ሀገራችን የጀመረችውን ፈጣን የኢኮኖሚ፣ የልማትና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በማስቀጠል የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በላቀ ደረጃ ለማሳካት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ሴክተር አቀፍ የትኩረት መስኮችን ለይቶ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በጥረት ተደራሽ የሆነና ሀገራችን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተላቃ በዕድገትና የልማት ጐዳና እንድትገሰግስ የታለመና ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን እያሳየ ያለ ዕቅድ መሆነ ይታወቃል። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሀገራዊ ዕቅዱን ከማሳካት አኳያ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማትና ሥራ ፈጠራ፣ በከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት፣ በከተሞች መሠረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በከተሞች መልካም አሰተዳደር፣ የመኖሪያና የመንግሥት ቤቶች ልማት እና በመሳሰሉት ዘርፎች በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ነገር ግን የበላይ አመራሩ በተዋረድ ለሚገኙ አመራሮች ሥልጣንና ኃላፊነትን በመስጠት ስትራቴጂክ ዕቅዱን በማሳካት የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወንና ዘመኑ የሚጠይቀውን የአመራር ዘይቤ፣ ክህሎት፣ አሠራር፣ ሠራተኛ፣ መዋቅር አደረጃጀት እና የጋራ ዕሴቶችን መገንባት ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም ለላቀ ዉጤታማነት መሠረት የሚሆኑትን ማለትም ትክክለኛ የአመራር ዘይቤ፣ ክህሎት፣ አሠራር፣ ሠራተኛ፣ መዋቅር/አደረጃጀት እና የጋራ ዕሴቶችን እየተተገበረ ካለው የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥና ሚዛናዊ የውጤት ተኮር ሥርዓት ትግበራ ጋር በማቀናጀትና በማስተሳሰር የአሠራር ሥርዓትን በማሻሻል የአገልግሎት ቅልጥፍናን፣ የሥራ ውጤታማነትን፣ ተጠያቂነትንና ግልፀኝነትን ባጣመረ መልኩ ዕውን በማድረግ ተቋማት ተልዕኳቸውን በላቀ ደረጃ እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ትክክለኛ የአደረጃጀትና የአሠራር ሥርዓት ብቻ ለላቀ ውጤት ስለማያበቃ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራት በነገሠባቸው የሥራ ዘርፎች የልማታዊ አስተሳሰብ እንዲሰፍን በማድረግ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን በመፀየፍ በቁርጠኝነት የሚታገል አስፈፃሚና ፈፃሚ ለመፍጠር ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ሊያሰፍን የሚችል የአሠራር ሥርዓት ከመፍጠር ባሻገር የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን ይጠይቃል፡፡ በዚህም መሠረት የበላይ አመራሩ የጋራ ዕምነቶቸን በመገንባትና የጠራ አመለካከትን በመፍጠር የሚኒስቴር መ/ቤቱን ተልዕኮ የማሳካት ሚናቸውን ለመወጣት የተለያዩ መመሪያዎችንና ማንዋሎችን ማዘጋጀትና ለተግባራዊነታቸው ግንባር ቀደም ሆኖ መፈፀምና ማስፈፀም ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም በየደረጃው የሚታየውን የማስፈፀም አቅም ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመፍታት ያልተማከለ አስተዳደርን አጠናክሮ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት ዓመታዊ እቅዱ እስከ ግለሰብ በሚወርድ መንገድ ምን እንደሚሰራ፣ ለምን እንደሚሰራ፣ መቼ እንደሚሰራና በማን እንደሚሰራ በአግባቡ መመለስ የሚያስችል የአመራር፣ የአሠራርና የተግባር አፈፃፀም መመሪያ መኖሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ይታመናል::
በመሆኑም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 25 በተሠጠው ሥልጣን መሠረት በየእርከን ደረጃው ያለውን አሠራር በተቀናጀ መልኩ በሥርዓት ለመምራት እንዲቻል ይህን የአመራር፣ የአሠራርና የተግባር አፈፃፀም መመሪያ አውጥቷል፡፡ መመሪያው ዘጠኝ ክፍሎችና 39 አንቀጾች ሲኖሩት የመጀመሪያው ክፍል የመመሪያውን ዓላማ፣ አስፈላጊነት፣ የተፈፃሚነት ወሰን፣ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በአዋጅ የተሠጠውን ሥልጣንና ተግባራት፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱን ተልዕኮ፣ ራዕይ፣ ዕሴቶች፣ ቁልፍ የትኩረት መስኮችና በየቢሮው የሚከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችን ያካትታል፡፡ በክፍል ሁለት ስለ (የሥራና በጀት) ዕቅድ ዝግጅት የአፈፃፀም ክንውንና የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓትን የተመለከቱ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ ክፍል ሶስት የግዢ ጥያቄ አቀራረብ እና የንብረት አጠባበቅ መርሆዎችን ይዟል ።
በክፍል አራት – አጠቃላይ የክትትል፣ ግምገማና ግብረ-መልስ ሥርዓት እና የተቀናጀ የውጤት ተኮር ምዝና ትግበራን የተመለከቱ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ በክፍል አምስት ለተግባር ስኬት ወሳኝና አጋዠ የሆነ የችግር መፍቻ ስልቶችን፣ የአመራራ፤ ክትትልና ድጋፍ ዘይቤ፣ የውክልና አሰጣጥ አግባብ፣ የኮሚቴ ሥራንና የጊዜ ሰሌዳ አከባበርን የተመለከቱ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ በክፍል ስድስት የተጠሪነት፣የግንኙነትና የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓትን የተመለከቱ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ በክፍል ሰባት የጉባኤ የሚኒ ካቢኔ፣ስትራቴጂያዊ አመራር፣ የሥራ አመራር ኮሚቴና የቴክኒክ ቲም፣ አካላት አደረጃጀት፣ መርሆዎች እና ተግባርና ኃላፊነቶችን ይመለከታል፡፡ በክፍል ስምንት የስብሰባ ሥርዓትና የውሳኔ አፈፃፀም አግባብን የተመለከቱ ጉዳዮች ተካተዋል በመጨረሻም በክፍል ዘጠኝ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አደረጃጀቶችና አሰራሮችን ማመቻቸትን የተመለከቱ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡