የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮርፖሬትና ሀብት ሥራ አመራር ቢሮን መሠረታዊ የአሠራር ለውጥ ጥናት በማጠናቀቅ በተፈቀደው አደረጃጀት ላይ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል በምደባ ለማሟላት እንዲያስችለው ቅድመ ሁኔታዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሠረት በቢሮው የተጠናውን መሠረታዊ የአሠራር ለውጥ ጥናት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል የተዘጋጀውን አዲስ አደረጃጀት ተግባራዊ ለማድረግ እና እያንዳንዱ ሠራተኛ ይበልጥ ውጤታማ ሊሆኑ በሚችሉበት የሥራ ዘርፍ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመመደብ የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የደረጃ ዕድገት መመሪያ በሚፈቅደው መሠረት የሠራተኞች ድልድል መስፈርት ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል፡፡
የድልድል መስፈርቱ ሲዘጋጅ የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫ፣ የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ የትግበራ ስትራቴጂ ዕቅድ እንዲሁም የሌሉች ተቋማት ተሞክሮዎችን በመውሰድ እና የሚኒስቴር መ/ቤቱን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ በተፈቀደው አደረጃጀት ላይ የሠራተኞችን ድልድል ለማከናወን የተለዩት የድልድል መስፈርቶችም በተቻለ መጠን ሊለኩ የሚችሉ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል፡፡
በሲቪል ሰርቪስ በኩል እንደዋነኛ የብቃት መመዘኛ መስፈርቶች ተደርገው ሲወሰዱ የቆዩትን የትምህርት ዓይነትና ደረጃ፣ የሥራ ልምድና የማህደር ጥራት በመስፈርቱ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን፣ በተጨማሪ በዘርፉ የተያዘውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ በቢሮው በሚደረገው የድጋፍ አሰጣጥ የአመራሩና የሠራተኛው የቴክኒክ ብቃትና የባህሪ ሁኔታዎችን ከሥራ ብቃት አንጻር እንዲሁም እንደ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የሚጠበቁ የስነምግባር ሁኔታዎችና ለለውጥ ያለውን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ለመመዘን የሚያስችሉ : መስፈርቶችንና አመላካቾችን ለመለካት ይቻል ዘንድ ይህ የድልድል መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ የድልድል መመሪያው ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ተጠንተው ለሚቀርቡ ለሌሎች የመ/ቤቱ የሥራ ክፍሎች እንዲያገለግል ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡