የትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል የአገራችን የትምህርትና ሥልጠና ስርዓት ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ የዕድገት ሁኔታ፣ ከሰው ኃይል ፍላጎትና አግባብነት ካላቸው የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሁም ለልማት ጉዞ ውስጥ ቀዳሚ ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ተልዕኮውን በትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ሀገራዊ ሃላፊነቱን የሚወጣ ተቋም ነው፡፡
ይህንን ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት በየደረጃው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በየሥራ ዘርፋቸው የሚሰጡት አመራር በተቀረፀው አሠራርና መመሪያ መሠረት የሚከናወን ቢሆንም አልፎ አልፎ በአዋጅ፣ በመመሪያና ደንቦች ብቻ ሊፈፀሙ የማይችሉና የጋራ ውሣኔ የሚሹ ጉዳዮችን ማየትና መወሰን የሚችል የሥራ አመራር አካል ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡
በዚህም መሠረት የሥራ አመራር አካሉ አፈጻጸም መመሪያ፣ የጋራ ተጠያቂነትን ሥርዓትን ማጐልበት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ የአመራር ኰሚቴው አባላትን በኰሚቴው የሚወስኑ ጉዳዮችንና አጠቃላይ ሁኔታን የሚገልፅ አጭር መተዳደሪያ መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ይህ መመሪያ የበላይ አመራሩን ሥልጣን የሚተካ ሳይሆን እንደአስፈላጊነቱ የሚደግፍ ይሆናል፡፡