ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን የሚጠበቅባቸውን ብቁ የሰው ኃይል ያፈሩ ዘንድ፣ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች እንዲያከናውኑ እንደዚሁም ውጤታማ የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባራት ማከናወን እንዲችሉ የመምህራኑ ሚናና አስተዋጽኦ ከወሳኝ በላይ በመሆኑ ፣ መምህራን በአገራችን ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የበለፀገ ኢኮኖሚና ማኅበረሰብ በመፍጠር ስራ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ መወጣት ስለሚጠበቅባቸው
መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግኑኝነት በአካዳሚያዊ ቤተሰባዊነት መልኩ መቃኘት ያለበት በመሆኑና መምህራን ለተማሪዎቻቸው ለአጠቃላይ የትምህርት ማኅበረሰብና መላው ሕዝብ በሚሰጡት ፍቅር፣ ለአገር ባላቸው ተቆርቋሪነትና ለስራ በሚሰጡት ክብር መልካም ተምሳሌትና አርአያ መሆን ስለሚጠበቅባቸው፤
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ ትምህርት ትሩፋት እንዲለወጡ በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ መምህራን የማህበረሰቡን እሴቶች በማክበርና በፍፁም ጨዋነት አብረው መሥራት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ በሚያስቀምጠው መሠረት ተቋማት የሰው ኃይላቸውን እንዲቀጥሩ ፣ እንደሚያለሙና በውጤታማነት ላይተመስርተው እንዲያበረታቱ እንዲያቆዩ ወይም እንዲያሰናብቱ ለማስቻል አገራዊ የሆነ ወጥ መመሪያ በማስፈለጉ
ተቋማት መምህራንንም ሆነ ሌሎች የተቋሙን ሰራተኞች ለመቅጠር፣ ለማስተዳደርና ለማልማት በአዋጅ የተሰጣቸው ነጻነት እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ አገር አነስተኛውን የመምረጫ መሰፈርትና ተቋማት መከተል ያለባቸውን ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ይህ በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአገር ውስጥ መምህራን ምልመላ፣ ቅጥርና ልማት ሥርዓት መመሪያ ወጥቷል፡፡