በዛሬው “የነጋሪት ገጾች” አምዳችን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 መሠረት ሀብቱ በህገ-ወጥ መንገድ የፈራ መሆኑን በተመለከተ ጥቆማ የማቅረብ ኃላፊነት ያለባቸውን አካላት በተመለከተ መረጃ እናጋራችሁ፡፡
ጥርጣሬዎችን ሪፖርት የማድረግ ግዴታ ያላባቸው አካላት
የፋይናንስ ተቋማትና ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የተሰየሙ የንግድና የሙያ ሥራዎች ገንዘብ ወይም ንብረት የወንጀል ፍሬ ስለመሆኑ ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ጋር የተያያዘ ወይም የተገናኘ ወይም ለዚሁ ተግባር ሊውል የሚችል ስለመሆኑ ሲጠረጥሩ ወይም ለመጠርጠር በቂ ምክንያት ሲኖራቸው ወዲያውኑ ጥርጣሬያቸውን ሪፖርት ማድረግ አለባቸው። ይህም ግዴታ ግብይት ለማድረግ የተፈጸመ ሙከራንም ይመለከታል።
የፋይናንስ ተቋም የሚባሉት፡-
ባንክ፣ መድን ሰጪ ኩባንያ፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም፣ የፖስታ ቁጠባ ተቋም፣ የሐዋላ ድርጅት፣ የውጭ ገንዘብ ምንዛሬ ተቋም ወይም ብሔራዊ ባንክ አግባብ ባለው የሕግ ማዕቀፍ መሠረት የፋይናንስ ተቋም ብሎ የሚሰይመው ማናቸውም ሌላ ተቋም ነው፤
ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ የተሰየሙ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የንግድና የሙያ ሥራዎች፡-
• የሪል ስቴት ወኪሎችና ደላሎች፤
• የከበሩ ድንጋዮች ወይም የከበሩ ብረቶች ነጋዴዎች፣
• ራሳቸዉን ችለዉ የሚሠሩ የሂሳብ ባለሞያዎችን ያካትታል
እኚህ አካላት በስራ አጋጣሚ ጥርጣሬ የሚፈጥር ነገር ካጋጠማቸው ጥቆማ የመስጠት ህጋዊ ግዴታ አለባቸው፡፡
ምንጭ፡- በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 2 እና 17