የቴሌኮሙኒኬሽን ቁጥሮች ውጤታማ ምደባ፣ አጠቃቀም እና አስተዳደር የሚያስፈልጋቸው ውስን ሀብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም የቴሌኮሙኒኬሽን ቁጥሮች በቅልጥፍና፣ በፍጥነት፣ በግልጸኝነትና በፍትሃዊነት እንዲሁም የደንበኛውን ደረጃ፣ የባለፈቃዱን ዓይነት እና የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አድልዎ በሌለበት ሁኔታ መመደባቸውን ማረጋገጥ እና ለደንበኞች ተደራሽ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የቴሌኮሙኒኬሽን ቁጥሮች አጠቃቀም የደንበኞችን ፍላጎት እና መብት እንዳይገድብ መከታተልና መቆጣጠር ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም ዘርፉ የሚመራበትን ግልጽ የአሠራር ስርሃት መዘርጋት የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም ባለስልጣኑ የቁጥጥር ስራን ለመሥራት እና ተፈጻሚ ለማድረግ ያስችለዋል፡፡
ይህንም መሠረት በማድረግ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የቴሌኮምኒኬሽን ቁጥር መመሪያን ያዘጋጀ ሲሆን ይህም በዘርፉ ውጤታማ ስራን መሥራት ያስችላል ተብሎ ይታመናል።