የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን በማብቃት ቀልጣፋ፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራርና አመራር ማረጋገጥ በከተሞች ለመልካም ልማታዊ አስተዳደር መገንባትና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን ለመቆጣጠር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ በሌላ በኩል በከተሞች መልካም አስተዳዳር መስፈን ዜጎች ፍትሃዊ የመንግሥት እና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች እንዲያገኙ፣ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ልማት በማረጋገጥ ድህነትን በፍጥነት በመቅረፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑ በሚንስቴር መስሪያ ቤታችን መጋቢት/2006 ዓ.ም. በተዘገጀውና በመንግሥት በጸደቀው የተሸሻለው የከተሞች ልማታዊ መልካም አስተዳደር ግንባታ ማዕቀፍ እና የማስፈጸሚያ ስልቶቹ በሚለው ሰነድ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ ሰነድ ውስጥ በግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ላይ የተመሰረተ ማዘጋጀ ቤታዊ አገልግሎት ተሰጠ ለማለት የሚቻለው ማዘጋጃ ቤቶች የሚሰጧቸው አገልግሎቶች የትኞቹ እንደሆኑ፣ አገልግሎቶቹን ለማግኘት ከዜጋ ምን እንደሚጠበቅና ይህንንም በግልጽ እንዲያውቀው ሲደረግ፣ አገልግሎት ሰጪው በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ብቻ አገልግሎት ሲሰጥ፣ ተገልጋዩ ቅሬታ ያቀረበ ከሆነ ቅሬታ የቀረበለት አካል ውሳኔውንና ውሳኔ የሰጠበትን ምክንያት ለተጠቃሚው በጽሑፍ እንዲሰጥ ሲደረግ መሆኑን አስቀምጧል፡፡
ሆኖም አሁን በከተሞች እየታየ ያለው የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ በሚፈለገው ደረጃ የበቃ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ውጤታማ ሆኗል ተብሎ ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ በመሆኑም ለማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ ስታንዳርድ ማዘጋጀትና የተዘጋጁት ስታንዳርዶች በየከተሞቹ እንዲተገበሩ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በሌላ በኩልም በከተሞች መካከል ፍትሀዊ፣ ግልፅና ጤናማ የውድድር መንፈስ በመፍጠር ከተሞች እንዲለወጡ እንዲበረታቱና የሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እንዲሁም የማኅበራዊ ለውጥ ማዕከል እንዲሆኑ ድጋፍ ማድረግ፣ መከታተልና ግብረመልስ መስጠት የሚኒስቴር መ/ቤቱ ዋነኛ ተልዕኮው በመሆኑ፤ ውጤትን መሠረት ያደረገ ዘላቂነት ያለው የምዘና፤ የውድድርና የዕውቅና ሥርአት መዘርጋትም አስፈላጊነቱ የጎላ ነው::
በዚሁ መሠረት የተዘጋጁትን የአገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርዶች በከተሞች ግልጽነትና ተጠያቂነት በተሞላበት አኳኋን ለማስተግበርና በቀጣይም ጥራት ያለው የአገልግሎት አቅርቦት የአፈጻጸም ምዘና ለማከናወን፣ ሂደቱንም ስርዓት ባለው መንገድ ለመምራት እንዲሁም አሰራሩን ግልጽ፣ ወጥና በዘላቂነት እንዲያሰራ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ይህ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ስታንዳርድ ማስተግበሪያና የአገልግሎቶች አቅርቦት የአፈጻጸም ምዘና መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡