ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት ከጤና አጠባበቅ አንፃርም የጤና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው እንዲሁም የአረጋውያን መጠለያዎች እንዲደራጁና ሁኔታዎች አስገዳጅ ሆነው ሲገኙ በመጠለያው ለኑሮ ተስማሚ የሆነ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ይጠበቃል፡፡

እርካታ (Self Fulfillment)

አረጋውያን ዘመናቸው ሊያበረክቱ የሚችሉትን የካበተ ችሎታቸውን ለማሳደግ ዕድል እንዲያገኙ እንዲሁም ለትምህርታዊ፣ ለባሕላዊ፣ ለሃይማኖታዊና ለመዝናኛ ተግባር በሚያገለግሉ ማህበረሰባዊ ሀብቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ሊመቻችላቸው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ሰብዓዊ ክብር (Dignity)

አረጋውያን በቀሪው ዘመናቸው ተከብረው፣ ሰላማቸውና ፀጥታቸው ተጠብቆላቸው የመኖር እንዲሁም ከማናቸውም ብዝበዛና ከኃይልም ሆነ ከአእምሮ ያልተገባ ሥራ (Abuse) የመጠበቅ መብታቸው ሊከበርላቸው የሚገባ ሲሆን በዚህም ረገድ በዕድሜ፣ በጾታ፣ በዘር፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በአካል ጉዳት፣ በሀብት ደረጃ ወይም በሌላ ማናቸውም አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ፍትሐዊ በሆነ አያያዝ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው የተባበሩር መንግስታት የአረጋዊያን መብቶች መርሆ በአጽንዖት ይገልፃል፡፡

በተጨማሪ የመንግሥታት ተወካዮች አረጋዊነት በተመለከተ በማድሪድ ባደረጉት ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጉባዔ የአረጋዊነት ዓለም አቀፍ የድርጊት-መርሐ ግብር እ.ኤ.አ 2002ን አፅድቀዋል፡፡ ከድርጊት መርሐ ግብሩ አንፃርም አረጋውያንና ልማት፣ የተሻሻለ ጤንነትና ደኅንነት በአረጋዊነት ዕድሜ እና የተረጋገጠ ማኅበራዊ ዋስትና፣ የአቅም ግንባታ እና እገዛ የሚሰጡ ሁኔታዎች ተብለው በሚታወቁ ሶስት ተቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎችን መሠረት ያደረጉ ተግባራትን በብሔራዊ ደረጃና በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር ለማከናወን ቁርጥ አቋም አድርገዋል፡፡

ይህ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚደረግ እንቅስቃሴ በአህጉር ደረጃ በአፈሪካም የሚስተዋል ነው፡፡ የአፍሪካ መብቶች ቻርተር ያረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮልም አረጋዊያን ሊጠበቁላቸው ስለሚገቡ ዘርፈብዙ መብቶች የሚያመላከት አህጉራዊ ሰነድ ነው፡፡ ሀገራችን እ.ኤ.አ ጁላይ 2020 ከሌስቶ እና ቤኒን በመቀጠል ይህን ፕሮቶኮል አፅድቃለች፡፡

ሀገራዊ የአረጋዊያን መብት ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት በምዕራፍ ሦስት የተቀመጡት ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች አረጋውያንንም የሚያካትቱ ሆነው በተለይ ግን አንቀጽ 41(5) በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በድንጋጌውም መንግሥት አረጋውያንን ለማቋቋምና ለመርዳት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ ደረጃ እንክብካቤ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ አረጋውያኑም በማኅበር ከመደራጀታቸውም ባሻገር በዚሁ ዙሪያ የሚሰሩ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በመሥራት ላይ ናቸው፡፡

በተጨማሪም በመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 አንቀጽ 18 (1) (ሐ) እና በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014 አንቀጽ 18(1) መሠረት የጡረታ መውጫ ዕድሜ 60 በመሆኑ እና ከዚህ ዕድሜ በላይ ያሉት ሰዎች አረጋውያን ስለሚባሉ እንዲሁም በሠራተኝነት በማገልገላቸው የአገልግሎት ጡረታ አበል የማግኘት መብት አላቸው፡፡

የአረጋውያንን መብቶች መጣስ የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት

አረጋውያን ለሀገር ባለውለታ እንደመሆናቸው ከሁሉም አክብሮት እና እንክብካቤ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ማህበረሰቡም ለአረጋውያን ከፍ ያለ አክብሮት የመስጠጥ ባህል ያለው ነው፡፡ ሆኖም ይህን የማኅበረሰብ መልካም ባህል የሚጥሱ አይጠፉም፡፡ ከዚህ አንፃር የትኛውንም ወንጀል በዕድሜ ምክንያት ራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ሰዎች ለይ የሚፈፀም ከሆነ በፈፃሚው ላይ ቅጣት እንዲደሚያከብድበት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 84(1)(ሠ) ስር ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም በእድሜ መግፋት ምክንያት እራሳቸውን መከላከል በማይችሉ አረጋውያን ላይ ወንጀል መፈፀም ቅጣት ከብዶ እንዲጣልበት የሚያደርግ ነው፡፡

ሌላው ከአረጋውያን ጋር በተያያዘ የሚነሳው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ሲሆን በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 198 መሠረት ይህ ግዴታ የሚኖረው በቀጥታ ወላጆችና ተወላጆች ወይም በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች መካከል እንዲሁም በወንድማማቾች እና እህትማማቾች መካከል ነው፡፡ አረጋውያን እድሜአቸው በመግፋቱ ምክንያት ኑሯቸውን ለመግፋት የማይችሉ በሆነ ጊዜ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ሰዎች የቀለብ መስጠት ግዴታቸውን መፈፀም አለባቸው፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር እና ቀለብ ሰጪው ያለ በቂ ምክንያት ግዴታውን ያልተወጣ ከሆነ በተበዳይ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 658(ሀ) መሠረት በመቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡

በተጨማሪም አረጋውያን የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን የሌሎችን እገዛ በሚጠይቁበት ጊዜ በቅንነት የሚያግዙ የመኖራቸውን ያህል ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው የማታለል ወንጀል የሚፈፅሙ መኖራቸው አይካድም፡፡ ይህ ድርጊት በወንጀል ህጉ የሚያስቀጣ ሲሆን ማንም ሰው የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ እገዛ ለጠየቁ ለአረጋውያን አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር፣ የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር ወይም መግለፅ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የአረጋውያኑን የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቀም በማድረግም ሆነ ባለማድረግ አታልሎ የራሳቸው የአረጋውያኑን ወይም የሦስተኛ ወገን የንብረት ጥቅም የሚጎዳ አድረጎት እንዲፈፅሙ ያደረገ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ከባድነት አስከ አምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ እንደሚቀጣ ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 692 መረዳት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ አረጋውያን የሀገር ባለውለታ ከመሆናቸው አንፃር የሕግ ድጋፍና ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ የሚገባ ሲሆን መንግሥት የአረጋውያንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሕግ የተጣለበትን ሀለፊነት ሊወጣ እንዲሁም ማህበረሰቡ እና ሰቪክ ማህበራትም የበኩላቸውን ሊያበረክቱ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ