የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የልማት ድርጅቶች በኢኮኖሚ ውስጥ ተገቢ ድርሻቸውን ለመወጣት ሊመሩ የሚችሉበትን ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደር የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ተግባራዊነቱን የመከታተልና የመደገፍ እንዲሁም በተለያዩ የፕራይቬታይዜሽን ስልቶች የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን/አክሲዮን ማህበራትን ወደ ግል አልሚዎች የማዛወር ተልዕኮ ተሰጥቶታል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር ተግባር የመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ የተቀመጡ መሠረታዊ ሃሣቦች ሆነው ግቡ የገበያ ክፍተት የሌለባቸውና ለመንግሥት ስትራቴጅክ ያልሆኑ ድርጅቶችን በመለየት በሽያጭ፣ በጋራ ልማት፣ በኪራይና በማኔጅመነት ኮንትራት ወደ ግል ይዞታ በማዛወር ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የተሻለ የአገር ሀብት አጠቃቀም እና ተወዳዳሪ የሆኑ ድርጅቶች/ኢንዱስትሪ መፍጠር ለማስቻል ነው፡፡
በዚህ መሠረት በመንግሥት እጅ የነበሩ ድርጅቶች/አክሲዮን ማህበራት ወደ ግል አልሚዎች ከተላለፉ በኋላ የድህረ ፕራይቬታይዜሽን ስራዎች ማለትም በፕራይቬታይዜሽኑ የተሳተፉ ባለሀብቶች የገቧቸውን የክፍያ፣ የቢዝነስ ፕላን መፈፀም እና ሌሎች የውል ግዴታዎች በመከታተል ተፈጻሚነቱን ማረጋገጥና ተገቢውን ድጋፍ የመስጠት ስራዎችን ሊመራ የሚችል ማንዋል ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ ማንዋል ተዘጋጅቷል፡፡