መንግሥት የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ዘርፍ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረጽ ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠርና በከተማችን የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህ መሠረት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተደራጁ ዜጎችን የገበያ ድጋፍ በመስጠት በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተደራጅተው የሚሰሩ ኢንተርፕራይዞች የውጭ ምርት እንዲተኩና በገበያው ላይ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር በመቅረፍ ለከተማዋ ነዋሪ ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርትና አገልግሎት እንዲያቀርቡ እገዛ እየተደረገ ነው፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ሥራ ለሚገቡ ነዋሪዎች በአካባቢ፣ በክልልና በውጭ ገበያ ተጠቃሚ የሚሆንበትን የድጋፍ ስርዓት በመዘርጋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ የሚገኝ ቢሆንም እስካሁን ያለው የገበያ ድጋፍ አሰጣጥ ሁኔታ የኢንተርፕራይዞችን ብቃትና ተወዳዳሪነት የማያበረታታና ውስን ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያሳትፍ እንደነበር ይታወቃል፡፡
የገበያ ልማትና ግብይት አገልግሎቶች ኢንተርፕራይዞች ከሚፈልጉት ድጋፍ አንፃር ፍትሃዊነት የጎደለው ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለው፤ የኢንተርፕራይዞችንና ምልልስ የሚጨምር ለብልሹ የሆኑ አሰራሮች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር ከመፍጠር አንፃር ክፍተት የነበረበት መሆኑን ለማየት የተቻለ ሲሆን ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ወጥነት ያለው የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 64/2011 አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ (3)(ሠ) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡